ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓም

ኢሳት የሚዲያ አፈና ሊፈጽም ቀርቶ አፈናን ማሰብ እንኳን አይችልም!

ሰሞኑን ጋዜጠኛና አክቲቪስት ርዮት አለሙ ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ያደረገችው ሙሉ ቃለ ምልልስ ታርሞ እንዲተላለፍ መወሰኑን ተከትሎ ድርጊቱ “አፈና ነው” የሚል እንደምታ ያለው መልክት በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ተመለክተናል፡፡ መልዕክቱ ኢሳት ከቆመለት አላማ ጋር የሚጻረር በመሆኑ የኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ ተወያትቶበታል።

ኢሳት የአቅም ውስንነት፣ የቦታ ርቀት እንዲሁም ተደጋጋሚ የአፈና ሙከራዎች ሳይበግሩት የኢትዮጵያን አየር ሞገድ እየሰነጠቀ በመላው አገሪቷ ጨለማን የገፈፈ ፈርቀዳጅ የሚድያ ተቋም መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግልም ላለፉት 9 ዓመታት በኢሳት ዙሪያ የተሰባሰቡ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የለውጥ አቀንቃኞች ብቻ ሳይሆኑ በአለም ዙሪያ የተደራጁ ደጋፊዎች ለኢሳት ስኬት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

ዛሬ በአገራችን ያለው ሁኔታ በአንድ በኩል ተስፋና እድል የያዘ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ስጋትና ጭንቀትን እያስከተለ በመሆኑ ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች ብሎ መናገር ይቻላል። መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ አገር፣ ወደ ተሻለ ጎዳና ትሄድ ዘንድ ኢሳትን የመሳሰሉ ሃላፊነት የሚሰማቸው የሚዲያ ተቋማት ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ አገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ኢሳት ከልብ ያምናል።

ኢሳት ተቺና ሞጋች ሚድያ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች በተቻለ አቅም ሚዛናዊና ከስሜት የጸዱ እንዲሁም የሚተላለፉ ዘገባዎችም ሆኑ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ከግል አመለካከት እና ከግል ሃሳቦች ይልቅ የነጠሩ ሃቆች (facts) ላይ መሰረት ማድረጋቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ኢሳት ላለፉት 9 ዓመታት ሲመራበት የቆየ መርህ ሲሆን፣ ይህንንም አገር ውስጥ የተፈጠረውን የሚዲያ ነጻነት በመጠቀም ከእስከዛሬው በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ይንቀሳቀሳል ።

እንደሚታወቀው የሚድያ ተቋማት ለህትመት ወይንም ለአየር የሚያበቋቸውን ይዘቶች አይተውና ገምግመው፣ የሚወጣውን ቆርጠው የማውጣት፣ መውጣት የሌለባቸውን ደግሞ ቆርጠው የማስቀረት ሙሉ ስልጣን አላቸው። ይህ አሰራር በኢሳት በኩል ላለፉት 9 ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ እና ዛሬም ሆነ ነገ የሚቀጥል ነው። ይህን ደግሞ ኢሳት ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ ያሉ በሚዲያ ስነምግባር የሚመሩ ሃላፊነት የሚሰማቸው የሚዲያ ተቋማት የሚጠቀሙበት አሰራር ነው።

ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ያደረገቸው ቃለ ምልልስ በየደረጃው ባሉ ኤዲተሮች ታይቶ ችግር እንዳለበትና አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎ እንዲወጣ ለአዘጋጅዋ በክብር ተገልጾላታል። በዝግጅቱ ላይ ያሉት ጉድለቶች ለአዘጋጁዋ በተላከው ደብዳቤ ላይ በግልጽ የሰፈረ በመሆኑ፣ እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢ አይሆንም።

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ኢሳት ውስጥ አፈና የሚካሄድ አስመስሎ ማቅረብ ትክክል ያልሆነ፣ ላለፉት 9 ዓመታት ችግሮችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ ባህል ያዳበረውንና ለማንም የሚዲያ ተቋም አርዓያ መሆን የሚችለውን ተቋም፣ ከተለመደው ባህሉ ወጥቶ በጫና የሆነ ፍላጎትን እንዲፈጽም የሚያስገድድ ኢ፟፟ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። ኢሳት እንኳንስ በውስጡ ላሉት ጋዜጠኞች ቀርቶ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ መተንፈሻ የሆነ ሚዲያ ነው። አርሶ አደሮች፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ የፋብሪካ ሰራተኞች፣ ወታደሮች፣ ነጋዴዎች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም በተለያየ ማህበራዊ እርከን ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ሃሳብ ማራመድ ብቻ ሳይሆን ብሶታቸውንና ተስፋቸውን አጉልተው የሚያሰሙነት የሚድያ ተቋም መሆኑ በስፋት የሚታወቅ ሃቅ በመሆኑ ይሄንኑ አጠንክሮ ይቀጠላል።

ኢሳት ትናትንም፣ ዛሬም ወደፊትም የሚዲያ አፈና አያደርግም። ገና ለገና የሚዲያ አፈና ዘመቻ ይካሄድበታል በሚልም የሚዲያ ነጻነት የሚያጎናጽፈውን የአርትዖት ስራ ከመስራት ወደ ሁዋላ አይልም።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢሳትን የተሻለ ደረጃውን የጠበቀ ፕሮፈሽናል የሚድያ ተቋም ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢሳትን ደከመን ሰለቸን ሳትሉ፣ ላለፉት 9 ዓመታት ከፍተኛ መስዋትነት ከፍላችሁ ላቆማችሁት የኢሳት ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመግለጽ ይወዳል።

የኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *