May 9, 2021

ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በታሪካዊው ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ምን አለ?

… ልጅ እያሱ፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ አጤ ኃይለ ሥላሴ ንጉስ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዚህ ቤት ኖረውበታል። ቤቱ በእንጨትና በድንጋይ የተሠራ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ነው። ፊቱን ወደ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ያዞረው ህንፃው በአጤ ሚኒሊክ የተሠራ ሲሆን አዲስ አበባን ቁልቁል ለማየት የሚያስችል ነው። የኪነ ህንፃ ባለሙያዎች ‘የአዲስ አበባ መልክ አለው የሚባል የሕንፃ ዓይነት ነው’ ይሉታል- ኢትዮጵያዊ ጥበብ ያረፈበት መሆኑን ለመግለፅ።

BBC Amharic – አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ሕንፃና የቅርስ ጥበቃ መምህር ሲሆኑ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከሚደረገው እድሳት ጋር ተያይዞ በበጎ ፈቃደኝነት ያስጎበኛሉ።

እርሳቸው እንደነገሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ መንግሥቱ ከመጎብኘቱ አስቀድሞ ‘እንግዶች ስለሚመጡ ባለሙያዎች ቢያስጎበኟቸው ይሻላል’ በሚል ከቅርስ ጥበቃ፣ ከኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች፣ የታሪክ አዋቂዎች የተውጣጡ ሰባት ባለሙያዎች በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የተጋበዙ ሲሆን እርሳቸው አንዱ ነበሩ።

በወቅቱም የሚያሰማሙ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የጋራ ነጥቦች ያዘጋጁ ሲሆን፤ ለጎብኝዎች ገለፃ ሲያደርጉ ነበር፤ በተለያየ ጊዜም ቤተ መንግሥቱን የመጎብኘት ዕድል ገጥሟቸዋል፤ በመጭው መስከረም ወር ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ ምን አለ? ስንል ጠይቀናቸዋል።

ቤተ መንግሥቱ በ40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡ የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኙበታል።

ከስፋቱ የተነሳ ቦታውን ለማስጎብኘት በቤተ መንግሥት ውስጥ ያሉትን ቦታዎች በ5 ይከፍሉታል። አንደኛው በፊት ተትቶ የነበረ የቤተ መንግሥቱ ጓሮ ሲሆን በዚህ ሥፍራ የወዳደቁ ቆርቆሮዎች፣ የወታደሮች መኖሪያ፣ የተበላሹ የጦር መኪኖች የሚቆሙበት ቦታ ሲሆን አሁን እድሳት ተደርጎለት ጥሩ የመናፈሻ ሥፍራ ሆኗል።

ሁለተኛው አጤ ሚኒሊክና አጤ ኃይለ ሥላሴ ያሰሯቸው የቤተ መንግሥትና የጽ/ቤት ሕንፃዎች ይገኛሉ።

ሦስተኛው የኮሪያ መንግሥት ያሰራቸው ቢሮዎች ሲሆኑ አሁን አገልግሎት እሰጡ ይገኛሉ፤ ይሁን እንጂ ለሕዝብ ጉብኝት ክፍት አይሆኑም።

አራተኛው በተለያየ ምክንያት የማይጎበኝ ሲሆን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ካገር በወጡበት ጊዜ ቢሯቸው ይሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች እርሳቸውን ለማስደሰት የሰሩላቸው እዚያው ግቢ ውስጥ ነጠል ብሎ የተሰራ ቤት ነው።

• ወመዘክር፡ ከንጉሡ ዘመን እስከዛሬ

ይህም ብቻውን የተሰራና ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መኖሪያ ጀርባ ይገኛል። ለመጎብኘትም በመኖሪያቸው ማለፍን ስለሚጠይቅ ለጉብኝት ክፍት አይሆንም። የዚህ ቢሮ የተወሰነ ክፍሉ እንደፈረሰም ይነገራል።

አምስተኛው በሸራተን ሆቴል በኩል ሲታለፍ የሚታየውና በፊት ገደላማና ጫካ ሆኖ የሚታየው አዲስ የሚሰራው የእንስሳት ማቆያና አኳሪየም (የውሃ አካል) ሲሆን ግንባታ እየተካሄደበት ነው።

አሁን ሙሉ ቤተ መንግሥቱን ልንጎበኝ ነው፤ አርክቴክት ዮሐንስ አንድ ሰው ቤተ መንግሥቱን ለመጎብኘት ሲገባ ከሚያገኘው ይጀምራሉ።

1ኛ. የመኪና ማቆሚያና ሞል

ይህ ቦታ ከሒልተን ሆቴል ወደ ላይ አቅጣጫ ስንጓዝ ቤተ መንግሥቱ ከመድረሳችን በፊት በስተቀኝ ይገኛል። ታጥሮ የቆየ ባዶ ቦታ የነበረ ሲሆን አሁን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ይሰሩበታል። በቅርቡ ግንባታው የሚጀመር ሲሆን ለጎብኝዎች የመኪና ማቆሚያ ሆኖም ያገለግላል።

ይሁን እንጂ ግንባታው ስላልተጠናቀቀ ሰው የሚገባው በታች ባለው የደቡብ አቅጣጫ በር ነው፤ እዚያ ሲደርሱ የትኬት ቢሮ፣ ሻይ ቤት፣ መታጠቢያ ክፍሎች፣ የእንግዶች ማረፊያና መረጃ የሚሰጥባቸው ቦርዶችና ዲጂታል ማሳያዎችን ያገኛሉ።

ይህ የትኬት ቢሮ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ሲሆን ከመሬት ጋር ተመሳስሎና ተስተካክሎ የተሰራ በመሆኑ ከላይ ሲታይ ቤት መሆኑን በጭራሽ አያስታውቅም።

2ኛ. የመረጃ መስጫ ቦታ

ይህን ሥፍራ ከትኬት ቢሮው ወደ ላይ ሲጓዙ ያገኙታል። በዚህ ቦታ ለጉብኝት ክፍት የሆኑ ቦታዎች በዲጅታልና በህትመት ገለፃ ይደረግበታል። ከጥላ ጋር የተዘጋጀ ማረፊያ ወንበሮች ያሉት ሲሆን ተሰርቶ ተጠናቋል።

እሱን አለፍ እንዳልን ልጆች የሚቆዩበት የመጫዎቻ ቦታ እናገኛለን፤ በጣም የተጋነነ ባይሆንም መጠነኛ ተደርጎ ለልጆች መጫዎቻ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ተሟልቶ የተዘጋጀ ነው።

አረንጓዴ ሥፍራ ተብሎ የተሰየመውን ጠመዝማዛ መንገድ ደግሞ የልጆች መጫወቻውን እንዳለፍን እናገኘዋለን። ቦታው ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚኬድበት ዳገታማ መንገድ አለው፤ ይህም ለአካል ጉዳተኞች እንዲመች ተደርጎ በእግረኛ መረማመጃ ንጣፍ የተሰራ ነው።

ወደፊት በግራና በቀኝ ኢትዮጵያዊ ሆኑ የጥበብ ሥራዎች አሊያም ታሪካዊ ሁነቶች ማሳያዎች ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፤ አሁን ዛፎችና ሳሮች የተተከሉ ሲሆን መንገዱም ዝግጁ ሆኗል።

3ኛ. የልዑላን ማረፊያ ቦታ

ልጅ እያሱ፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ አጤ ኃይለ ሥላሴ ንጉስ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዚህ ቤት ኖረውበታል። ቤቱ በእንጨትና በድንጋይ የተሠራ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ነው። ፊቱን ወደ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ያዞረው ህንፃው በአጤ ሚኒሊክ የተሠራ ሲሆን አዲስ አበባን ቁልቁል ለማየት የሚያስችል ነው። የኪነ ህንፃ ባለሙያዎች ‘የአዲስ አበባ መልክ አለው የሚባል የሕንፃ ዓይነት ነው’ ይሉታል- ኢትዮጵያዊ ጥበብ ያረፈበት መሆኑን ለመግለፅ።

ከፊት ለፊቱ አዲስ የተሠራና ብዙ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ፎቶ የሚነሱበት ሥፍራ አለው። በቅርቡ በተደረገው የእራት ግብዣ በነበረው ጉብኝት ቤቱ እንዳይጎዳ በሚል ውስጥ ሳይገባ ከውጭ ነበር የተጎበኘው።

4ኛ. የዳግማዊ አጤ ሚኒሊክ ጽ/ቤትና መኖሪያ ቤት (ኮምፕሌክስ)

በዚህ ሥፍራ መጀመሪያ የምናገኘው የፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) መኖሪያ ነው። አባ መላ የአጤ ሚኒሊክ የጦር ሚንስትር የነበሩ ሲሆን ይኖሩበት የነበረ ትንሽ የእንጨት ቤት ከአጤ ምኒሊክ መኖሪያ ቤት ጎን ላይ ይገኛል።

አጤ ሚኒሊክ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላም እንደ መኖሪያና ቢሮ አድርገው ሲጠቀሙበት ነበር። ቤቱ ፈርሶ የነበረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ታድሷል።

ወደ አጤ ሚኒሊክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽ/ቤት በሮች በእንጨት የተሠሩ ሲሆን በሚያምር መልኩ የአበባና የሐረግ ጌጥ የተፈለፈለበት ነው። ይህ ቤት ከሁለት ሌሎች ቦታዎች ጋር በድልድይ ይገናኛል። አንደኛው በሰሜናዊ አቅጣጫ የአጤ ምኒሊክ የፀሎት ቤትና የስዕል ቤት ሲሆን እንቁላል ቤት በመባል ይጠራል። አንዳንዴም እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበት ነበር።

የአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ በቀደመው ጊዜImage copyrightDANIEL KIBRET FBአጭር የምስል መግለጫየአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ በቀደመው ጊዜ

የፀሎት ቤቱና የስዕል ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ነው። ሁለተኛው ፎቅ ላይ ከፍ ብላ የተሰራች በመስታወት የተሸፈነች ቤት አለች፤ ይህች ቤት ‘ቴሌስኮፕ’ ያላት ሲሆን አዲስ አበባን በሁሉም አቅጣጫ ማየት ያስችላል።

በዚች አንቁላል ቤት መገናኛው ድልድይ ጋ የመጀመሪያው ስልክ የገባበት ቤት ይገኛል። ቤቱ ከድንጋይና ከእንጨት የተገነባ ነው። አርክቴክት ዮሐንስ የኪነ ህንፃውን ጥበብ ሲገምቱ ከአርመኖችና ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሕንዶች ሳይሳተፉበት እንደማይቀሩ ይገምታሉ።

ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የውይይት ክበብ በመሆን አገልግሏል።

ሌላኛው ከአጤ ሚንሊክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት ነው። ይህ ቤት ከቤተ መንግሥቱ በምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ነው።

በምድር ቤት የዙፋን ግብር ቤት ይገኛል። የነገሥታቱ መመገቢያ አዳራሽ ሲሆን ንጉሣዊ ቤተሰቦች ምግብ የሚመገቡበት ክፍል ነበር፤ ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የደርግ ምክር ቤት መሰብሰቢያ በመሆን አገልግሏል።

5ኛ. ሦስት አብያተ ክርስቲያናት

አብያተ ክርስቲያናቱ ከግብር ቤቱ አዳራሽ በስተ ምሥራቅ በኩል ይገኛሉ።

ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን (የአጤ ሚኒሊክ ሥዕል ቤት)፡ በአጤ ሚኒሊክ ጊዜ ለብቻ በአጥር ያስከለሏት ሲሆን አሁን ሕዝብ ይገለገልባታል። ይሁን እንጂ አጤ ሚኒሊክ ከመኖሪያቸው ተነስተው የሚሄዱባት መንገድና በር አሁንም ድረስ ይገኛል።

የባታ ማሪያም ቤተ ክርስቲያ (በንግሥት ዘውዲቱ የተሰራ ሲሆን የአፄ ሚኒሊክም አፅም ያረፈው እዚሁ ነው) አሁን ከቤተ መንግሥቱ ውጭ ሲሆኑ ጥበቃ ይደረግለታል። ጎብኚዎችም ሲመጡ እዚያ ያሉት ካህናት ምድር ቤት ያለውን መቃብራቸውን ከፍተው ያሳያሉ።

በበርካታ ሰው የሚጎበኝም ከሆነ ለቤተ መንግሥቱ ቀድሞ እንዲታወቅ ይደረጋል። ሦስተኛው ከዚህ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ የሚገኘውም የገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ነው።

6ኛ. ታችኛው የዙፋን ችሎት

ይህ ችሎት በአጤ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተሠራ ሲሆን በታችኛው መዋቅር ያልተፈታ አገራዊ ጉዳይን የሚያዩበት የ’ሰበር ሰሚ ችሎት’ ቦታ ነው።

ይህ ባለ አንድ ፎቅ ቤት የንጉሡ ጽ/ቤትም በመሆን አገልግሏል። በውስጡ ጽ/ቤታቸውን ጨምሮ መዝገብ ቤትና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችም አሉት።

አጤ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ሲወርዱ የደርግ ወታደሮች ቤቱን ተቆጣጥረውት ነበር። የኮሎኔል መንግሥቱ አስተዳደርም ቢሮ አድርጎ ይጠቅምበት ነበር። ንጉሡ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላም ችሎታቸውና ቢሯቸው ከነበረው ቦታ ምድር ቤት እንደተቀበሩና በኋላም አፅማቸው ወጥቶ እንደተወሰደ ይነገራል።

የደርግ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ቢሮ፣ የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ረዳት የመንግሥቱ ገመቹ ቢሮ፣ እንዲሁም ታስረው የነበሩ ደርግ ወታደሮች የታሰሩበት ቦታም ነው።

በአንድ ወቅት በመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ላይ የመግደል ሙከራ በተደረገበት ጊዜ ያመለጡበት ቦታም ይሄው ሕንፃ እንደሆነ ይነገራል።

ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠርም የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ይህንን ሕንፃ መኖሪያ አድርገውት ነበር።

አቶ መለስ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላም አስክሬናቸው የወጣው ከዚሁ ቤት ነው። በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ መኖሪያ ቤት ማሰራት ጀምረው ነበር።

ከዚያም በኋላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መኖሪያ አድርገውት የነበረ ቢሆንም አራት ዓመታትን ከቆዩ በኋላ አዲስ ወደ ተሰራው ቤት ተዘዋውረዋል።

ይህም ለጉብኝት ክፍት እንደማይደረግ መረጃ እንዳላቸው አርክቴክት ዮሐንስ ነግረውናል።

7ኛ. የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ቤት

መንግሥቱ ኃይለማሪያም ባንድ ወቅት ረዘም ላሉ ቀናት ወደ አውሮፓ አቅንተው ነበር። በዚህ ጊዜ ወዳጆቻቸው እርሳቸው ሲመለሱ ለማስደሰት ለመንግሥቱ አዲስ ቤት ለመስራት ተነጋገረው በጣም በአፋጣኝ ቤት ሰርተውላቸው ነበር። ቤቱ መዋኛ እንደነበርው የሚነገር ሲሆን ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው አርክቴክት ዮሃንስ ገልፀውልናል።

8ኛ. የአንበሶችና ሌሎች እንስሳት ማቆያ

ይህ ሥፍራ በቤተ መንግሥቱ ደቡባዊ አቅጣጫ ይገኛል። በብረት ፍርግርግ የተሠራ ትንሽ የእንስሳት ማቆያ ሲሆን በአሁን ወቅት ምንም ዓይነት እንስሳት አይኖሩበትም። ቀደም ሲል የነበሩት እንስሳት ወደ ሌላ ሥፍራ ተዛውረዋል የሚል መረጃ አለ።

9ኛ. በአጤ ሚኒሊክ ጊዜ የተሠራው የጽህፈት ቤት

በዚህ ቤተ መዛግብት የተለያዩ መረጃዎች ተሰንደው ይገኛሉ። ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተደራጀ ሲሆን ከአፄ ሚኒሊክ ጀምሮ የነበሩ ታሪካዊ ሰነዶች ይገኙበታል። ከትምህርት ሚንስቴር በስተቀር ሌሎች የሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ሰነዶቻቸውን ያስቀምጡበት እንደነበር ይነገራል። የደብዳቤ ልውውጦች፣ የብራና ጽሁፎችና ሌሎች የአገር ውስጥ ጉዳዮች የተሰነዱበት ሲሆን አሁን እድሳት ያልተደረገበትና ጎብኝዎችም ወደዚያ መጠጋትም ሆነ ማየት አይችሉም።

10ኛ. የታችኛው ዙፋን ችሎት

የዙፋን ችሎቱ በቤተ መንግሥቱ ደቡባዊ አቅጣጫ ፊቱን ወደ ሸራተን ሆቴል አቅጣጫ አዙሮ የቆመ ትልቅ ሕንፃ ሲሆን በአጤ ሚኒሊክ ጊዜ የተሰራ ነው።

ከሕንፃው ፊት ለፊት ሰንደቅ ዓላማ መስቀያ ይገኛል። በፊት ለፊቱም ነጋሪት እየተጎሰ፤ እምቢልታ እየተነፋ ትልልቅ የጦርነት አዋጆች የታወጁት ነው።ከዚህም በተጨማሪ ሃገራዊ ጉዳይ የሚነገርበትና የሚታወጅበት አደባባይ አለው።

ሕንፃው ምድር ቤት ያለው ሲሆን ከላይ ያጌጠ አዳራሽ አለው፤ አዳራሹ ውስጥ የዘውድ ምልክት ያለው በሃር ከፋይ የተሰራ ዙፋኑን የሚያጅብ መቀመጫ አለ። መሰብሰቢያ አዳራሽ እና በግራና በቀኝ ሰፋፊ ክፍሎች አሉት።

በደርግ አስተዳዳር ጊዜ የደርግ ምክር ቤት ሆኖ ለረጂም ጊዜ አገልግሏል። የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሹማምንትም በዚሁ ምድር ቤት ታስረው ነበር። የምክር ቤቱ አባላት ከላይኛው ፎቅ ሆነው ‘ይገደሉ አይገደሉ’ የሚል ክርክሮች ይካሄዱበት ነበር- በምድር ቤቱ ደግሞ ሞታቸውን አሊያም ሽረታቸውን የሚጠባበቁ እስረኞች ይህን እየሰሙ ይሳቀቁ እንደነበር ይነገራል።

ምድር ቤቱ ውስጥ አራት ክፍሎች አሉት። በእነዚህ ቤቶች ወፋፍራም የብረት ዘንጎች ያሉ ሲሆን ሰዎች ተሰቅለው ይገረፉበት ነበር ይባላል። አሁን በሙዚየሙ እድሳት እንደ አዳራሽ እንዲጎበኝ ሦስት ነገሮች ታስበዋል።

የደርግ ችሎት የነበረው ኢትዮጵያ ተቀብላቸው የነበሩ ትልልቅ ሰዎች እንደ የዩጎዝላቪያው ቲቶ፣ የፈረንሳዩ ቻርለስ ደጎል፣ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥና የሌሎችም ፎቶ ለዕይታ ተዘጋጅተዋል። በአጤ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ እነዚህ ሰዎች በዚህ አዳራሽ አቀባበል ተደርጎላቸው ስለነበር እነርሱን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ይታዩበታል።

ሌላኛው በደቡባዊ አቅጣጫ የመንግሥታት ታሪኮች ለዕይታ ይቀርብበታል፤ አሁን ላይ ከአፄ ሚኒሊክ ጀምሮ እስከ አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ድረስ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች ፎቶና በእነሱ ዘመን የተሰሩ ሥራዎች ለዕይታ ይቀርባሉ።

በምሥራቃዊው ክፍል አገር የተመሠረተችበት ንግርት (አፈ ታሪክ) አንድ ጠንካራ ማኅበረሰባዊ ሥነ ልቦና የተዋቀረበት ንግርት ይቀርብብታል።

በዚህ አዳራሽ ሰሜናዊ ክፍል ከውጭ የተቀበልናቸውና ሀገር ውስጥ የዳበሩ ኃይማኖቶች ይቀርቡበታል፤ ዋቄ ፈታ ፣ ቤተ አስራኤላውያን ይከተሉት የነበረው የአይሁድ እምነት፣ ከዚያም እስልምና፣ ክርስትና፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት እንዲሁም ሌሎች የክርስትና እምነቶች በተወጠረ ሸራ ላይ በዲጂታል እንዲታዩ ይደረጋል።

ከሕንፃው ወጥተን በደቡባዊ አቅጣጫ ግድግዳው ላይ የብረት ቀለበቶች ይታያሉ፤ እነዚህ ቀለበቶች በዳግማዊ ሚኒሊክ ጊዜ መኳንንቶቻቸው በቅሎዎቻቸውን የሚያስሩበት ቦታ ነበር።

በደርግ ጊዜ ደግሞ ኋላ ላይ የተረሸኑት የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሹማምንት እስረኞች ፀሐይ የሚሞቁበት ቦታ ሆኖም አገልግሏል።

በ1981 በነበረው መፈንቅለ መንግሥት የተሳተፉት 12ቱ ጀኔራሎችም የታሰሩበት ቦታ ነው።

11ኛ. አዲስ እየተሰራ ያለው አኳሪየም እና የእንስሳት ማቆያ

ቦታው ከቤተ መንግሥቱ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን በአፄ ሚኒሊክና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የተጀመረውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በተሻለ መንገድ ለመተግበር አዲስ እየተሰራ ያለ ሥፍራ ነው።

12ኛ. የአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ

ይህ አዳራሽ በጣም ትልቅ አዳራሽ ሲሆን ኪነ ሕንፃው የኢትዮጵያዊያን፣ የአርመናዊያንና የሕንዶች እጅ ያለበት እንደሆነ ይገምታሉ።

የግብር አዳራሹ በግምት 8 ሺህ ሰዎችን ያስተናግዳል ተብሎ ይገመታል፤ በዘመኑ የተለያዩ አገልግሎቶች ያሏቸው በሮች ያሉት ሲሆን በቅርቡም አድሳት ተደርጎለታል።’ገበታ ለሸገር’ የእራት ግብዣ የተካሄደውም በዚሁ አዳራሽ ነው።

13ኛ. ትንሿ ኢትዮጵያ

ይህ ቦታ ቀድሞ ያልነበረና የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሃሳብ ነው። ከአዳራሹ በስተ ደቡብ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ የሃገረሰብ ኪነ ሕንፃ የሚታይበት ሥፍራ ነው። በአሁኑ ሰዓት ብዙ የተሰራ ነገር ባይኖረውም ሥራው ተጀምሯል።

በመጨረሻም

በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚታደሱትና የሚጠገኑትን ቅርሶች በተመለከተ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ያነሳንላቸው አርክቴክት ዮሐንስ “የተሰራው የእድሳት ሥራ የሚያስወቅስ ነው ለማለት እቸገራለሁ፤ ይሁን እንጂ የባለሙያ ተሳትፎና ድጋፍ ቢኖራቸው ከዚህ የተሻለ ማድረግ ይቻል ነበር የሚል እምነት አለኝ፤ ይህንንም በፅሁፍ ለሚመለከተው አቅርቤያለሁ” ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የተደገፈው በአረብ ኢሜሪትስ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት የወጣ ውጪ አለመኖሩን መረጃው እንዳላቸው ገልፀውልናል።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0
Read previous post:
ኢዜማ የፓርቲውን የስራ አስፈፃሚ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)  የፓርቲውን የስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ይፋ አደረገ። በዚሁ መሰረት ሃያ...

Close