“Our true nationality is mankind.”H.G.

‹‹ካለፈው ተምረናል፤ ይቅር ተባብለናል፤ ይቅርታና ምሕረትንም አውርደናል››

‹‹እውነተኛው የሀገራችን ጀግኖች መጠሪያ ‹ፋኖ› ዛሬም ካለ ለአማራ እና ቅማንት ሕዝቦች ከልብ የሆነ እርቀ ሠላም ሊሳተፉ ይገባል፡፡›› ተሳታፊዎች

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2011ዓ.ም (አብመድ) የአማራ እና ቅማንት ሕዝቦች ዘላቂ እርቀ ሠላም እንዲፈጠር የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ከአንድ ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በጎንደር ከተማ ምክክር ተካሂዷል፡፡

በምክክሩ የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ‹‹እንኳን ከራሳችን ጋር የጠፉ ጠላቶቻችንም ይናፍቁናል፤ ጎንደር እንኳን ከራሳችን ጋር መታረቅ በሀገሬው አዲስ ሰው ሲነካ እንኳ ‹ምነው የሰው ሀገር ነው ብለህ ነው› ብሎ ‹መከታ› የሚሆን ነው›› ያሉት፡፡ 
በተልዕኮ እና በገንዘብ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋት የለበትም ያሉት ሐሳብ ሰጭዎቹ ‹‹እውነተኛው የሀገራችን ጀግኖች መጠሪያ ፋኖ ዛሬም ካለ ለአማራ እና ለቅማንት ሕዝቦች ከልብ የሆነ እርቀ ሠላም ሊሳተፉ ይገባል፡፡ ከሕዝቡ በተጨማሪ ችግሩን የጠነሰሱትና ወደፊትም ስጋት የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትም ሊታረቁ ይገባል›› ብለዋል፡፡ 
‹‹አልተጣላንም›› ብቻ ሳይሆን ‹‹ይቅር›› ማለትንም በገቢር ማረጋገጥ የሚጠይቅ ወቅት ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ እውነተኛ እርቀ ሠላም ለማውረድ ከሕዝብ እስከ ግለሰብ መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሠላም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አምባየ ወልዴ እርቀ ሠላሙ የፀና እንዲሆን የተፈፀመውን በደል ማመን እና ኃላፊነት መውሰድ፣ መፀፀትና ይቅርታ መጠየቅ እንዲሁም ይቅርታ የመስጠት ቅን ልቡና እንደሚያፈልግ ገልጸዋል፡፡ ከችግሩ መማርም ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት 33ኛ ዕዝ ኢንዶክትሬሸን ኃላፊ ሜጄር ጀነራል ሙሀመድ ተሰማ ‹‹ያለፉ ቁስሎችን ረስተን ቁስሎችን በሚያክሙ ሥራዎች ላይ ዝግጁ መሆን አለብን፤ መከላከያ ሠላም እንዲረጋገጥ እና እርቁ እንዲሰምር ቀጣይ እስከ መንደር ድረስ በሚዘልቀው ምክክር ድጋፍ ያደርጋል›› ብለዋል፡፡

በተለያዩ ፍላጎቶች በሠላም ማሳጣት የተጠረጠሩ ዜጎች እጃቸውን ለሕግ እንደሚገባና ጥፋተኞች ሆነው ‹እጅ አንሰጥም› ያሉ እና ቤተሰቦቻቸው ሕግ እንዳይከበር ሊያደርጉ እንደማይገባም ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣዕምያለው አሳስበዋል፡፡

የአዴፓ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ‹‹ሰውን ለማጥፋት ካወጣነው ሀብት ይልቅ ለሠላም የምንለው ‹ይቅርታ› ያለድካም ሕይወትን የሚያቆይና የሚያግዝ ኃይል ነው›› ብለዋል፡፡ ‹‹የመንግሥትን ለእኛ የቤት ሥራ ስጡን፤ ካልተወጣነውም ጠይቁን፡፡ እናንተን ግን እውነተኛ እርቀ ሠላምን ማውረድ አለባችሁ›› ብለዋል አቶ ዮሐንስ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ደግሞ ‹‹በሕግ አምላክ ብሎ ራሱ በራሱ ይዞ ‹የፍትሕ ያለህ› ብሎ ከሚመጣ ሕዝብ የወጣ ዜጋ ላለመጠየቅ በጫካ አይኖርም፤ ይህም እንዳትታረቁ ምክንያት ሊሆን አይገባም›› ብለዋል፡፡ 
ሕዝቡ ለነፃነቱና ለሠላሙ ሲል እርቅ ማውረድ እንዳበትና ለህልውናው ዋስትና መሆኑን ማመን እንደሚገባ ዶክተር አምባቸው፡፡ ከግንቦት 01 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩም ዶክተር አምባቸው አሳስበዋል፡፡
ለአብዛኛው ሰላም ወዳድ ሕዝብ ሲባል ሰላምን የማይሹ ሰዎችን ብቻቸውን እንዲቀሩ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በውጭይቱ መጨረሻም በሃይማኖት አባቶች አስፈፃሚነት እርቀ ሠላሙ ወርዷል፤ ይህን መሠል የእርቀ ሠላም ሥነ-ሥርዓት እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ -ከጎንደር – Amhara Mass Media Agency

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤
0Shares
0