ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

አዎ…ቴድሮስ ፀጋዬ የኢትዮጵያዊነትን ለምድ የለበሰ የህወሓት ተኩላ ነው!!

በስዩም ተሾመ – ከኢሳቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በፊት የማውቀው ቴድሮስ ጸጋዬን ነው። ለመጀመሪያ ግዜ በሚዲያ አስተያየት ሲሰጥ የሰማሁት በራዲዮ ፋና ነው። የስንተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ እንደሆነ አላስታውስም። ነገር ግን ለእረፍት ወደ አስላ ሄጄ ሳለሁ አንድ ቀን ቴድሮስ ፀጋየ የተባለ አንደበተ-ርዕቱ የሆነ ልጅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስድስት ኪሎ ካምፓስ ተማሪ በራዲዩ ፋና ቀጥታ የስልክ መስመር ገብቶ በነፃነት አስተያየት ሲሰጥ ሰማሁት። በዚያን ወቅት ሃሳብና አስተያየትን በዚያ ልከ በነፃነት መስጠት የሚችሉት በጣም ጥቂት ግለሰቦች ነበሩ። ለምሳሌ ጥቀስ ካላችሁኝ እንደ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በድፍረት የተሞላ ወይም ደግሞ እንደ አቦይ ስብሃት ነጋ በማንአለብኝነት፥ እንደ ደራሲ ስብሃት ገብረእግዜያብሔር በጥልቅ ዕውቀት የተሞላ፤ እንደ የኢቲቪው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በባዶነት የደነዘዘ ወይም እንደ ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የናወዘ፣… በአጠቃላይ በዚያን ወቅት ያሰቡትን የመናገር ነፃነት የነበራቸው፤ ወይ ለህወሓት ባለስልጣናት ያሸረገዱ አሊያም በራሳቸው ህይወት የፈረዱ ብቻ ነበሩ።

ነገር ግን ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ቴድሮስ ፀጋዬ ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ያለ ከልካይ ወይም ሃይ-ባይ የፈለገውን ሃሳብና አስተያየት መስጠት ይችል ነበር። በወቅቱ እኔ እንደ እሱ ራዲዮ ጣቢያ ላይ ቀርቤ በነፃነት አስተያየት ለመስጠት ወይ ለመሞት ወይም ለመታሰር መቁረጥ አለብኝ አሊያም የህወሓት/ኢህአዴግ አባል መሆን አለብኝ። የህወሓት/ኢህአዴግ አባል ካልሆንኩ ወይም ለሞትና መታሰር ካልወሰንኩ በስተቀር እንደ ቴድሮስ ፀጋዬ በነፃነት መናገርና መተቸት በራስ ላይ አጎብዳጅነትና ታዛዥነት ወይም ሞትና እስራት እንደ መጥራት ነው። በአጠቃላይ እንደ ቴድሮስ ፀጋዬ ሃሰብና አመለካከትን መግለፅ የቢሆን-አለም ቅዠት ነው። ለቴድሮስ ፀጋዬ ግን በእውን የተረጋገጠ ነገር ነው። ቴድሮስ ፀጋዬ ገና ተማሪ እያለ የፈለገውን ነገር መናገር ይችላል፣ በፈለገው የሚዲያ አውታር ላይ ቀርቦ ሃሳብና አስተያየት ይሰጣል። እንደ እኔ ያለው ግን የቴድሮስን ንግግር ሳያላምጡ ከመዋጥ በስተቀር ምንም ዓይነት የተለየ ሃሳብና አስተያየት መስጠት እንደ እስክንድር ነጋ እና አንዱአለም አራጌ ለእስራት፣ እንደ ሲሳይ አጌና እና ታምራት ነገራ ለስደት ይዳርጋል። የሆነው ሁሉ ሆኖ ቴድሮስ ፀጋዬ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ግዜ የመታሰር ስጋት ተሰምቶት ያውቃል? ወይም ደግሞ ሀገር ጥሎ መሰደድ ግድ ሆኖበት ያውቃል? አያውቅም!!! ለምን?

1ኛ) የመጀመሪያው ነገር ቴድሮስ ፀጋዬ ትግሬ ወይም ትግራዋይ መሆኑ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ በዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ እንደ ቴድሮስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ብርሃኔ፣ ዳዊት ከበደ፣ ሰናይት መብራቱ፣ ብርሃኔ ንጉሴ፣… ወዘተ የትግራይ ተወላጅ መሆን ልክ በአፓርታይድ ዘመነ-መንግስት እንደነበሩት የደቡብ አፍሪካ ነጮች የተሻለ መብትና ጥቅም ለማግኘት የሚያስችል በአጋጣሚ የተገኘ የተፈጥሮ ገፀ-በረከት ነበረ።

2ኛ) በእርግጥ ህወሓት/ኢህአዴግ እሱ መስማትና መናገር ከሚሻው ሃሳብና አስተያየት ውጪ የምታስብና የምትናገር ከሆነ ይቅርታና ምህረት የለውም። በተለይ ህወሓት ከእሱ የተለየ ሃሰብና አስተያየት ያላቸው የትግራይ ተወላጆችን ከየትኛውም ብሔር በተለየ በዓይነ-ቁራኛ የመመልከት አባዜ አንዳለው ይታወቃል። ለምሳሌ በአብርሃ ደስታ ላይ የደረሰው እስራትና እንግልት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። ቴድሮስ ፀጋዬ በፈለገው ጉዳይ ላይ የመሰለውን ሃሳብና አስተያየት ሲሰጥ አንድም ቀን ከህወሓት የደህንነት ሰራተኞች ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶበት አያውቅም። ምክንያቱም የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የማይፈልጉትን ነገር በፍፁም ተናግሮና ፅፎ አያውቅም።

3ኛ) በዚህ ሀገር በስፋት እየተቀነቀነ ላለው የብሔር/ዘውግ ፖለቲካ አድራጊና ፈጣሪው ህወሓት መሆኑ እሙን ነው። ይህ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ከብሔሮች እኩልነትና መብት ይልቅ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ስሪት በማፍረስ፤ ከአንድነት በላይ ልዩነትን በማስረፅ፥ ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን በመስበክ፥ ማስረፅ፥ ማስፋትና ማስፋፋት ላይ የተመሰረተ ነው። ኢትዮጵያዊ አንድነትና አብሮነትን የሚያቀነቅን ማንኛውም ወገን ከህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ጋር ድጋፍ ስምምነት ሊኖረው አይችልም። ቴድሮስ ፀጋዬ ግን በማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ላይ የራሱን ሃሳብና አስተያየት መስጠት ከጀመረበት ከ2011 እስከ 2017 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ድረስ ኢትዮጵያዊነትን በሚያወድስበት አንደበቱ አንድም ቀን ተሳስቶ የኢትዮጵያዊነት ፀር የሆነውን ህወሓት ስምና ምግባር ጠቅሶ አያውቅም። ከአመሰራረቱ እስከ ውድቀቱ ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስና ለማፈራረስ ሲተጋ የነበረውን ህወሓት ሳይጠሩ ስለ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ሊመሰክሩ ይችላሉን?

የኢትዮጵያ አንድነትን የሚሰብከው ድምፃዊ ፀሓዬ ዮሃንስ ከአባይ ፀሓዬ ጋር ወይም የጋራ አብሮነትን አጉልቶ የፃፋው ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚያብሔር ከአቦይ ስብሃት ነጋ ጋር ተቀራራቢ የሆነ አቋምና አመለካከት የላቸውም፣ ፈፅሞ ሊኖራቸው አይችልም። ጋሽ ስብሃት በሀገሩ በክብር ያረፈው ከህወሓቶች በላይ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ስለገዘፈ ነው። ድምፃዊ ፀሓዬ ዮሃንስ ስለ ኢትዮጵያ ያዜማቸው ዘፈኖች ከህወሓቶች በፊት በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ የታተሙ ነበሩ። በአጠቃላይ እንደ ፀሓዬ እና ጋሽ ስብሃት ያሉ ሰዎች በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ከህወሓት በፊት ያሉና ከህወሓት በኋላም የሚኖሩ ናቸው። ቴድሮስ ፀጋዬ ግን የህወሓት/ኢህአዴግ ጭቆና እየበረታ በሄደበት ወቅት በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ዘንድ እውቅና እያገኘ፣ በደልና ጭቆናው እየባሰ ሲሄድ ደግሞ በዚያው ልክ በስነ-ፅሁፍና ሙዚቃ ላይ የሚሰጣቸው ትችቶች ይበልጥ እየጨመሩና ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ ሄዱ። በመጨረሻ ህወሓት ከአዲስ አበባ ሲባረር ቴድሮስ ፀጋዬ የፖለቲካ ተንታኝና የመብት ተሟጋች ሆኖ ብቅ አለ። በእርግጥ እንደ እኔ ያሉ ሰዎች ከስንት አንዴ በስህተት ስለ ህወሓቶች አዎንታዊ ነገር ሊናገሩ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን እንደ ቴድሮስ ፀጋዬ ያለ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን ሰው እንዴት አንዴ እንኳን ተሳስቶ ስለ ህወሓት አሉታዊ ሃሳብና አስተያየት አይሰጥም??? የኢትዮጵያን አንድነት ለመታደግ የሚተጋ ሰው እንዴት ሆኖ ከመነሻ እስከ መድረሻው ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ስም ጠቅሶ እኩይ ምግባሩን በይፋ መናገር ይሳነዋል?

በመሰረቱ እንደ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ያሉ ሰዎች በኢትዮጵያዊነት እና ህወሓት ላይ ሙጭጭ ያሉበት ምክንያት አንዱ አጥፊ. ሌላው ጠፊ ስለሆነ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የህወሓት ዘረኛ አቋምና አመለካከት እስካለ ድረስ ሁሌም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት አደጋ ላይ ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሲለመልም የህወሓት ዘረኛ አቋምና አመለካከት ከስሩ ተነቅሎ ይወድቃል። የህወሓት የበላይነት እስካለ ድረስ ግን ምርጫው፤ የህወሓት ብሔርተኝነት ወይም የኢትዮጵያ አንድነት ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን አንድነት የሚሹ በሙሉ ህወሓትንና የእሱ ስሪት የሆነውን የዘውግ ብሔርተኝነት አለመውቀስ አይችሉም። በሌላ በኩል የብሔር ፖለቲካና ብሔርተኝነትን ማስቀጠል የሚሹ ከሆነ ደግሞ የህወሓትን ስምና ምግባር ጠቅሶ አለማወደስ አይቻልም። እንደ ቴድሮስ ፀጋዬ ያሉ ሰዎች ግን፤ ኢትዮጵያዊነትን ሲያወድሱ ተሳስተው እንኳን የህወሓትን እኩይ ምግባር አይጠቅሱም። የዘውግ ብሔርተኝነት የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያነሱ ደግሞ በዚህ ረገድ ህወሓት የነበረውን ድርሻና ሚና በግልፅ አይጠቅሱም። ቴድሮስ ፀጋዬ “የህወሓት ቡችላ ነው” የምለው ለዚህ ነው። ህወሓት በእነ ዳንኤል ብርሃኔ በኩል ሲያቀነቅነው የነበረው ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ሳይሳካ ሲቀር ቴድሮስ ፀጋዬ የተባለውን ተኩላ የኢትዮጵያዊነት ለምድ አልብሶ ልኮታል። እውነታው ይኼው ነው!!!

ይህ ዛሬ በድንገት የተገለጠልኝ እውነት አይደለም! ባለፈው ከሲሳይ አጌና ጋር ያደረኩትን ቃለ ምልልስ ተከትሎ በርዕዮት ሚዲያ ላይ ባቀረበው ዝግጅት ሆነ በስልክ ደውሎ ሲሰድበኝ እውነታው ሳይገለጥልኝ ቀርቶ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ቴድሮስ በራሱ ማሰብና ማስተዋል ቢሳነው ስህተቱን አይቶ የሚመክረው አይጠፋም በሚል እምነት ነው። እሱ ግን ስህተቱን አውቆ ዝም አላለም ወይም መካሪ የለውም። በመሆኑም በእውን የሆነውና እያደረገ ያለው እኩይ ምግባር በይፋ መነገርና መታወቅ ስላለበት ብቻ በዚህ መልኩ ለመፃፍ ተገድጄያለሁ። ይህን ስል ‘እኔ ከስህተት የፀዳሁ ፍፁም ሰው ነኝ’ እያልኩ አይደለም። ነገር ግን በህይወቴ አንድም ቀን ቢሆን የህወሓትን ዘረኛነት እና እኩይ ዓላማ ለማስፈፀም ለይምሰል ኢትዮጵያዊነትን አቀንቅኜ አላውቅም። ሳለውቅ ተሳስቼ ማድረግ የሌለብኝን አድርጌ ወይም በስሜት ተገፋፍቼ ማለት የሌለብኝ ብዬ አውቃለሁ። ነገር ግን ለአንዲት ሰኮንድ እንኳን አውቄና ፈቅጂ በኢትዮጵያና ህዝቧ ላይ ክፋት አስቤ ሆነ አድርጌ አላውቅም። እስካሁን ድረስ በጥሞና ለማጤን እንደሞከርኩት ቴድሮስ ፀጋዬ ማለት በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግድ፣ ለህወሓትና ለራሱ ጥቅም ሲል ሀገርና ህዝብን አሳልፎ የሚሸጥ ይሁዳ ነው። አዎ… ቴድሮስ ፀጋዬ የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ ነው። ቴድሮስ ፀጋዬ በእኔና ሲሳይ አጌና ላይ የከፈተውን ዘመቻ ሁለተኛ ክፍል ይህን ሊንክ በመጫን መመልከት ይቻላል፦https://youtu.be/ckZ1Nmy3Zdo 

ዝግጀት ክፍሉ – የጽሁፉ ባለቤት አቶ ስዩም ተሾመ ራሱ ቴዎድሮስ የተናገረውን በማጥመድ እንድታመጣጥኑት ማስፈንጠሪያውን አስቀምጧል። በመሆኑም ጽሁፉ የሚዛናዊነት ጥያቄ አይነሳበትምና አትመነዋል