የፌዴራል መንግስት ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ ዜጎች እንዲፈናቀሉና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀምባቸው ያደረጉ የፖለቲካና የፀጥታ አመራሮች ላይ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እርምጃ ሊወስድ መሆኑ ተገለፀ።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የመስሪያ ቤቱን የ9 ወራት እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት በዛሬው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው የሰላም ግንባታ በማረጋገጥ፣ የፌዴራላዊ አንድነትን በብሄራዊ መግባባትና በክልሎች ተመጣጣኝና ፍትሃዊ ዕድገት ለማምጣት በሚያስችሉ እና በተቋማዊ ሪፎርም የተከናውኑ ስራዎችን ለምክር ቤቱ ገልፀዋል።

ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቀሶችን በማቅረብ በዘላቂነት የማቋቋም ስራ እየተከናውነ ይገኛልም ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት።

በዚህም የፌደራል መንግስት በቋሚነት 1 ሚሊየን 745 ሺህ 800 ኩንታል እህል ያሰራጨ ሲሆን፥ ከ60 ነጥብ 3 በመቶ በላይ በመንግስት ከ39 ነጥብ 6 በላይ ደግሞ በለጋሾች መሸፈኑን አንስተዋል።

ከተፈናቃዮች ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ ዕለታዊ የምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች በቂ ባለመሆናቸው መንግስትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች እርዳታ እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን ከዚህ ቀድም ወደ ቀያቸው ከተመለሱት በተጨማሪ አሁን ወደ ቀደመ መኖሪያቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸውና ፍቃደኝነታቸውን ያረጋገጡ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ፍቃደኛ ሆነው ወደ ቀያቸው ለመመለስ ትራንስፖርት ውስጥ የሚገቡ ዜጎችን ለምን ወደ ቀያቸው ትሄዳላቹ በሚል ድብደባ የተፈፀመባቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

ይህ የሚሆነውም በዜጎች ደም ሃብት የሚያከማቹ፣ በጦር መሳሪያ እና ህገ ውጥ የሰዎች ዝውውር ጨምሮ ዜጎችን የሚያፈናቅሉ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የተሳሰሩ እና በህግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በክልሎች በኩልም በህግ የሚፈለጉ የፖለቲካና የፀጥታ አመራሮችን አሳልፈው የመስጠት ችግር መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ እስካሁን በህግ ከሚፈለጉት ውስጥ 50 በመቶዎች ብቻ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

በመሆኑም የፌዴራል መንግስት እስካሁን ክልሎችን በትብብርና በልመና ተጠርጣሪዎችን አሳልፈው እንዲሰጡ የሚያደርገውን ጥረት በማቆም ያለውን ሰልጣን ተጠቅሞ እርምጃ  በመወሰድ በህግ ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል።

ሰላምን ለመገንባት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች  የሚነሱት አለመግባባቶች  ወደ ግጭት እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚሸጋገሩበት ምክንያት እራስን ብቻ የተቀበለ ለሌሎች ቦታ የሌለው አመለካከት እየተፈጠረ  በመምጣቱ መሆኑንም አመላክተዋል።

በላይ ተስፋዬ – (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *