… ደም ተስካር የሆነላቹህ በርቱ፣ ግፉበት። በጥጋብና በእብሪት ተራገሙ። ተሳደቡ። መንጋቹሁን ንዱ። የምትነዱም ተነዱ። ቆንጨራ ግዙ። በደንብ አስሉት። ከዛም እረዱ፣ ግደሉ። ለጌቶቻቹህ ግብር አስገቡ። አምልኳቸው። አትመራመሩ። እነሱ ስለ እናንተ ይጨነቃሉና አጅቧቸው። “ዝጉ” ሲሏቹህ ዝጉ። “ክፈቱ” ሲሏቹህ ክፈቱ። አስተጓጉሉ። አፍርሱ። አቃጥሉ። አውድሙ። አፈናቅሉ። አንድዱ። ቀሙ። ዝረፉ። በደቦ ፍረዱ። ስቀሉ። አካል ተልትሉ ….. በውጭም ያላቹሁ ማቀጣጠያ ቤንዚን ላኩ። እንዳታቋርጡ። መማገጃ ማገዶ ላኩ። ጎ ፈንድድድድድድድድድ !!… ጎ ፈንድ ለበጎ ዓልማም እንዳለ አትዘንጉ

በየቀለሙ እየተመረጠ ነው… ወይፈን ይጣላል። ሙክት ይገነደሳል። መሲና ትወድቃለች፣ ጊደር ትታረዳለች፣ ሰንጋ ይጋደማል። የዶሮ አንገት እየተበጠሰ ይወረወራል፣ ጠቦት በየመልኩ አንገቱ እየተቀነተሰ ይንፈራገጣል። ደም መስኩን አጨቅይቶታል። …  በሚጎርፈው ደም ላይ እየተንከባለሉ እልልታቸውን ያቀልጣሉ። በደም እየተለወሱ መሬት ይደቃሉ። ምንነቱ በማይታወቅ ቋንቋ አረፋ እየደፈቁ ያጉተመትማሉ። አለቃቸው በወርቅ ተሸልሞ ያናፋል… እግሩ ስር ሽቱ እየደፉ ይርመጠመጣሉ …. ትዕይንቱ ይገርማል። የሰው ዘር ከከተማ ነቅሎ ያለቀ ይመስላል። የተጋዙበት መኪና ብዛቱ የቀድሞውን የእናት አገር ጥሪና የባድመ ዘመቻ ያስታውሳል። እዛም ደም ጎርፏል… ለማይረባ ጉዳይ የሰውም የአንሳሳቱም ደም ይደፋል… አለቆች ደሙን እየተጋቱ ይግታሉ … ስካር… ተስካር…. መጨረሻ …. እምዬ ኢትዮጵያ ….

አሁን ያለንበት ጊዜ ከዚህ በምንም አይለይም። ሰንጋው አባቶች ናቸው። ጊደር ልጃገረዶች ናቸው። መሲና ሴተ ላጤዎች ናቸው። ወይፈን ጎረምሶች ናቸው። ጠቦቶች ልጆች ናቸው። ሙክቶች የደረሱት ናቸው። ዶሮዎች ጨቅላ ህጻናት ናቸው። ከየ አይነቱ ደም ፈሷል። አዎ የደም ጎርፍ ወርዷል። አለቆች ይደንሳሉ። አስከሬን ይነግዳሉ። አስከሬን ይሸቅጣሉ። “ጎ – ፈንድ” እያሉ ያከማቻሉ። ወገን ማሰቢያው ስለጠፋበት ግብር ይከፍላል። ግብር ያስገባል። ከአስከሬን ቸርቻሪዎች ጋር እንደ መንጋ ይበራል። ይዘምራል። የወገኖቹን ሬሳ እየተቀባበለ ሙሾ ይወርዳል። ያሽካካል…

የእንስሳት ደም ሲጨቀይ ከአዲስ አበባ በዙም ሳይርቅ ይቅርታ ከፊንፊኔ፣ ይቅርታ ፣ ከበረበራ … ያበደው ይህንን ትርኢት በአይኑ አይቷል። ቦሰናም አይታለች። ደጎል የለበትም። ደጎል በስብእናው ከሰዎች፣ በተለይም ደም ከሚጋቱትና ከሚግቱ አበላዎች ይሻላል። መሻል ሳይሆን ይበልጣል። ውሻን ስድብ ያደረጉ ጅሎች ስለመሆናቸው ምስክር ነው።  ጤና ይስጥልኝ ያበደው ነኝ። እንዴት ከረማቹህ… እንዴት እያደረጋቹህ ነው…

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

ነዋይ አልጠግብ ባዮች “ሴራ” ያመርታሉ። ነዋይ የማይጠግቡ ሴራውን ይረጫሉ። ሴራው ሲመረት በረብጣ ብር በጀት ነው … ያበደው ዘለለ። ወደ ላይ አየ። እንባ አቀረረ። እየሆነ ያለውን አሰላ። ልቡ ደከመችበት። አቅም እንደሌለው ተሰማው። አጥወለወለው። አሞት ተፋ። ቆሽቱ ሸተተው … ወደ ላይ እንዳንጋጠጠ ቀረ።

ለካ የዛሬው እምነት ደም ሆኗል። ለካ የዛሬ እምነት ከሰውነት ደረጃ የሚያወርድ ነው። ለካ የዛሬ እምነት አስከሬን መቸርቸር ነው። ለካ የዛሬ እምነት የህጻናት ደም መጠጣት ነው። ለካ የዛሬ እምነት በደም እየሰከሩ በሚዲያ ማስታወክ ነው። የዛሬ እምነት ግብሩ የናት ደም፣ የህጻናት ደም፣ የአዋቂዎች ደም፣ የእመጫቶች ደም፣ የጨቅላዎች ደም …. በቃ ደም ደም!! ያለ አንዳች ሃፍረት አስከሬን ቸርችረው ይናጥጡናል። በደም ሰክረው ያስታውኩብናል። ሰፊው ህዝብ ” ጎ – ፈንድ” እያለ ግብር ያስገባል። ለዲጂታል ሌቦች ይገብራል። በራሱ ግብር አገሩ ስትፈርስ ያሻካካል። እየተቀያየረ የሚላክትን የትንኮል ፓኬጅ ሳያቅማማ ስፖንሰር ያደርጋል። በሚሊዮን፣ በዶላር፣ በፓውንድ፣ በአይነት፣…… ከልዩ አድናቆት ጋር …. አይ ኢትዮጵያና ሰፊው ህዝብ ….

አብዛኞች ካደፈጡና ዝም ካሉ፣ ጥቂቶች ሰፊው ህዝብ ይሆናሉ። ያስገብራሉ። ይናኛሉ። ይገዝፋሉ። የአብዛኞች መለጐም ጥቂቶች እንዳሻቸው ያለ ዩሉንታ እንዲተፉ ያደርጋል። ቦሰና በዚህ አሳብ ትስማማለች። ቦሰና ከሸዋ ነች። እሷም ዋስትና የላትም። የዘንድሮ ስካርና እብሪት እሷንም ከሰላሌ ጎጆዋ ወደ አባይ ሸለቆ ሊወረውራት ይችላል።

ቦሰና ሲከፋትና እንደ ሉሲፈሩ ሚስት ” ትንታግ ” ልትተፋ ስትል ታቀረቅራለች። ” እነሱ ምን ያድርጉ እንደ ጠንቋይ ቤት ግብር የሚያስገቡትና የሚነዱት አጋሰሶቻቸው ናቸው ….” አለችና ተራገመች። ባድመ የሞተ ወንድም አላት። ስሙን ጠራችውና ” አንተ ታድለሃል” ብላ ሃዘኗን በምጸት ገለጠች።

ባድመ በሰዓታት ውስጥ የሰው ልጅ ምጣድ ላይ እንዳለ ተልባ የተንጣጣበት፣ እንደ ፈንዲሻ የተበታተነበት፣ እንደ ጋማ ከብት ፈንጂ ላይ እንዲሮጥ የተደረገበት … ቦሰና ተነፋረቀች። ስንት ሺህ … አቤት ደም … እኔን እኔን እኔን … ቤት ይቁጠራችሁ … የቦሰና እንባ ደርግ ሊወድቅ አካባቢ እናቶች በምልጃ ሲያፈሱት ከነበረው ከአንዱ ጋር ይመሰላል።

Related stories   የ80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ

” ሞት ሺህ ጊዜ ቢኖር ለሱ” ትላለች። መለስን ካወቀችው ቀን ጀመሮ በደግ አንስታው አታውቅም። ሉሲፈር ነው ትላለች። ሉሲፈር የአጋንንቶች አለቃ መሆኑንን ተምራለች። ሉሲፈሮች የእነሱን ራዕይ የሚያስፈጽሙ ምልምሎች አሉዋቸው። ቢሞቱም አላማቸው አይሞትም። ይኽው አሁን አስከሬን የሚቸበችቡትና ደም የሚጋቱት እነሱ አይደሉ …. ምልምሎቹ…. ቦሰና የተማረቸውን ሳታጓድል አስተጋባች…

ለውጡ የተተበተበው በዚሁ በሉሲፈር መንፈስ ነው። ሉሲፈሮች እጥልቁ ውስጥም ሆነው የደም ግብር ይገባላቸዋል። በህይወት እያሉም ምሳቸው ደም ነው። ለውጥ መጣ። መልካም ዜና መስማት ተጀመረ። አገር አልባዎች፣ የጎረቤት አገር ለማኞች፣ በየስርቻው የነብሩ ወገኖች፣ በየመማቀቂያ የታሸገባቸው ዜጎች በራላቸው። ሞታቸውን ሲቆጥሩ የነበሩ አዲስ ህይወት ያዙ… ሁሉም ከየጽንፉ ወጣ … የታሸገው ተከፈተ። የሉሲፈር ጠረን ገለማ።

ግላምቱ ለውጡን ጋረደው። የታሸገባቸው የደረሰባቸውን ግፍ ሲናገሩ አገር አዘነ። አለቀሰ። ዳሩ ምን ያደርጋል ለውጡ በረከቱን ማሳየት ሲጀምር – መክለፍለፍም ነበረበት የግልማቱ ሃይ አሸነፈውና አነቀው። የገለሙና በሉሲፈር ራዕይ የተጠመቁ አሴሩበት። ለሴራቸው ብር ረጩ። ብር በጆንያ፣ በታንከር፣ በሻንጣ፣ በጎማ፣ በቸርኬ …

ገጀራ ተበተነ። መሳሪያ ተረጨ … ወንድም ወንድሙን እየበላ ነው። ሉሲፈር የደም ግብሩን በምልምሎቹ እየተጋተ ነው …. ያበደው ተወራጨ … ጌዲዮና ጉጂ ሜዳ ላይ የፈሰሱትን ወገኖች ያየ እንዴት ይጨክናል። ጨቅላዎች አፈር ቅመው፣ አፈር ልበሰው ከማየት በላይ ምን ይምጣ… እመጫት የመታረሱ ወግ ቀርቶባት ጡቷ ደረቷ ላይ ተጣብቆ ማየት አያምም… ሃላፊዎች የሚያስተዳድሩትን ህዝብ አግተው እየተደራደሩበት ነው። ቢኒሻንጉል የሆነውስ፣ ሶማሌ ክልል የሆነው…. ፓርላማው ሲወያይ በቲቪ አይቶ ደጎል ወደ ውጭ ወጣ።

እርግጥ ነው ሰሞኑንን የሚሰማው ክሽፈት ነው። ሁሉ ይደረግልኝ ባይ ሆነ። ያውቃሉ የተባሉትም ሌሎችም ጥቅም ጥቅም ጠቅም ብቻ ሆነ ወሬያቸው። ሁሉ ሰላማዊ ስልፍ አድራጊ ሆነ። የታሸገው ሲከፈት ከገለማን ግልማት ጋር አሁን አጥወለወለን። የሚያሰክን ጠፋ። የዛሬ ዓመት አገሪቱ ባዶ ካዝና ነበረች። ተሳፋ እንጂ ባዶ ቦሃቃ ነበረች። ታላባ ታልባ ነጥፋ ነበር። እዳዋ አላላውስ ብሏት ተንደባለል ነበር። ምንዛሬ ነጥፎባት ነበር… ሰውየው ለጤና ባለምያዎች ሲናገሩ ቦሰና አንጀቷን ጭብጥ አድርጋ ትሰማ ነበር። ማይሟ ቦሰና እንዲያ ነገር ግብቷት ችንቀት ሲያንቆራጥጣት ምሁሮቹ ነዋይ ነዋይ ነዋይ ….

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

ያበደው ጮክ ብሎ መለፍለፍ ጀመረ ‘ ጎ – ፉንድ ” ላይ ተረባረቡ። ግብር አስገቡ። የሉሲፈር መንፈስ እንዳይራብ ምልምሎቹን ደጉሙ። ታዘዙ። ባሪያ ሆናችሁ አገልግሉ። ደም አፍስሱ። ደም ይፍሰስ። ህጻናትን እረዱ አሳርዱ። ስጋቸውን ብሉ። አገሪቱን አፍርሱ። ፍራሿንም ጫኑ። ሽጡት። የራሳችሁን ሃውልት አስገንቡ። ስታስገነቡ ሰፋ አድርጉት። ምድር ቤትም ይኑረው። ምድር ቤት እንደ በረዶ ይሁን። መብራት አይኑረው።

ቀጠለ ያበደው- ደም ተስካር የሆነላቹህ በርቱ፣ ግፉበት። በጥጋብና በእብሪት ተራገሙ። ተሳደቡ። መንጋቹሁን ንዱ። የምትነዱም ተነዱ። ቆንጨራ ግዙ። በደንብ አስሉት። ከዛም እረዱ፣ ግደሉ። ለጌቶቻቹህ ግብር አስገቡ። አምልኳቸው። አትመራመሩ። እነሱ ስለ እናንተ ይጨነቃሉና አጅቧቸው። “ዝጉ” ሲሏቹህ ዝጉ። “ክፈቱ” ሲሏቹህ ክፈቱ። አስተጓጉሉ። አፍርሱ። አቃጥሉ። አውድሙ። አፈናቅሉ። አንድዱ። ቀሙ። ዝረፉ። በደቦ ፍረዱ። ስቀሉ። አካል ተልትሉ ….. በውጭም ያላቹሁ ማቀጣጠያ ቤንዚን ላኩ። እንዳታቋርጡ። መማገጃ ማገዶ ላኩ። ጎ ፈንድድድድድድድድድ!!

በረዥሙ ተነፈሰ …. ተዝካር …የደም ተዝካር … እናንተ ሁሉን አዋቂ የሆናችሁ እባክቹህ አርግቡ። አሁን ሚዛን ስተናል። አሁን ልክ አይደልንም። ምልክቶቹ ከምልከትነት በላይ ሆነዋል። ለመዘርፍም ሆነ በትዕቢት ለመኖር አገር ግድ ነው። ተፈጥሯችንን እናስብ። አስከሬን ቸርቻሪዎች ነገ ሲበለሻሽ ጥለውን ይሄዳሉ። የዛኔ ዋይታ ይሆናል። … የደም ተሳካር መጨረሻው ደግ አይሆንም። ያለ አገር አይሆንም። እንደ መንጋ አንነዳ …

እናንተ ያደፈጣቹህ ተናገሩ፣ ዝምታው እስከመቼ ነው። እናንተ ብዙሃኖች ተንፍሱ። እናንተ ዝም ብላቹህ ጥቂቶች ፈነጩ። የናንተ መለዘብ ዋጋው ብዙ ነው። ተነሱ !! ተናገሩ!! ደም ተስካር የሆነላቸውን …… ሰላም ሁኑ !! አሁን ጊዜው የደጎል ነው። ቦሰናም ቡና …

 

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *