“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለሕገ መንግሥት ሕልውና የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሚና

ሌላው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እያስፈለገ ነገር ግን ሳይደረግ የተፈጸመውንም ቢያንስ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ ጥሩ ማሳያው የድሬዳዋ አስተዳደር አፈጣጠር ነው፡፡ ድሬዳዋን ፖለቲካዊ ጭንቀት የወለዳት መስተዳድር ናት ማለት ይቻላል፡፡ አግጥጦ መጥቶ የነበረውን ችግር ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ድሬዳዋ ትፈጠር ቢባል ኖሮ ምናልባት የኦሮሚያም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል ምክር ቤቶች በዚያን ወቅት ሊስማሙ ይችል ነበር ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር፡፡ VIA- Reporter

በውብሸት ሙላት

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፀደቀበትን 23ኛ ዓመት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማክበር በአፋር ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በሰመራ ባለፈው ዓርብ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በ1987 በኅዳር ወር ፀድቆ በዚያው ዓመት በነሐሴ ወር ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ጀምሮ ላለፉት 23 ዓመታት በኦፊሴል የተደረገበት ማሻሻያ የለም፡፡ እስካሁን ድረስ አለመሻሻሉ አንድም ማሻሻያ የሚፈልግ ጉዳይ አልገጠመም ከሚል ድምዳሜ ላይ ሊያደርሰን የሚችል ሲሆን፣ አንድም መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የማሻሻል ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት አልፈለጉም፣ አልፈቀዱም የሚል መደምደሚያ ላይ ሊያደርሰን ይችላል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ግን ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትከተለው የምርጫ ሥርዓት ይቀየር ዘንድ ገዥው ፓርቲ ይሁንታ በመለገሱ ምክንያት ወደ ቅይጥ ትይዩ ለመቀየር የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር የግድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር ሲባል ከሕገ መንግሥቱ ላይ አንዲት ንዑስ አንቀጽ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ይህ  በኦፊሴል የሚደረግ የመጀመርያው ማሻሻያ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለሕገ መንግሥት ማሻሻል (Amendment) ጉዳይ ሲነሳ ቁም ነገሩን በአጭር አነጋገር ሲቀመጥ ሕገ መንግሥት ላይ ማስተካከያ የሚደረግበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ማሻሻያ ከጥቅል ክለሳ (Revision) ይለያል፡፡ በክለሳ ሲሆን፣ በርካታ አንቀጾች፣ መሠረታዊ መገለጫዎች ሁሉ ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ የ1948ቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በ1923ቱ ሕገ መንግሥትን ያሻሻለ ሳይሆን የከለሰ ነው፡፡

ማሻሻያ ሲባል በአብዮትም ይሁን በሌላ መንገድ ሕገ መንግሥት ከመለወጥም ይለያል፡፡ የ1948ቱ ሕገ መንግሥት በአብዮት ቀሪ ከተደረገ በኋላ በ1979 ዓ.ም. የወጣው የደርግ ሕገ መንግሥት የቀድሞውን በመከለስ የወጣ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነው፡፡ መንግሥታዊ አወቃቀሩ፣ ሥልጣን የሚገኝበት ሥልቱ፣ የዜጎችና የመንግሥት ግንኙነቱ ሙሉ በመሉ ተቀይሯል፡፡ የደርግ አገዛዝ ከወደቀ በኋላም የመጣው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በቀድሞው ላይ ክለሳ በማድረግ የተገኘ ሳይሆን እንደ አዲስ የተዘጋጀ ነው፡፡

መሻሻል በአንድ የሕገ መንግሥት ሰነድ ውስጥ የሚደረግ የለውጥ ዕርምጃ ወይም ዕድገት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ማሻሻያ የሕገ መንግሥቱን ቃላት፣ ሐረግ፣ ዓረፍተ ነገር ወይም አንቀጾችን ላይ የሚደረግን መጠነኛ ለውጥ ሊያጠቃልል ይችላል፡፡

ከላይ የተገለጹት ሲሻሻሉ በምትካቸው የሚፈጸመው ነገር  በከፊል መጨመር፣ በከፊል መቀነስ ወይም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ሊሆን ይችላል፡፡  በእዚህ መንገድ የሚደረጉ ማናቸውም ለውጦች ከሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ባህሪና ዓላማ፣ ግብና መንፈስ ጋር በሚጣጣም፣ በሚስማማና አብሮ በሚሄድ መልኩ እንጂ ከእዚህ በተቃርኖ ሊሆን አይችልም፡፡ በተቃራኒው ሲሆን ውጤቱ ከማሻሻያነት ያልፋል፡፡ ክለሳ ወይም ለውጥ ሊሆን ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ የማድረግ ሒደት ሕገ መንግሥቱ ሕይወት ኖሮት ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ፣ በአጭር ጊዜ እንዳይሞት፣ በሌላም እንዳይተካ ያደርገዋል፡፡ አንድን ሕገ መንግሥት በወቅቱ እንደ ሁኔታዎች ፍላጎት ማስተካከያና ማሻሻያ ሳያደርጉ መቆየት ወደ ክለሳና ሙሉ በሙሉ ቅያሬ ወደ ማድረጉ ማምራቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡

የ1923ቱ ሕገ መንግሥት በወቅት በወቅቱ ባለመሻሻሉ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማክተሚያን ተከትሎ የመጡ ለውጦችን እንዲሁም የኤርትራን በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀልን ተከትሎ በአገሪቱ የተፈጠረው ሁኔታ ማስተናገድ ስላልቻለ በ1948 ተከለሰ፡፡ ከዚያም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው በፍጥነት ሲቀያየር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ባለበት ተቸንክሮ ቆሞቀር በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ፡፡

የ1966ቱ ተጨናግፎ የቀረው ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ የ1948ቱን እንዲተካ የታሰበው እጅግ ዘግይቶ የመጣ ስለነበር መፅደቅ እንኳን ሳይችል ቀረ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም በአዋጅ ወይም በይፋ ተሻሻሎ አያውቅም፡፡ ‹‹በሚስጥር›› ግን ሁለት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡

በመሆኑም አንድን ሕገ መንግሥት እንደ ሁኔታው በወቅት በወቅቱ ማሻሻል ተገቢ ነው፡፡ በክለሳም በለውጥም ሕገ መንግሥት ሲለወጥ የአገር አስተዳደርና ተቋማት ከእንደገና በአዲስ መልክ ማዋቀርን ስለሚያስከትል ብዙ የሥርዓት መናወጦችን ያመጣል፡፡ የተናወጡትን ሥርዓቶች እንደ አዲስ በማዋቀርና በማቋቋም የአገር ውድ ሀብትና ጊዜ ወዘተ. ይባክናል፡፡   

ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ምክንያት የሚሆነው ጊዜ በሄደና ነገሮች በተቀየሩ ቁጥር ሁለንተናዊ በሚባል መልኩ የዕድገት ደረጃ ስለሚቀየር ነው፡፡  ሁኔታዎች ሲቀየሩ፣ ችግሮች ሲከሰቱ እነሱን ተከትሎ ካልተሻሻለ ሕገ መንግሥቱ ጊዜው የሚዋጀውን አልሆነም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ዓይነት ሕግም ይሁን ሕገ መንግሥት አብረው ከኅብረተሰብ ዕድገትና ፍላጎት ጋር በመሳነት ማደግና መሻሻል ይገባቸዋል፡፡  እናም ሕገ መንግሥት ዘላቂነት ኖሮት ገዥ፣ ህልውና ቅቡልነት ኖሮት ይቀጥል ዘንድ መሻሻል የግድ ይሆንበታል፡፡

አንድ ሕገ መንግሥት ሲዘጋጅ ራሱን የቻለ ሒደት እንዳለው ሁሉ በማሻሻሉም ወቅት መከተል የሚገባቸው ሥርዓቶች አሉት፡፡ የማሻሻያ ሐሳብ ማመንጨት፣ በመቀጠልም በቀረበው ሐሳብ ውይይት ማድረግ፣ ከውይይቱ በኋላ ደግሞ ሥልጣን ባለው አካል ዘንድ ተቀባይ እንዲሆኑ ማድረግና በመጨረሻም ማፅደቅ ናቸው፡፡

የተለያዩ ሕገ መንግሥቶች የሚሻሻሉባቸው ማሻሻያ ባህሪያት የተለያዩ ስለሚሆኑ የሕገ መንግሥት ዓይነትም ለመለየት ይረዳሉ፡፡ አንድ ሕገ መንግሥት ‹ግትር› ወይም ‹ተጣጣፊ› በማለት ለመፈረጅ የማሻሻያ ሒደቱን በማጤን ይታወቃል፡፡ ማለትም ሕገ መንግሥቱ በቀላሉ የሚሻሻል ከሆነ ‹ተጣጣፊ› ነው ማለት የሚቻል ሲሆን፣ በቀላሉ የማይሻሻል ከሆነ ‹ግትር› ሕገ መንግሥት ይባላል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሚሻሻልበትን ሁኔታ እንመልከት፡፡ የማሻሻያ ሐሳብ የማመንጨት ሒደት ምን እንደሚመስል በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 104 ሥር በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የማሻሻያ ሐሳብ በሦስት አካላት ሊቀርብ ይችላል፡፡ የመጀመርያም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሆን፣ በዚህ ተቋም የሚመነጭ ወይም በእዚህ በኩል የሚመጣ የማሻሻያ ሐሳብ ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ የሁለት ሦስተኛውን ይሁንታ ማግኘት ያስፈልገዋል፡፡

ሁለተኛው የማሻሻያ ሐሳብ የማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን፣ በዚህም ጊዜ ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ የሁለት ሦስተኛውን ድምፅ ድጋፍ ማግኘትን ይጠይቃል፡፡

በሦስተኛነት ከዘጠኙ ክልሎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ማለትም አሁን ካሉት ውስጥ ቢያንስ ሦስቱ በአንድነት ሲጠይቁ ነው፡፡ በዚህን ጊዜም የማሻሻያ ሐሳቡን ያነሱት ክልሎች በክልላቸው የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምፅ የማሻሻያውን ሐሳብ የደገፉት ከሆነ ነው፡፡ በእዚህ መንገድ የማሻሻያው ሐሳብ ለውይይትና ለውሳኔ እንዲሁም ለሕዝቡና ጉዳዮች ለሚመለከታቸው ክፍሎች እንደሚቀርብ ተደንግጓል፡፡

ይህ አንቀጽ ቢያንስ ሁለት እንከኖች አሉበት፡፡ አንደኛው የማሻሻያ ሐሳብ ማመንጨት የሚችሉትን አካላት ሦስት ብቻ ማድረጉ ነው፡፡ በእነዚህ ሦስት ተቋማት አማካይነት ካልሆነ በስተቀር በተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌሎች ማኅበራት ወይም ሕዝቡ በራሱ (ቢያንስ ዝቅተኛው ቁጥር ተገልጾ) ማሻሻያ የማቅረብ ዕድል አለመሰጠቱ ነው፡፡

ከእዚህ የሚከፋው ግን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮች ከሌሎች ክልሎችም ጋር ተዳብረው ቢሆንም እንኳን ማሻሻያ የማቅረብ ዕድል መነፈጋቸው ነው፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩልም እንዳያቀርቡ እነዚህን ሁለት መስተዳድሮች ወክሎ የሚገኝ ተመራጭ የላቸውም፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሁለት መስተዳድሮች ምንም እንኳን በብዙ መንገድ እንደ ክልል ቢቆጠሩም በዚህ ግን ያነሱ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ነዋሪዎችም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከማቅረብ እንዲርቁ ተደርገዋል፡፡ ይህ አንዱ እንከን ነው፡፡

ሁለተኛው የዚህ አንቀጽ ችግር የሚስተዋለው ማሻሻያ እንዲደረግበት ከላይ በተገለጸው ሁኔታ የቀረበው ሐሳብ ለውይይት ለሕዝብ እንደሚቀርብ የገለጸበት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የማሻሻያ ሐሳቡ ለሕዝብ እንዲቀርብ መደረጉ ተገቢ ሆኖ ሳለ የሚቀርብበት ሁኔታና ሕዝቡ ተወያይቶበታል የሚለውን ለመወሰን ምንም ነገር አለመገለጹ ነው፡፡ ድፍን ብሎ የቀረበ ነው፡፡ በሕዝበ ውሳኔ መልክ የሚቀርብ ይሁን፣ ወይም ለማሳወቅ ያህል የሚቀርብ ነው የሚለው ነገር አይታወቅም፡፡ እንዲሁም ሁሉም የማሻሻያ ሐሳብ ለሕዝብ የሚቀርብ መሆን አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አንድ ቃልን ለመቀየር የሚቀርብ ማሻሻያ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ እንዲወያይ ማድረግ ብዙ ብከነትን ያስከትላል፡፡

ከእዚህ አንፃር ሲታይ ይህ አንቀጽ በራሱ ማሻሻያና ማብራሪያ ያስፈልገዋል፡፡ ማብራሪያው በአዋጅ መልክ የሚወጣ ሊሆንም ይችላል፡፡ የማሻሻያ ሐሳብ ማመንጭት የሚችሉትን ለማስተካከል ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ከሕዝብ ጋር የሚደረገውን ውይይት የሚመለከተውን ቢያንስ በአዋጅ ማብራራት ይጠይቃል፡፡

ከላይ የተገለጸው የማሻሻያ ሐሳብ ማመንጭት ጋር በተገናኘ ሲሆን፣ ማሻሻያ እንዴት እንደሚደረግ ደግሞ ቀጥለን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የፌዴራል ሥርዓቶች ጠቅላላ መርሕን በመከተል የሕገ መንግሥትን መሻሻል በተመለከተ 105 ተደንግጎ ይገኛል።

ሕገ መንግሥቱ የሕገ መንግሥት መሻሻል ሒደትን በሁለት ከፍሎ የሚያይ ሲሆን፤ አንደኛው የሕገ መንግሥት መሻሻል በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ከተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች እንዲሁም ከአንቀጽ 104 ውጭ ያሉት የሚሻሻሉበት ሥርዓት ነው። ይህንን መደበኛ የሕገ መንግሥት ልዩ ማሻሻል ሒደት ማለት ይቻላል።

ሁለተኛው የሕገ መንግሥት መሻሻል ሒደት በምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩትን መብቶችና ነፃነቶችን በሙሉና አንቀጽ 104 የሚሻሻሉበት መንገድ ነው። ይኸኛውን ልዩ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሒደት ማለት ይቻላል፡፡  ልዩ የሕገ መንግሥት መሻሻል ሒደቱ ከመደበኛው የሚለየው ሥርዓቱ የድምፅ ሰጪውን ቁጥር መጨመራቸው  ነው። ይህንንም ያደረገበት ምክንያት መብቶችና ነፃነቶች በቀላሉ እንዳይሸረሸሩ ነው ብሎ መገመት ይቻል ይሆናል። ነገር ግን የሰብዓዊ መብቶችን አወንታዊና በበጎ መንገድም ለማሻሻልም ጭምር ቢፈልግ እንኳን ሒደቱን እንዲሁ አዳጋች ያደርገዋል፡፡

መደበኛ የሕገ መንግሥት መሻሻል ሒደት ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ ማመንጨት ተነስቶ ውሳኔ የሚያገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛው ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁና ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ ከሦስት እጅ ሁለቱን ማለትም አሁን ካሉት ዘጠኙ ቢያንስ የስድስቱን  ክልሎች ድጋፍ ሲገኙ ነው፡፡ የእነዚህ ክልሎች ምክር ቤቶች ቢያንስ በአብላጫ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁት ይገባል። በዚህ መንገድ ይፀድቃል፡፡

የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶችን እንዲሁም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብን ማመንጨት የሚመለከት ልዩ የሕገ መንግሥት መሻሻል ሒደት ግን ከሕዝብ ተወካዮችና ከፌደሬሽን ምክር ቤቶች በተጨማሪ ሁሉም የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ማፅደቅ ይኖርባቸዋል። እዚህም ላይ እንደ ላይኛው የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምክር ቤቶች ምንም ዓይነት ድምፅ የላቸውም፡፡

ስለሆነም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የማሻሻል ሒደት ጥብቅ ሲሆን፣ በተለይ ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ማሻሻሉ ደግሞ ይበልጥ ጥብቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ወቅት የሚፈጥራቸው አዳዲስ ክስተቶችና አስተሳሰቦች ለማካተት እንዲሁም በአንዳንድ ወገኖች የሚቀርቡ ቅሬታዎች አስፈላጊነት በመመርመር ማሻሻል የሚቻልበት ዕድል ዝግ አይደለም።

ሕገ መንግሥቱ 23ኛ ዓመቱን አክብሯል፡፡ ይሁን እንጂ በኦፊሴል የተደረገ ማሻሻያ እስካሁን እንደሌለ ከላይ ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡ በሌላ አገላለጽ በአዋጅ የወጣ ይፋ የሆነ የለም ለማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በያንስ ሁለት አንቀጾች ተሻሻለዋል፡፡ የመጀመርያው አንቀጽ 98 ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሕዝብና ቤት ቆጠራን የሚመለከተው አንቀጽ ነው፡፡ የመሻሻላቸው ነገር አሳማኝ ነው፡፡ ነገር ግን ሳያሳውቁ፣ ሳይታወጁና ሕዝብም ሳይወያይባቸው መሻሻላቸው በራሱ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፡፡ የማይሻሻል ዘላለማዊ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እስከሌለ ድረስ ይፋ ማድረጉ ሕገ መንግሥቱን ሕይወት መስጠት እንጂ ሌላ ጉዳት አይኖረውም፡፡

