“Our true nationality is mankind.”H.G.

የቤተ እስራኤላውያን ልዑክ ለስሜን ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ልማት እንደሚሠራ አስታወቀ፤

በአምባሳደር በላይነሽ ዛቫድያ የተመራው የቤተ እስራኤላውያን ልዑክ ለስሜን ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ልማት እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡የቤተ እስራኤላውያን ልዑክ ለስሜን ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ልማት እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2011ዓ.ም (አብመድ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በእሳት አደጋ የደረሰበትን ጉዳት ለማዬትና በቀጣይ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለመለየት በአምባሳደር በላይነሽ ዛቫድያ የሚመራ ልዑክ ከሰሞኑ ወደ ስፍራው ማቅናቱ የሚታወስ ነው፡፡ ልዑኩ የፓርኩን የጉዳት ሁኔታ ተመልክቶና ከአካባቢው ማኅበረሰብና አመራር ጋር ተወያይቶ ወደ ባሕር ዳር ተመልሷል፡፡

በባሕር ዳር ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ማድረጉም ታውቋል፡፡ የልዑካን ቡድኑን የሚመሩት አምባሳደር በላይነሽ ዛቫድያ ‹‹በፓርኩ እሳት መነሳቱን ስንሰማ በጣም አዝነናል፤ ፓርኩ በርካታ ብዝኃ ሕይወት ያለበትና ከዓለም ትልልቅ ፓርኮች አንዱ የሆነ ሀብታችን ነው፡፡ አሁን ያጋጠመው አደጋ ቢወገድም ለወደፊት እንዴት መጠበቅ እንዳለበትና እንዲያገግም ምን መሥራት እንደሚያስፈልግ ለመለዬት የሚያስችል ግብዓት ለመውሰድ መጥተናል›› ብለዋል፤ የሚፈልጉትን ያህል መረጃ ማግኘታቸውንና ወደ እስራኤል ተመልሰው ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚመክሩበትም አስታውቀዋል፡፡

የልዑካን ቡድ አባላት የተለያዬ የሙያ ስብጥር ያላቸውና ለዘላቂ ድጋፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት አምስት ናቸው፤ ከእነዚህም ውስጥ ዲፕሎማት፣ የደን ባለሙያ፣ የታሪክ ተመራማሪ እና አውሮፕላን አብራሪ ይገኙበታል፡፡

ልዑካኑ በደባርቅና ጎንደር ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል፤ በተለይ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በእሳት አደጋ መከላከል ዙሪያ ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት ፈር ቀዳጅ ሆኖ ሐሳቡን መቀበሉ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑን በባሕር ዳር ያነጋገሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደን ነው፡፡ ‹‹ቤተ እስራኤላውያኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻን መሆናቸውን እናውቃለን፤ ያውቃሉ፡፡ አሁን ደግሞ በችግራችን ጊዜ ደርሰው ትክክለኛ የቁርጥ ቀን ወዳጆቻችን መሆናቸውን አሳይተውናል፡፡ ወደፊት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ግንኙነታችንን የምናጠናክርበትና ከእስራኤል በርካታ ልምዶችን የምንቀስምበትን ሁኔታ እናመቻቻለን›› ብለዋል፡፡

እስራኤላውያን አነስተኛ የተፈጥሮ ፀጋን ለላቀ ጥቅም የማዋል ጥበብ እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ምግባሩ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በስፋት ለመሥራት የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ቤተ እስራኤላውያኑ አብዛኞቹ የተወለዱት ኢትዮጵያ ነው፤ አንዳንዶቹ እስራኤል የተወለዱም እንኳን ቢሆኑ ወላጆቻቸውና አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከኢትዮጵያ ናቸው፤ ስለዚህ ሀገራችን ሀገራቸው ናት፡፡ የፀሎት ቦታዎቻቸው፣ መካነ መቃብሮቻቸው፣ ባድማዎቻቸው … አሁንም በክልላችን ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ መጥተው በክልላችን እንዲያለሙ ጭምር እንፈልጋለን›› ነው ያሉት፡፡
‹‹ከዚያም ሆነው ልባቸው ከዚህ እንደሆነ እናውቅ ነበር፤ በችግራችን ጊዜ ደርሰውም ይህንን አረጋግጠውልናል፡፡ ስላደረጉልን እገዛ በክልሉ መንግሥት ስም ቤተ እስራኤላውያንና መላው እስራኤላውያንን እናመሠግናለን›› ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውም በሁለት ዙር የመጡትን የልዑካን ቡድን አመሥግነዋል፡፡ እስራኤላውያን ሰደድ እሳትን በመቆጣጠር ያላቸውን ልምድ መሠረት አድርጎ የኢፌዴሪ መንግሥት ሲጠይቅ የእስራኤል መንግሥት ፈጣን ምላሽ መስጠቱን አድንቀው ‹‹ቤተ እስራኤላውያኑ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አደጋውን ለመጋፈጥና አሁንም አካባቢው እንዲያገግም አስተዋጽኦ ለማድረግ መምጣታቸው እጅግ የሚያስመሰግን፤ ከትክክለኛ እህትና ወንድም ደግሞ የሚጠበቅ ነው›› ብለዋል፡፡

በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራትና በተለይ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ከቤተ እስራኤላውያኑ ልምድ እንደሚወሰድም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት –

Amhara Mass Media Agency

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”
0Shares
0