ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

አጫጭር የውጭ ዜና

ኢራን የአሜሪካ ማዕቀብ ከኒውክሌር ስምምነቱ እንድትወጣ ሊያደርጋት እንደሚችል አስታወቀች

ኢራን የአሜሪካ ማዕቀብ ከኒውክሌር ስምምነቱ እንድትወጣ ሊያደርጋት እንደሚችል አስታወቀች። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃባድ ዛሪፍ ቴህራን የዋሽንግተንን አዲስ ማዕቀብ ተከትሎ ሌላ አማራጭ ለማየት እንደምትገደድ ተናግረዋል።

ከአማራጮቹ አንዱ ደግሞ ቴህራን ከሃገራት ጋር ስምምነት የደረሰችበትን የኒውክሌር ፕሮግራም ስምምነትን ማቋረጥ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት። ጃባድ ዛሪፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የኒውክሌር ስምምነቱ አካል የሆኑት የአውሮፓ ሃገራትም ኢራንን እያገዟት እንዳልሆነም ገልጸዋል።

አሜሪካና ኢራን ያላቸው ግንኙነት በተለይም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ይበልጥ ሻክሯል። ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አሜሪካን ከ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት ውጭ አድርገዋታል።

ከሳምንት በፊትም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ በአሸባሪነት የፈረጁ ሲሆን፥ ሃገራት ከኢራን ምንም አይነት ነዳጅ እንዳይገዙም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ይህን ተላልፈው ለነዳጅ ገበያ ቴህራን ጋር የሚደራደሩ አካላት ካሉም ከባድ ማዕቀብ እንደሚጥሉ መግለጻቸውም የሚታወስ ነው። ይህን ተከትሎም የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ እየተባባሰ መምጣቱ ይነገራል።

ሩሲያ አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ለመፈጸም ፈቃደኛ መሆኗ ተነገረ

ሩሲያ አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ለመመፈጸም ፈቃደኛ መሆኗ ተነገረ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያና ከቻይና ጋር አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ባለስጣኖቻቸው በጉዳዩ ዙሪያ ከሃገራቱ ጋር የሚደረገውን ድርድር እንዲያስጀምሩ ትዕዛዝ አስተላለፍዋል።

ሞስኮም በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገርነ ስምምነት ለመፈጸም ዝግጁ ስለመሆኗ ሬውተርስ የክሬሚሊን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረዳት አማካሪ  ዩሪ ኡሻኮቭን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ረዳት አማካሪው በሃገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ባደረጉት ንግግርም ሞስኮ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ስለመሆኗ አመላክተዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ግን የትራምፕን እቅድ እርግጠኛ ያልሆነ በማለት ገልጸውታል። ትራምፕ በጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር እንዲደረግ ፍላጎት እንዳላቻው ይነገራል።

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

ለዚህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለና አዲስ የጦር መሳሪያ ዝውውርን የሚቆጣጠር ህግ ይኖር ዘንድ ከሞስኮና ቤጂንግ ጋር ለመደራደርና ስምምነት ላይ ለመድረስ ማሰባቸው ነው የሚነገረው።

የሱዳን ተቃዋሚዎች ከአገሪቱ ጦር ሰራዊት ጋር ጥምር የሽግግር ምክር ቤት ለመመስረት መስማማታቸውን አስታወቁ። በትናንትናው ዕለት የተደረሰው ስምምነት የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ከተወገዱ በኋላ ሥልጣን የተቆናጠጠውን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ይተካል። ከጦሩ ዋና ዕዝ ደጃፍ ተቀምጠው ተቃውሞ ሲያሰሙ ከከረሙ ዜጎች አንዱ የሆኑት መሐመድ አሚን በትናንትናው ዕለት የተደረሰው ስምምነት የሲቪል መንግሥት ለማቋቋም አንድ እርምጃ ነው ብለዋል። ሲቪሎች ከጦር ሰራዊቱ ጋር የሚያቋቁሙት ምክር ቤት ሁሉንም አስተዳደራዊ ጉዳዮች በበላይነት የሚመራ ሲሆን የሱዳንን የዕለት ከዕለት ጉዳዮች ለማስፈፀም ወታደሮች የማይኖሩበት የሽግግር መንግሥት ይቋቋማል። የሽግግር መንግሥቱ አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የመጀመሪያውን ምርጫ የማሰናዳት ኃላፊነት ይኖረዋል።የተቃውሞው መሪ አሕመድ አል-ራቢያ በጥምር ምክር ቤቱ ውስጥ ምን ያክል ሲቪሎች ምን ያክል ወታደሮች ይካተቱ የሚለውን ለመወሰን ምክክር እየተደረገ መሆኑን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች 250 ሚሊዮን ዶላር በሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ እንደምታደርግ አስታወቀች። በመንግሥት የሚተዳደረው የአቡ ዳቢ የልማት ፈንድ ገንዘቡን ለመስጠት ከሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ጋር ስምምነት መፈራረሙን የአገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል። በነዳጅ ዘይት የናጠጡት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለሱዳን 3 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል የገቡት ባለፈው ሳምንት ነበር። ከዚህ መካከል 500 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ ለሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ገቢ ይሆናል። ቀሪው 2.5 ቢሊዮን ዶላር በምግብ፣ መድሐኒት እና የነዳጅ ውጤቶች ለሱዳን ይደርሳል።

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቤኒን ዜጎች ያለ አንድ ተቃዋሚ የሕዝብ ተወካዮቻቸውን ሲመርጡ ዋሉ። ዛሬ ማለዳ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት የምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ የአገሪቱ ዜጎች የፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን አጋር የሆኑ ሁለት ፓርቲዎች ካቀረቧቸው እጩዎች መካከል 83 የምክር ቤት አባላትን መምረጥ ጀምረዋል።በቅድመ-ምርጫው በአገሪቱ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች በኃይል ተደፍጥጠዋል። በትናንትናው ዕለት የተቃዋሚ ይዞታ በሆኑ አካባቢዎች በተቆጡ ዜጎች መንገዶች ተዘግተው ታይተዋል። የአገሪቱ መንግሥት የመልዕክት መለዋወጫዎች እና ማኅበራዊ ድረ-ገፆችን በመዝጋት የኢንተርኔት አገልግሎትን ገድቧል።አምስት ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ ለመስጠት ቢመዘገቡም የቤኒን የኤኮኖሚ ዋና ከተማ በሆነችው ኮቶኑ ወደ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የሔዱት ዜጎች ጥቂት መሆናቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። እጩዎቻቸውን ከማስመዝገብ የተከለከሉ ዋና ዋና የተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱ ዜጎች በምርጫ ከመሳተፍ እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በኢንዶኔዥያ ከ270 በላይ የምርጫ ሰራተኞች የስራ ጫና ባስከተለባቸው ሕመም ሳቢያ መሞታቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ። ለረዥም ሰዓታት የምርጫ ሒደትን ሲከታተሉ የነበሩ ሰራተኞች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በእጃቸው ለመቁጠር ተገደው ነበር። የኢንዶኔዥያ የምርጫ ኮሚሽን ቃል አቀባይ አሪፍ ፕሪዮ ሱሳንቶ እንዳሉት ሌሎች 1,878 የምርጫ ሰራተኞች ታመው አልጋ ይዘዋል።ባለፈው ሚያዝያ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሔደው የኢንዶኔዥያ ምርጫ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች በድምፅ ቆጠራው ተሳትፈዋል። የምርጫ ሰራተኞች ያለ ማቋረጥ ቀን እና ለሊት ለመስራት በመገደዳቸው አካላዊ ጫና ተፈጥሮባቸዋል። ድምፅ መስጠት ከሚችሉ 193 ሚሊዮን የኢንዶኔዥያ ዜጎች መካከል 80 በመቶው በ800,000 ጣቢያዎች መርጠዋል። የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ቃል-አቀባይ በአሰልቺ እና አድካሚው ሥራ ሳቢያ 272 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል። የምርጫ ኮሚሽኑ ለሟች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 36 ሚሊዮን ሩፒ (2,500 ዶላር) ካሳ ለመክፈል ማቀዱን አንድ የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

በጀርመን ሐምቡርግ ከተማ በተካሔደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆኑ። በወንዶች ጎራ በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያዊው ታዱ አባተ ቀዳሚ ሆኗል። ባለፈው አመት ውድድሩን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ታዱ በዛሬው ዕለት በ2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በመግባት ቀዳሚ ሆኗል። የ21 አመቱ ወጣት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት ውድድር ከቦታው ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ሶስት ደቂቃ ብቻ ዘግይቶ ገብቷል። ሌላው ኢትዮጵያዊ አየለ አብሽሮ በ02:08:27 እንዲሁም የዩጋንዳው ስቴፈን ኪፕሮች በ02:08:32 ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።በሴቶች ጎራ በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ድባቤ ኩማ አሸናፊ ሆናለች። ድባቤ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2:24:42 ፈጅቶባታል። የኬንያዋ ማግዳሊን ማሳይ እና የታንዛኒያዋ ፋይሉና ማታንጋ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። በዛሬው ዕለት በለንደን በተካሔደው የማራቶን ውድድር ኬንያዊው ኡልዩድ ኪፕቾጌ በወንዶች ጎራ አሸናፊ ሆኗል። ኢትዮጵያውያኑ ሞስነት ገረመው እና ሙሌ ዋሲሁን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።ከአትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የከረመው ሞ ፋራሕ ውድድሩን አምስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በለንደን ማራቶን የሴቶች ውድድር ኬንያውያኑ ብሪጅድ ኮስጌይ እና ቪቪያን ቼሪዮት አንደኛ እና ሁለተኛ ሲወጡ ኢትዮጵያዊቷ ሮዛ ደረጄ ሶስተኛ ሆና ጨርሳለች።

source DW, FBC

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0
Read previous post:
Ethiopia, China´s Companies Sign Memorandums of Understanding

Addis Ababa, Apr 27 (Prensa Latina) The Ethiopia Investment Commission signed memorandums of understanding with...

Close