የዘመቻ አተራምስ አዝማቾች መልካቸው የተለያየ ነው። ቡድኖች፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ አኩራፊዎች፣ ባለ ረብጣ ህብታሞች፣ ራሳቸውን ታዋቂ አድርገው የሳሉ፣ አዋቂ የሚባሉ፣ የተገዙና ዲርጎ የሚከፈላቸው …  እንደሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይናገራሉ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዘመቻ አተራምስን እሳትና ነዳጅ የሚያከፋፍሉትን ዜጎች ደግሞ ዋልታና ማገር ይሏቸዋል። 

ኢትዮጵያን በማተራመስ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን የማይተኙት የዘመቻ አተራምስ አካላት በውል ከሚታወቁት ውጪ ዓላማቸውና ዋና ፍላጎታቸው ግልጽ አይደለም። እነዚህ ክፍሎች ቆዳቸውን፣ ስማቸውንና፣ ማንነታቸውን በመቀያየር አገሪቱ ሰላሟን ጠብቃ እንዳትሰራ ይተጋሉ። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የጂኦፖሊቲክስና ሶሻልጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንን ጉዳይ ያብራራሉ።

ማህበራዊ ሚዲያው በተለይ (ፌስቡክ) አግባብ ባልሆነ መንገድ አፍራሽ ለሆኑ ተግባራት የመጠቀም ሁኔታ ይስተዋላል። የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ብዙ አገሮችንም እያተራመሰ ይገኛል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አሉባልታ፣ በሬወለደ የሚል የፈጠራ ወሬ፣ የተሳሳተ ዜና እና የግልና የቡድን ስሜት ይስተዋላል። አፍራሽ ማህበራዊ ሚዲያዎች ዘዴ ካልተፈጠረላቸው እሳት ለመጫርም ሆነ ነዳጅ ለማርከፍከፍ ዕድሉ እንዳላቸው መታወቅ አለበት። ይህን አፍራሽ ተግባር ለመቀነስና ለመቆጣጠር ራሱን የፌስቡክን ኩባንያ ትብብር መጠየቅ ይቻላል ወይንም የኢትዮጵያ መንግሥት አቅሙን አዳብሮ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ ይመክራሉ። ያሳስባሉ። 

ፌስቡክ የራሱ ሕግ አለው። ለምሳሌ አንደኛው ሕግ “ግለሰቦችና ድርጅቶችን ለማጥቃት የሚቃጡ፣ ጥላቻ የሚያስፋፉ እና የማይፈልጓቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲገለሉ የሚያደርጉ በፌስቡክ ቦታ የላቸውም” ፌስቡክ እንዲህ ዓይነት ድርጅቶችና ግለሰቦችን አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ አክራሪዎችን የሚያደንቁና የሚደግፉ ግለሰቦችና ቡድኖች አገልግሎቱን እንዳያገኙ ያግዳል። ለምሳሌ ያህል እንደብሪቲሽ ብሔራዊ ፓርቲ (British National Party)፣ የእንግሊዝ መከላከያ ሊግ (The English Defence League) እና ብሔራዊ ግንባር (National Front)ን ጨምሮ ከሰሞኑ 12 የሚሆኑ የእንግሊዝ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ላይ ፌስቡክ ማዕቀብ እንደጣለ ያወሳሉ።

አንዳንድ እርፍት የሚነሱና ወቅታቸውን ያልጠበቁ ጥያቄዎችን ማንሳትና አጀንዳ አድርጎ ማራገብ፣ ያለሙያ ገብቶ መዘባረቅና ስራን ለይቶ አለመስራት የማተራመሻ ስልቶች ናቸው። ፕሮፌሰሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ታሪክ፣ አፈ-ታሪክ፣ ትርክትና ቀዶጥገና የተካሄደበት ታሪክ (doctored history) ተደባልቀዋል። እነዚህ ታሪኮች ሕዝቡን ግራ እያጋቡ ነው። አሁን ብዙ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እያሉ ለምን የአዲስ አበባ ይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑ ያጠያይቃል። የሽግግር ጊዜው አልፎ፣ አገር ተረጋግቶ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በሰከነ መንፈስ ተረጋግቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያቀፈ ውይይት አካሂዶ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ይህ እስኪመጣ አዲስ አበባ “የኔነች” “ያንተ አይደለችም” የሚለው ጊዜውን ያልጠበቀና ብዙ ነገሮችን ያላገናዘበ ንትርክ ሊቆም ይገባል” ሲሉ ይመክራሉ።

” … ጋዜጠኝነትና ፖለቲካ ተንታኝነት በተሳሳተ መንገድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ መሆናቸውም ሌላው መንስኤ ነው” የሚሉት ባለምያው፣  እነኚህ ሁለት የተለያዩ ሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መደበላለቃቸውን ያሰምሩበታል።  የጋዜጠኝነት ሙያ እና ፖለቲካ ተንታኝነት የሚገናኙበት ነገር ቢኖርም ራሳቸውን የቻሉ ሙያዎች ናቸው። ለዚህ ነው የዓለም አቀፍ ዜና አውታሮች ሲ ኤን ኤን፣ አልጀዚራ እና ቢ ቢ ሲ የሚሠሩ ጋዜጠኞች የተለያዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ሲኖሩ የተለያዩ ፖለቲካ ተንታኞችን እያቀረቡ የሚያወያዩት።

ይህ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ላለፈው አንድ ዓመት ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆኑ ሙያቸው ከፖለቲካ ዕውቀት ራቅ ያሉ ሰዎች ሁሉ ተንታኝ ሆነው የተሳሳተ ትንተና ሲሰጡ ይታያል። ሞያተኛ የፖለቲካ ተንታኞች ስላልሆኑ ወገንተኝነት ያጠቃቸዋል፤ እንዲሁም ትንተናቸው ሚዛኑን ያልጠበቀ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የሆነ ውዥንብር ይፈጥራል። ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት የተለያዩ አቅጣጫዎችን የማየት ዕድል ቢኖራቸውም ከሙያቸው የሚጠበቀው ሚዛናዊነት እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ጋዜጠኞች ከወገንታዊነት የነፃ ሂሳዊ ድጋፍ (critical support) ቢሰጡ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ እንደሚጠቅም ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን ሃይሌ  የሚባሉት የህግ ባለሙያ እንደሚሉት በልዩ ስልትና በተቀነባበረ ዘመቻ አገሪቱ ላይ መርዝ እየተደፋ ነው። ሕዝቡ ታጋሽና ሃይማኖተኛ በመሆኑ፣ ከሁሉም በላይ የአብሮነት መስተጋብሩ ጠንካራ በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ የአሸባሪዎቹን ምኞት ያህል አልተጋደለም። አገሪቱም አልፈረሰችም።

” በተደራጀ የፈጠራ ትርክትና ከኩርፊያና ከስልጣን ጥማት የተነሳ ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ መሸገው አገር የሚያተራምሱትን ክፍሎች  የሚከተሉት ዜጎችና እነሱ የሚያመርቱትን መርዝ የሚያሰራጩ ወገኖች ያሳዝኑኛል። ይህ እንደ አገር ክስረት ነው” የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ ቀና አመለካከት ያላቸው ሁሉ ይህንን ሊዋጉ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ይህ ካልሆነ እንዲሁ እያየን አገር አልባ እንሆናለንም ይላሉ።

በትናትናው እለት ምርጫ ቦርድን በሚመሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስም የተነዛውን ወሬ “ታዋቂ” የሚባሉን ጨምረው ሲያራግቡት ነበር። የሸገር ሬዲዮ ላይ ቀርበው ምርጫው እንደሚራዘም ተናገሩ በሚል የብርቱካን ሚደቅሳን ስም በማንሳት የቅጥፈት ዜናውን ሲያሰራጩ የነበሩ ክፍሎች ከሸገር ሬዲዮ ላማታራት እንኳን ፍላጎት አላሳዩም። ዜናው የተሳሳተ መሆኑ ከተነገረ በሁዋላም ቢሆን ማስተባበል አልወደዱም።

ለአሜሪካ ሬዲዮ ምላሽ የሰጡት የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ው/ሮ ሶሊያና ሽመልስ ” ምርጫ ቦርድ ምርጫ ይራዘማል በሚል መግለጫ ሰጥቶ አያውቅም። ይህንን ለማለት ህጋዊ ስልጣንም የለውም” ማለታቸውን ተከትሎ አቶ ሰላሞን እንዳሉት ” እኛ የሚደፋብንን ሁሉ ከማራገብ ውጪ ለአፍታ እንኳን ስለማጣራት አናስብም” ይላሉ።

በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በትውልድ፣ በፖለቲካ እምነት ወዘተ ስልታዊና ዓላማ ያለው መርዝ ስፍራ እየተለየ ቢረጭም የታሰበው መተራመስ ሊፈጠር ባለመቻሉ ዛሬ የወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ደጅ መደረሱን አቶ ሰለሞን በሃዘን ነው የተናገሩት። እነዚህ አኩራፊ፣ ስፖንሰር የሚደረጉ፣ ዘረኛና የዘር በሽታ የለከፋቸው ወነጀለኛ ክፍሎች ከዚህ የከፋ የእልቂት ዜናና ጥሪ በስፋት እንደሚያሰራጩ በመረዳት ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚገባም አበክረው ያሳባሉ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *