መንግሥት እሳት ከማጥፋት ወጥቶ ስር ነቀል ለውጥ ላይ መሥራት እንዳለበት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናገሩ፡፡

ለውጡን ወደ ሕዝቡ በማድረስ እና ጥያቄዎችን በመመለስ በየቦታው እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ማስቆም እንደሚገባም ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የወቅቱን ኢትዮጵያ ግጭቶች እና መፍትሔዎች በመተመለከተ ከፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መረራ ትዝብት አሁን ላይ ለውጡ ወደ ሕዝቡ አልደረሰም የሚለው ሰው ብዙ ነው፡፡ ምክንያታቸውም ሕዝቡ “አመራሮች ተለዋወጡ እንጂ ያው ናቸው፤ አሁንም እየተዘረፍን፣ እየተንገላታን ነው፤ ዘራፊዎች አሉ፤ ለውጡ ከኛ አልደረሰም” እያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ውሎ አድሮ ሕዝቡን ወደ ተስፋ መቁረጥ ሊወስድ ስለሚችል መንግሥት (ገዥው ፓርቲ) በጥንቃቄ መሥራት እንዳለበት ነው ፕሮፌሰር መረራ ያሳሰቡት፡፡

ይህም አለመረጋጋት እና ግጭቶች እንዲበራከቱ ካደረጉ ምክንቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ ብዙ ጥቅም የለመዱ የገዥው ፓርቲ ወዳጆች እና ካድሬዎችም ‹‹በቃችሁ›› ሊባሉ እንደሚገባ ያሳሰቡት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ሕዝቡን ማማረሩ ከቀጠለ ውጤቱ ለሀገርም ሆነ ለራሳቸው ለችግር ፈጣሪዎች አደገኛ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ በሀገሪቱ እየታየ ላለው አለመረጋጋት በመንስኤነት ያነሱት ሌላው ችግር ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ አለመድረስን ነው፡፡

“በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድ ሀገራዊ መግባባት አለመምጣታቸው ሁሉም በየራሱ ፍላጎት እና አቅጣጫ እንዲጓዝና አንድነት እንዳይመጣ ምክንያት እየሆነ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች “የተሻለ፣ የረባ፣ መሬት የነካ ስምምነት ላይ መድረስ እና ብሔራዊ መግባባትን ማምጣትን ለድርድር ማቅረብ የለብንም” ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸውን የቤት ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው ነው ሐሳብ የሰጡት፡፡ “በፓርቲዎች መካከልም የሚጋጩ ሕልሞችን ይዞ ሀገርን ወደ ፊት ማስኬድ አይቻልም፤ ከተቻለ ማስታረቅ፣ ካልሆነ ደግሞ ከመጠፋፋት መቆጠብ ግን የግድ ነው፤ ምክንያቱም ከግጭትና ከመጠፋፋት ትርፍ ስለሌለ” ነው ያሉት፡፡ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ሀገሪቱ አደገኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን እንደሚያሳይም ነው የተናገሩት፡፡

ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥው ፓርቲን ጨምሮ) እና በተለያዩ መንገዶች የተደራጁ ኃይሎች መፍትሔዎችን ይዞ መሐል መንገድ ላይ መገናኘትና ከግትርነት ወጥቶ ስለመፍትሔዎችም መሥራትና መምከር የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት እንደሚያግዝ አመላክተዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

“ከዚህ ይልቅ አንዱ የአንዱን ሞትና ጥፋት መመኘት ግን ውጤቱ ጥፋት ነው፤ ስምምነት ላይ እንኳን ባይደረስ ‘ሕዝባችን ምን ይላል?’ ብሎ ማማከር ይገባል እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ ከሰል መቀባት ተገቢ አይሆንም” ነው ያሉት፡፡

በበሰለ ውይይትና ምክክር መፍትሔ መስጠት ላይ ማተኮር እንጂ እሳት ማጥፋት ላይ ብቻ መጠመዱ ለመንግሥትም ለሕዝቡም አይበጅም ያሉት ፕሮፌሰር መረራ የማንነት እና ሌሎችም ለለውጡ ምክንያት የነበሩ ጥያቄዎችን ስር ነቀል በሆነ መንገድ መፍታት፤ ሕዝቡንም ከምዝበራ በመታደግ ትክክለኛ የለውጥ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ጥያቄዎችን አፍኖ መያዙ እልቂት እንጅ መፍትሔ ስለማያመጣ በፍጥነት ሕዝቡን በማሳተፍ ወደ መፍትሔ መገባት እንዳለበትም የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መረራ ሐሳብ ሀገር ካልተረጋጋ ስልጣንም ሆነ ሁሉም ነገር እንደሚቀር መገንዘብ እንጂ ለሁሉም ኢትዮጵውያን የሠላምና መረጋጋት መንገዶችን ከማመቻቸት ይልቅ ‹‹ሀገሪቱ ብትናጋ ወደ ስልጣኔ እመለሳለሁ፤ እጠቀማለሁ›› በሚል ሕልም ውስጥ መግባት ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ ከቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር አስከፊ ውጤት መማር እንደሚገባም ነው ያስታወሱት፡፡

“ሁላችንንም የሚጠቅመው ለውጡን ማስቀጠል ነው፤ ኢሕአፓን ቁርስ፣ መኢሶንን ምሳ፣ ሌሎችን ደግሞ እራት ካደረገው የደርግ የለውጥ ጉዞ መማር ይገባናል፤ የቀድሞውን ሥርዓት እንመልስና እንጠቀማለን ብሎ ማሰብ ሕልም ነው የሚሆነው፤ ሕልሙ ደግሞ ሁላችንንም ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል” ነው ያሉት፡፡

ገዥው ፓርቲ ግጭቶችን ቀድሞ መከላከል ላይ ድክመት እንዳለበት ያመላከቱት ፕሮፌሰር መረራ አሁን በየቦታው እየፈነዱ ላሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እውነታውን ይፋ እያደረጉ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ወደ እሳት ማጥፋት መሄዱ ተገቢነት እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡ “በአንድ ሀገር መንግሥት ከሚያስፈልግባቸው እና ከዋና ዋና ሥራዎቹ ቀዳሚው የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት መጠበቅ ነው፤ ይህ ካልሆነ የመንግሥትነት ሚናው እየኮሰመነ ይሄዳል፤ በመሆኑም የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ለድርድር መቅረብ የለበትም” ብለዋል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ደፍረው እውነታውን ከማውጣት ይልቅ የሚገፏቸው ነገሮች እና የሚወስዷቸው እርምጃዎች ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ያብራሩት ፕሮፌሰር መረራ በለውጡ ፍጥነት እና ጥልቀት ላይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እየተፈራሩና የተለያየ አቅጣጫ ላይ ሆነው የሚወስዷቸው እርምጃዎች እና ውሳኔዎች ውለው አድረው ችግር እንደሚያስከትሉ ማጤን እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ “በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቡዳው ማን ነው? ማን ነው የፖለቲካ ችግር እየፈጠረ፣ እያስቸገረ ሀገርን ሰላም የሚያሳጣው?” የሚለውን መለየት እና ለሕዝብ ማሳወቅም ተገቢ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡ “እራሳችን ተዋክበን ሕዝቡን የምናዋክብ ልሂቃንም ችግር ከመፍጠር ይልቅ መፍትሔ እንሁን፤ ይህ ዓይነት ጉዞ ዋጋ ያስከፍላል” ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ፡፡ ለመግባባትና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ደግሞ ሁሉም መፍትሔ ይዞ መንገድ ላይ መገናኘት አለበት እንጂ የየራሱን ፍላጎትና ሕልም ይዞ ሲሄድ መቆሚያው እንደሚጠፋ እና ውጤቱም አስከፊ እንደሚሆን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘ(አብመድ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *