የአስጎብኚ ድርጅት ሹፌር ነኝ፡፡ አለቃዬ አንድ ጥቁር እንግዳ በአ.አ ጎዳናዎች እንዳንሸራሽር አዘዘኝ፡፡ ጓድ መንግሥቱ በድብቅ ሀገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎችን በጥንቃቄና በሚስጥር አስጎብኛቸው ሲል በደፈናው ትዕዛዝ ሰጠኝ፡፡ መስተዋቱ በተሸፈነ “የደህንነት” መኪና ውስጥ ወደ ተቀመጡት ሰው አመራው፡፡ ሳያቸው ድንግጥ አልኩ፡፡ በእጃቸው አጭር በትር ይዘዋል፡፡ ዐይናቸው ጎላ ብሎ ይታያል፡፡

“ደህና ዋሉ?” ትኩር ብለው በግንባራቸው ቂጥ ዐዩኝና “በመጀመሪያ ወደ አብዮት አደባባይ ወስደኸኝ ስታበቃ፣ ቀጥሎ ወደ ወደ ቤ/መንግስቱ አካባቢ እናመራለን፡፡” የዚህ ድምፅ ቅላፄ ድንገት ወደ ልጅነት ዘመን ትዝታዬ አነጎደኝ፡፡ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለው ዳንቴል ወደተሸፈነችው ሬዲዮናችን፡፡

በመንገዳችን በሙሉ ኮለኔሉ በተዋጣለት ፉጨት የድሮ የሀገር ዜማዎችን ማዜም ያዙ፡፡ በተለይ “ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል፣ 
ያ ጥቁር ግሥላ ደም ሸቶታል…” የሚለውን ዜማ ዋሽንት በሚያስንቅ ፉጨት ቢያዜሙትም የሆነ ስሜት የሚረብሽና የሚያስፈራ ስሜት አመጣብኝ፡፡

ድንገት ኦሎምፒያ አካባቢ ስንደርስ ጥያቄ ሰነዘሩ “እኔ እምለው አንተ ወጣት፣ ዛሬ ንግሥ አለ እንዴ?” 
“ኧረ የለም?” 
“እሺ ወያኔ ሕዝቡን ሠልፍ ጠርታዋለች?” 
“ኧረ አልጠራችም” 
“እና ሠፊው ሕዝብ መንገድ ላይ ምን ይሰራል? የሥራ ሰዓት አይደለም እንዴ አሁን?” 
“ያው በዝተን ነዋ፡፡ ሁሌም እንዲሁ ነን፡፡ አሁን ጦርነት ስለሌለ በዝተናል ኮለኔል መንግሥቱ” አልኳቸው።
“አሽሙር መናገርህ ነው፡፡ ለእናት ሀገር መሞትን የወሊድ እንክብል ከመጠቀም ጋር ታወዳድራለህ? የነገሩህን ነው አንተ ምንታደርግ፡፡ አቁምልኝ አሁን እዚህ ጋ!” አሉ አብዮት አደባባይ ስንደርስ፡፡ መስታወቱን ዝቅ አድርገው ፀጥ አሉ፡፡ ፍዝዝ ብለው አካባቢውን ቃኙ ግን የሆነ ነገር አበሳጫቸው፡፡ ገና ሮጦ እንደቆመ ሰው ከላይ ከላይ መተንፈስ ጀመሩ፡፡

“ወያኔ ሀገሩን በመሉ፣ ታሪካችንን ሲያወድም መክረሙን ብንሰማም፣ በአብዮት አደባባይ ላይ ግን እንዲህ ያለው ግፍ ሲሰራ፣ ሰፊው ሕዝብ በዝምታ ይመለከታል ብዬ አልጠረጠርኩም፡፡

ስንት ታንክ፣ መትረየስ፣ ቦምብ፣ ሚሳኤል፣ ትርዒት ያሳየንበትን ከፍተኛ አብዮታዊ መልዕክቶችን ያስተላለፍንበትን ታላቅ መድረክ ሆን ብሎ ምሽግ በምሽግ ማድረግ የወንበዴ ሴራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል” ተበሳጩ፡፡ ዐይናቸውን በፍጥነት እንደ ጠረጴዛ ቴኒስ ኳስ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደግራ አመላለሱት፡፡ ዛሬም ያስፈራሉ፡፡

“ሕዝባዊት ቻይናን ጎብኝተናል፣ ሶቭዬት ሕብረትን ዐይተናል፣ የካስትሮን እናት ሀገር ተዘዋወረንበታል፡፡ አንድም ባቡር በታላላቅ አደባባዮች ላይ ሲንፏቀቅ፣ በቆጥ ላይ ሲሰቀል አላየንም፡፡ ሰው እንዴት ዕድሜ ልኩን ምሽግ ሲቆፍር ይኖራል? ይኼ ከምሽግ ቆፋሪነት ባሕሪ የመነጨ የፍልፈል ሥነልቦና ነው፡፡ መቆፈር፣ መቆፈር፣ መመሸግ፣ መመሸግ፡፡” ተቆጡ፡፡

“እስቲ ወደ ቤተ መንግሥቱ ውሰደኝ፡፡” አሉ፡፡ ሂልተንን አልፈን ወደ ዋናው ቤ/መንግሥት ስንቃረብ፣ አልቻሉም፡፡ ድምፅ ሳያሰሙ አለቀሱ፡፡ ፍዝዝ ብለው ወደ ውስጥ እያዩ በር ላይ ያለውን ጥበቃ ሲያዩት ከራሳቸው ጋር አወሩ፡፡ “ውይ ይኼኛው ወታደር ደግሞ የጀግናው አብዮታዊ ሠራዊታችን አባል ይመስል የለም እንዴ፡፡ እህ.. እህ.. እህ…” ሌላ ለቅሶ፡፡

በመንገድ ላይ አንድ አፍሮ ፀጉሩን ያበጠረ ጎልማሳ ሰው ሲያዩ “ይኼ ጓድ ፍቅረሥላሴ አይደለም እንዴ?” አሉ፡፡ “ኧረ እኔ አላውቃቸውም” በመሃል የከፈትኩት ሬዲዮ የቀትር ዜና ማሰማት ጀመረ፡፡ ድምፅ ጨምርበት አሉኝ፡፡ ጨመርኩበት፡፡ “ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው” ሲል በደስታ በትራቸውን በሁለት እጃቸው ወደላይ እንደተሸለሙት ዋንጫ አነሱት፡፡ ፈገጉ። ወዲያው “ደርግ የተደመሰሰበት የዘንድሮው ግንቦት ሃያ በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡” ብሎ ነገር አበላሸ፡፡ ወርጄ ለመሮጥ ሁሉ አሰብኩ፡፡ ዐይኔን በድንጋጤ አፈጠጥኩ፡፡ በመስታወቱ ቀስ ብዬ ሳያቸው፣ አቤት የተናደዱት መናደድ፡፡

“ደምስስልኝ ማነው አጥፋልኝ ይኼን የወንበዴ ሬዲዮ፡፡ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በዶጋሌ ስንት በጀግንነት የተሰዉ ልጆ እንዳላፈራች፣ እናት ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ የወሮበላ መጫወቻ መሆኗ ያሳዝናል፡፡ ደርግ የተደመሰሰበት ይላል ይኼ የሽፍታ አፈቀላጤ፡፡ ደርግ ምን አደረገ? ወያኔና ሻዕቢያ አይደሉም እንዴ…”

ፌስቡክ እንዳስታወሰን (ድጌ)

Samson Getachew T S

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *