ከአምስት አመት በፊት ከወርቅ የወጪ ንግድ ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ የተገኘ ሲሆን፥ ባለፈው አመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ግን ወደ 30 ሚሊየን ዶላር ማሽቆልቆሉን ብሄራዊ ባንክ ይገልፃል። ለዚህም ማዕድናት ለኮንትሮባንድ ንግድ በስፋት ተጋላጭ መሆናቸው ቀዳሚው ምክንያት ሆኖ ይነሳል።

ወርቅ አምራች በሚባሉ አካባቢዎች የሚስተዋለው የህገ ወጥ ደላሎች እንቅስቃሴ ከወርቅ ሊገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሬ ምንም ወደሚባል ደረጃ እያደረሰው መሆኑም ይነገራል።

ከዚህ ባለፈም በአነስተኛ መጠንም ቢሆን ወርቅ አምራቾቹ ወርቅ ካመረቱ በኋላ የሚያስረክቡበት የብሄራዊ ባንክ ቅርንጫፍ በአንዳንድ አምራች አካባቢዎች አለመኖሩ የገበያ ትስስሩን በማላላት ህገ ወጥ ንግዱን እንዳባባሰውም ነው የሚነገረው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በበኩሉ የወርቅ ግዥ ማዕከላቱን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር በሚያቀርብለት ጥያቄ መሰረትና ወርቅ በተገኘባቸው አካባቢዎች እንደሚከፍት ገልጿል።

በባንኩ የከረንሲ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አበበ ሰንበቴ ወርቅ አምራች በሆኑ ክልሎች ሰባት የወርቅ ግዥ ማዕከላት መከፈታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ማዕከላቱ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ ጠቅሰው፥ በተከፈቱባቸው ክልሎች ጭምር የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግዱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አንስተዋል። ለዚህም የክልሎች ተቀናጅቶ አለመስራት እና የህግና የአሰራር ክፍተቶችን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

ባንኩም አምራቾች ያመረቱትን ወርቅ በህገወጥ መንገድ ከሚሸጡት ለባንኩ ወርቅ እንዲያስረክቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ አድርጓል።

ለዚህም ባንኩ ከአለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ 5 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ግዥ ሲፈጽም፥ አምራቾች ለሚያቀርቡት ወርቅ 90 በመቶውን ባመጡበት ወቅት ወስደው ቀሪውን 10 በመቶ ደግሞ በወሩ ውስጥ በተመዘገበው ከፍተኛ ዋጋ ተመርጦ እንዲወስዱም ያደርጋል። ይህ ሁሉ እየሆነ ግን አምራቾች ወደ ባንኩ እያስገቡት ያለው ወርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ነው ባንኩ የሚገልጸው።

ለዚህም የአስተዳደራዊ ስራዎች ክፍተት እና አምራቾቹን የመደገፉ እንቅስቃሴ አነስተኛ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ በአምራቾች ላይ የሚጣል ግብርን ጨምሮ ተፅዕኖ የፈጠሩ ህጎች እንደሚሻሻሉ ገልጸዋል።

የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር በበኩሉ ዘርፉን በእውቀት የመምራት ችግር እንዳለ በመጥቀስ ይህን ለመቅረፍ የስልጠና ማዕከል እያቋቋመ መሆኑን አስታውቋል።

አሁን ላይም በፌደራል ደረጃ የተሰጡ የማዕድን እና የነዳጅ ኩባንያዎች ፈቃድ እየተፈተሸ ሲሆን፥ የኩባንያዎቹ ገቢ፣ የምርት መጠናቸው እና ለብሄራዊ ባንክ የሚያቀርቡት የምርት መጠን ተለይቶ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል። መረጃውን በካዳስተር ስርዓት የማስገባቱ ስራም በቅርቡ እንደሚጀመርም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

 (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *