ኢትዮጵያ በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት በሁለት ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈፀመ ግድያ ተጠርጥሮ በሀገሪቱ ፖሊስ የሚፈለገውን በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ አሜሪካዊ የሆነውን አቶ ዮሃንስ ነሲቡ በዛብህን ለአሜሪካ መንግስት አሳልፋ ለመስጠት ወሰነች።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው፥ የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዲቪዥን በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በሁለት ሰዎች ሞት እና በሁለት የጦር መሳሪያን ያለአግባብ በመጠቀም ወንጀሎች ግለሰቡ መጠርጠሩን እና አሁን ላይ በኢትዮጵያ እንደሚገኝ በመግለፅ ተላልፎ እንዲሰጥ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ በኩል ጥያቄውን ለመቀበል የሚያስችል ማረጋገጫ ከአሜሪካ መንግስት በኩል እንዲሰጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ተናግረዋል።

Related stories   እነ ጃዋር " በዛሬው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁ አይደለንም" ሲሉ የመማከሪያ ጊዜ ጠየቁ

በዚህም መሰረት የተከናወነው የወንጀል ምርመራ ውጤትን በሰነድ በማያያዝ አሜሪካ ማቅረቧን ነው ያመለከቱት።

በሰነዱም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ ካውንቲ ፍርድ ቤት ግለሰቡ መከሰሱን እና በፈረንጆቹ መጋቢት 23 ቀን 2017 የእስር ትእዛዝ እንደወጣበት አረጋግጧል።

በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ 6 ንዑስ ቁጥር 12 በወንጀል ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ትብብር እንዲያደርግ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት ተጠርጣሪው ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት መወሰኑን አቶ ዝናቡ አስታውቀዋል።

Related stories   ሰበር ዜና - ቀዳማዊት እመቤት 12ኛውን ትምህርት ቤት አስረከቡ

ተላልፎ እንዲሰጥ ሲወሰንም  ተፈላጊው ግለሰብ ዜግነቱ አሜሪካዊ መሆኑ እና ግድያ የተፈፀመባቸው ሁለቱ ሰዎች ኢትዮጵያውያን  መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት መሆኑ ተመልክቷል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ መሰረት የተፈፀመውን ወንጀል የመዳኘት ስልጣን በዋናነት የኢትዮጵያ አለመሆኑ እና ግለሰቡ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የሰብዓዊ መብቱ እንደሚጠበቅ ከአሜሪካ በኩል ማረጋገጫ መሰጠቱ ከግንዛቤ ተወስዷል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩል ተመሳሳይ የትብብር ጥያቄ ለአሜሪካ ከቀረበ የጉዳዩን ይዘት በማየት ትብብር ከዋሽንግተን በኩል እንደሚደረግ ማረጋገጫ በመሰጠቱም ውሳኔው ተላልፏል ነው ያሉት።

Related stories   ህገወጥ ሰው አዘዋዋሪ ወንጀለኞችን ለመመርመርና ማስቀጣት የሚያስችል አዲስ የሰነድ ርክክብ ተደረገ

በሌላ በኩል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል በፍትህ ዘርፍ እየተደረገ ያለው ግኑኝነት እና የትብብር መንፈስ አወንታዊ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጥ መወሰኑን አቶ ዝናቡ አስረድትዋል።

በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪው ግለሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፥ አሳልፎ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

FBC

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *