የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኢጀንሲ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ በነበሩ ሰባት ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ።

በኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ሲሰሩ የነበሩ ሃይለስላሴ ቢሆን፣ የማነ ብርሃን ታደሰ፣ ሙከሚል አብደላ፣ ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴን፣ ያሬድ ይገዙ፣ አንዳርጋቸው ሞግሪያ እና ያለው ሞላ በዛሬው ዕለት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው ተከሳሾች የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት የፌዴራል የመንግስት ግዥ አፈፃፀም መመሪያን ወደ ጎን በመተው የተለያዩ መድሃኒት ግዥዎችን ያለ ውድድር ከአቅራቢ ድርጅቶች በቀጥታ በመግዛት 14 ሚሊየን 855 ሺህ 391 ብር በመንግስትና በህዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል መከሰሳቸውን ያስረዳል።

ተከሳሾች የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ) እና 411 (1) (ሐ)ና (2) የተቀመጠውን በመተላለፍ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን የክሱ ጭብጥ ያስረዳል።

ተከሳሾች የፌዴራል መንግስት የግዥ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 52 እንዲሁም በ2002 ዓ.ም የወጣውን የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ አንቀጽ 25 በተጨማሪም በመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ የግዥ መመሪያ አንቀጽ 10.33ን በመጣስ ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አገልግሎት የሚውል ልዩ ልዩ መድሃኒቶችን ከሲትረስ ኢንተርናሽናል የ13, ሚሊየን 855 ሺህ 391 ብር እንዲሁም ከአልኮል ላቦራቶሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አትሮፊን ሰልፌት አንድ በመቶ የአይን ጠብታ መድሃኒት የ1 ሚሊየን 406 ሺህ 281 ብር በድምሩ 15 ሚሊየን 261 ሺህ 672 ብር በመንግስትና በህዝብ ላይ ጉዳት በማድረስ በዋና ወንጀል አድራጊነት መከሰሳቸውን አብራርቷል።

በተመሳሳይ በሌላ መዝገብ ሃይለስላሴ ቢሆን፣ የማነብርሃን ታደሰ፣ ሙከሚል አብደላ፣ ሳፊያ ኑር እና ማስረሻ አሰፋ በመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሰራተኛ ሆነው ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት በጨረታ ተሸናፊ ከነበሩ ኢፋርም፣ ፋርማኪዩር እና ካዲላ ፋርማሲዩቲካል ከተባሉ ድርጅቶች የ104 ሚሊየን 47 ሺህ 316 ብር ግዢ በቀጥታ በማከናወን ሌሎች አቅራቢ ድርጅቶች ካቀረቡት በመብለጡና በመንግስትና በህዝብ ላይ 313 ሚሊየን 116 ብር ጉዳት በማድረስ መከሰሳቸውን የዐቃቤ ህግ ሪፖርት ያስረዳል።

በሁለቱም መዝገቦች ላይ የቀረቡት የተከሳሾች ጠበቆች የክስ መቃሚያ ለማቅረብ ጊዜ ይሰጠን በማለት የጠየቁ ሲሆን፥ ተከሳሾች በዋስትና ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከራከሩ ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ተከሳሾች የተከሰሱበት የህግ ድንጋጌ የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄዎቻቸውን ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት ግንቦት 13 ቀን 2011ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን፥ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ማገዱንም አሳውቋል።

በአንደኛው መዝገብ ያልተያዙ ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴንና አንዳርጋቸው ሞጎሪያ የፌዴራል ፖሊሲ በአድራሻቸው መጥሪያ በማድረስ ለግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ መታዘዙን ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

(ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *