ኢትዮጵያ አሁን የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን እንድትጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ አለመሆኗን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አሁን ላይ የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬዋን ለመጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም፤በተያዘው ዓመት አገሪቷ በቂ ሊባል የሚችል የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳላትም ተናግረዋል።

አንድ አገር የውጭ ምንዛሬን በመጠባበቂያነት የምታስቀምጠው አገሪቷ ችግር ሲገጥማት አውጥታ ለመጠቀም እንጂ የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚውን ለመምራት አለመሆኑንም አስረድተዋል።

የአገሪቷ የዕለት ተዕለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚመራው  ከወጪ ንግድ ፣ ከብድርና እርዳታ ፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ከዳያስፖራው በሀዋላ ከሚላክ  የውጭ ምንዛሬ መሆኑንም እንዲሁ።

በየጊዜው የሚከፈሉ የውጭ ዕዳ ክፍያዎች፣ ለግል ዘርፉ ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ ለነዳጅና ለመድሃኒት ግዥና ለመሳሰሉት ወጪዎችም በዚሁ የሚሸፈኑ ይሆናል።

እንደ ዶክተር ይናገር ገለፃ በአሁኑ ጊዜ አገሪቷ ከላይ የተጠቀሱት የውጭ ምንዛሬ ምንጮች ያልተቋረጡ በመሆኑ የመጠባበቂያ ክምችቷን እንድትጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም።

በተያዘው ዓመትም ከተለያዩ የውጭ አገሮች ምንጮች የተሻለ የውጭ ምንዛሬ በመገኘቱ ከባለፉት ዓመታት በተሻለ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያዋ ክምችት መኖሩንም አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ያህን የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ ባይችልም ኢኮኖሚውን አሁን ባለበት ሁኔታ ማስቀጠል የሚያስችል በቂ የውጭ ምንዛሬም አለ ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የወጪ ንግድ ማሳደግ ግን ዋነኛው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

አዲስ ዘመን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *