“Our true nationality is mankind.”H.G.

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላለፈ መልዕክት

“የመናገር ነጻነት” መንግሥት፣ ፓርቲ ወይም አንድ ሌላ አካል ለፈለገው የሚሰጠው አለያም ላልፈለገው የሚነፍገው ርጥባን አይደለም፡፡ ተፈጥሮ ያጎናጸፈችን መተኪያ የሌለው ታላቁ ስጦታችን፣ ሰው በመሆናችን ብቻ የምናገኘው ጸጋ ቢኖር ያሰብነውን በነጻነት መናገር ነው፡፡ ሰው የፈለገውን ሐሳብ በፈለገው መንገድ ለፈለገው ሰው የማቅረብ መብት አለው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለት ፈርጣማ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች የሚረቱበት እንጂ ፈርጣማ ጡንቻ ስላላቸው ሌላው እንዳይናገር በማፈን ስንኩል ሐሳባቸው እንዲያሸንፍ የሚያደርጉበት ሜዳ አይደለም። በሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲያብብ ብቻ ሳይሆን አሽቶና ጎምርቶ ፍሬውን እንድንበላ ከተፈለገ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከወረቀት ባለፈ በተጨባጭ መሬት ላይ ሳይሸራረፍ ሲተገበር ማየት አለብን። ያለንበት የታሪክ ምዕራፍ ይሄንን እውነታ በምልአት የሚቀበልበት ወቅት ነው። “በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ” የሚባልበት ዘመን አብቅቶ “ካለመናገር ደጃዝማችነት” የሚቀርበት ዘመን ከፊታችን እጁን ዘርግቶ እየጠበቀን ነው። አሁን ኢትዮጵያ በመናገር የሚገኘውን በረከት የምትሻበት እንጂ ለዘመናት እንዳደረገችው ተናጋሪውንም ንግግሩንም ደብዛውን የምታጠፋበት ዘመን ተደምድሞ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በሀገራችን መከበሩ ብቻ ሳይሆን በዚህ ወቅት መከበሩ ለእኛ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የፕሬስ ነጻነትን አታከብርም ተብላ ስትወቀስ በቆየች ሀገር ዓለም አቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን እንዲከበር የተደረገው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የተለወጠ፣ የተሻሻለ ነገር መኖሩን ዓለም መረዳት ጀምሯል ማለት ነው፡፡ መንገዳችን ፈታኝ ቢሆም ልንደርስበት ያሰብነውን ግብ ዓለም ተገንዝቦታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ከመላው ዓለም ተሰባስባችሁ በአዲስ አበባ የተገኛችሁትን የፕሬስ ተዋንያን፣ የፕሬስ ነጻነት አቀንቃኞችና የፕሬስ ነጻነት ተከራካሪዎች ሁሉ በዚህች ሀገር እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በቅርበት ለመረዳት፣ ተረድታችሁም ለማገዝ እንደመጣችሁ እናምናለን፡፡ እናንተ እዚህ በተሰባሰባችሁበት ጊዜ ኢትዮጵያ በሁሉም
ረገድ ለሰው ልጅ ኑሮ ምቹ ሀገር እንድትሆን ለማስቻል እየተረባረብን ነው፡፡ ለዚህም መሰረት የሆነውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ቅድሚያ በመስጠት ባለፈው አንድ ዓመት አያሌ የለውጥ ርምጃዎችን ወስደናል፡፡

Related stories   መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት

● እድሜ ልክና ሞት የተፈረደባቸው የመንግሥት ተቃዋሚዎች ከእሥር ተፈተዋል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞች አሁን የሚገኙት ከእሥር ቤት ውጭ ነው፡፡

● ተዘግተው የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደገና ወደ ኅትመት ብርሃን መጥተዋል፡፡

● ከሀገር ውጭ ሆነው የኖሩ ሚዲያዎች በነጻነት ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡ ከ260 በላይ ተዘግተው የነበሩ ብሎጎችና ገጸ ድሮች ተከፍተዋል፡፡

● በሀገር ውስጥ ነጻነት መታገል ያልቻሉና በመሣሪያ ጭምር ከሀገር ውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ከዐሥር በላይ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡

ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ Ethiopia: A New Horizon of Hope 2

● በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ፍረጃው ተነሥቶላቸው በፖለቲካው ሜዳ እንዲንቀሳቀሱ ተደርገዋል፡፡

● የብዙዎችን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብት በመጫን የሚታወቀው የፀረ ሽብር ሕግ እየተሻሻለ ነው፡፡

● የምርጫ ቦርድንና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ለማሻሻልና ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብቶች መከበር በሚረዳ መልኩ ለማዋቀር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

● የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩበትን የሥነ ምግባር ሕግ አጽቀዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የመዋቅርና የሕግ ማሻሻል ሥራ እየሠራን ነው፡፡

ከዓለም ታሪክ እንደምንረዳው ብልጽግናና ሥልጣኔ ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ በጥንታውያኑ ገናና የግሪክ ከተሞች ሥልጣኔም ሆነ፣ በዛሬዎቹ ሥልጡን ሀገሮች ሐሳብን በነጻነት መግለጽ የዴሞክራሲያቸው ዋልታ፣ የመሠልጠናቸው መሠረት እንደሆነ ለሁሉም ሰው ደምቆ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ሐሳብ በነጻነት በማይገለጽባቸው ሀገሮች ብልጽግና የለም፡፡ በአንፃሩ ልማትና ብልጽግናን በተጎናጸፉ ሀገራት ውስጥ ነጻ ፕሬስና በነጻነት ሐሳብን የመግለጽ መብት በተግባር ተረጋግጦ ይገኛል፡፡

Related stories   ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማጣራቱ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን እንደሚያካትት አስታወቀ፤ መንግስትና አማራ ክልል በማይካድራ ጉዳይ ተኝተዋል

እናንተ ወደ አዲስ አበባ የመጣችሁበት ወቅት ሀገራችንን ወደፊት ለማስኬድና ወደኋላ ለማስቅረት ትግል በሚደረግበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ የምትሰሟቸው ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ ውጥረቶችና እንካ ሰላንትያዎች ወደኋላ ለመቅረት ወይም ባሉበት ለመቸከል በሚፈልጉ ሐሳቦችና ኃይሎች የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች የለውጡን ጉዞ ፈታኝ፣ ከባድና መራራ ያደርጉት ይሆናል እንጂ አያስቀሩትም፡፡ ያለፈው አንድ ዓመት እንደተጓዝን ሁሉ ቀጣዮቹን ሺህ ዓመታትም እንጓዛለን፡፡ እናንተም የዚህ ታሪክ ምስክሮች ትሆናላችሁ፡፡

ለእኛ የፕሬስ ነጻነት ማለት የጋዜጠኞች ነጻነት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የሁላችንም ነጻነት ጭምር ነው፡፡ ፕሬስ የሁላችንንም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ማሳለጫ መንገድ ነው፡፡ ለፕሬስ ነጻነት የምናደርገው ትግል ለጋዜጠኞች መብት ስንል የምናደርገው ሳይሆን ለራሳችን መብት ስንል የምናደርገው ትግል ነው፡፡ የፕሬስ ነጻነትም የራሳችን ነጻነት ነው፡፡ ባለፉት ወራት በዋጋ ጭማሪ ምክንያት የጋዜጣ ወረቀት ከ70 በመቶ በላይ ጨምሯል፤ መንግሥት ግን ይሄ ጭማሪ በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ እንዲጨመር አልፈቀደም፡፡ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ጭማሪ ራሱ መንግሥት ድጎማ አደርጎ ተሸክሞታል፡፡ ይህንን ያደረግነው የፕሬስ መብት የኛም መብት ስለሆነ ነው፡፡ የሠለጠነና የዘመነ ማኅበረሰብ
እንዲኖረን የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ስንልም መብቱን የሚያስከብር፣ ኃላፊነቱንም የሚወጣ ማለታችን ነው፡፡ መብት የሌለው ኃላፊነት ባርነት ነው፤ ኃላፊነት የሌለው መብትም ልቅነት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ባርነትንም ሆነ ልቅነትን አንፈልጋቸውም፡፡

መንግሥት የፕሬስ ነጻነት መብት በሚገባ እንዲከበር ብዙ ሥራዎች ቢሠራም ሌሎች ብዙ ሥራዎች ደግሞ ይቀሩታል፡፡ የሚዲያዎችን ዐቅም ለማሳደግ፣ የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ዕድሎችን ለማመቻቸት፣ የተሻለ ሥራ የሚሠሩትን የሚያበረታታበት መንገድ ለመፍጠር፣ ለሚዲያ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን የቀረጥ ዋጋ ለመቀነስ፣ መረጃ ለማግኘት ያለውን ፈተና ለመቀነስ፣ የሚዲያ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ ሚዲያዎቻችን አካባቢያዊ ወይም ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ቁመና እንዲኖራቸው ለማድረግ ብዙ መሥራት እንዳለብን ተረድተናል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ሚናውን  ተገቢው መንገድ ለመወጣት የሚችልበትን ሕግና አሠራር መዘርጋት እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ እነዚህን ለማከናወን የሚያስችል የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎችን እያደረግን ነው፡፡ አንዳንዶቹም በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡

Related stories   “…ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ” አብይ አህመድ

በዚሁ ተነጻጻሪ ፕሬሶቻችን መብትና ኃላፊነትን አጣምሮ በሚይዝ መልኩ እንዲጓዙ እንፈልጋለን፡፡ አራተኛው መንግሥት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም መንግሥት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በሽግግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብን ለማገዝና ለማሻገር የሚያስችል የሚዲያ ከባቢያዊ ሁኔታ ያስፈልገናል፡፡ ከግጭት ቀስቃሽነት፣ ከጠብ ጫሪነት፣ ከአሉታ አነፍናፊነትና ከስሜታዊነት የወጣ ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ ሞያዊ ብቃቱን የጠበቀ፣ የሞራል ልዕልና ያለው፣ የሚሠራው ሥራ የሚያስከትለውን ውጤት ቀድሞ ለመገመት የሚችል ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ በተለይም በቀጣዩ ዓመት ከሚኖረን ምርጫ ጋር ተያይዞ በእውነት፣ በዕውቀትና በሚዛናዊነት የሚሠራ ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡

ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ Ethiopia: A New Horizon of Hope 3

በፕሬስ ነጻነትና ዕድገት ላይ የሚሠሩ አካባቢያዊ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደግፉን በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ የፕሬስ ተቋሞቻችን ሞያዊና ቴክኖሎጂያዊ ዐቅም እንዲጎለብት፣ ዕውቀትና ሥነ ምግባር ያለው ፕሬስ እንዲኖረን፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው ጋዜጠኞች እንድናፈራ፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶቻችን ሁለንተናዊ ዐቅም እንዲዳብር፣ የፕሬስ ማኅበራት እንዲጠናከሩ እዚህ የተሰበሰባችሁትን የሁላችሁንም ድጋፍ እንሻለን፡፡ በዚህ ረገድ ሊያግዙን ከሚመጡ ጋር ሁሉ ለመሥራት መንግሥታችን ዝግጁ መሆኑንም ልንገልጥላችሁ እንወዳለን፡፡

መልካም ‹የፕሬስ ነፃነት ቀን› ይሁንልን! ይሁንላችሁ፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና ሕብረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ሚያዚያ 25፣ 2011 ዓ.ም

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0