ሌላው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እያስፈለገ ነገር ግን ሳይደረግ የተፈጸመውንም ቢያንስ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ ጥሩ ማሳያው የድሬዳዋ አስተዳደር አፈጣጠር ነው፡፡ ድሬዳዋን ፖለቲካዊ ጭንቀት የወለዳት መስተዳድር ናት ማለት ይቻላል፡፡ አግጥጦ መጥቶ የነበረውን ችግር ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ድሬዳዋ ትፈጠር ቢባል ኖሮ ምናልባት የኦሮሚያም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል ምክር ቤቶች በዚያን ወቅት ሊስማሙ ይችል ነበር ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር፡፡

ድሬዳዋ በፌዴራል ሥር እንድትተዳደር ለማድረግ አዋጅ የወጣው የከተማዋ አስተዳደር ላይ የተነሳውን በሶማሌዎችና በኦሮሞዎች መካከል በተነሳው የይገባኛል ጥያቄ መሠረት ነው፡፡ ጭንቀቱ በወቅቱ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ይደረግ ቢባል ኖሮ የኦሮሚያ ጨፌ ወይም የኢትዮጵያ ሶማሌ ምክር ቤት ከክልሉ ላይ ተቀንሶ ለፌዴራል ይሰጥ ሲባል አወንታዊ ምላሽ ሊሰጡ ይችል ነበር ብሎ ማሰብ፣ አንድ ሰው የራሱን ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት በፈቃደኝነት ምንም ቅር ሳይለው ይወስናል ብሎ እንደማሰብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁን ማፅደቅ ከተቻለ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልም ቅያሜ ሊፈጥር ቢችልም ሁሉን ማድረግ ብዙም ለማይሳነው አውራ ፓርቲያችን ኢሕአዴግ፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል አይችልም ነበር ማለት ይከብዳል፡፡

ከማሻሻያ ጋር በተያያዘና የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አፋር ክልል ላይ መከበሩን ምክንያት በማድረግ ሁለት ነጥቦች እናንሳ፡፡ አንዱ ሕገ መንግሥቱ አርብቶ አደሮችን ለመጥራት የሚጠቀምበት ቃልን የሚመለከት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(5) ላይ እንደተገለጸው በአማርኛ ‹ዘላን› በማለት ይጠራቸዋል፡፡ እንግዲህ አፋር ክልልን በምክንያነት የተነሳው አብዛኛው ነዋሪ አርብቶ አደር በመሆኑ የብሔርን ክብርና መብት መጠበቅ እንደዚህ ዓይነት ቃላትንም በማረም ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የቃላት ማሻሻያ ለማድረግስ የግድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ መወያየት ያስፈለገዋልን?

ሁለተኛው ጉዳይ በቅርቡ የምርጫ ሥርዓቱን ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ምክንያት የሚሻሻል የሕገ መንግሥት አንቀጽ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ሕገ መንግሥትን የሚያሻሻል ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ የደረሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ተቃዋሚም ኢሕአዴግንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ የአፋር ክልልን ጨምሮ ሌሎች አራት ታዳጊ ክልሎችን የሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ግን የዚህ ድርድር ተሳታፊ አይደሉም፡፡ ይህ የራሱ መዘዞች አሉት፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ስማቸውን የማያውቃቸው ፓርቲዎች እንኳን ሲሳተፉ ሕገ መንግሥትን የሚያህል ነገር የማሻሻል ውጤት ያለው ድርድር ላይ ማግለል ተገቢም አይደለም፡፡ አሁንም ከድሮው በከፋና በባሰ መልኩ ማሀሉና ዳሩን ማራራቅ ነው፡፡ ቀጥሎም ደግሞ ጤናማ የዴሞክራሲና የፓርቲ ግንኙነት አሠራር ቢኖር ኖሮ ኋላ የማሻሻያውን ሐሳብ እንዳይቀበሉ ያደርጋል፡፡

ሕገ መንግሥቱን በደንብ ነፍስ ይኖረው ዘንድ በየጊዜው እያሻሻሉ መሄድ ይገባል፡፡ የተሻሻሉትንም ይፋ ማድረግ፣ የሚሻሻሉትንም በማሻሻል ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካሄዶችንም በማረቅ ሕይወት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ ካልሆነ ወደ ክለሳ ወይም ለውጥ ሊያመራ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ታሪካችም በቂ ምስክር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0