«ምርጫ ቦርድ ሊያዘን አይችልም» – የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) መመስረቱን የማሳወቅ ሂደት እንዳልተተገበረ፤ መሰረትን ያሉት ፓርቲዎችም መክሰማቸውን በተመለከተ ፓርቲዎቹ እንዳላሳወቁ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለፀ፡፡

‹‹ምርጫ ቦርድ ሊያዘን አይችልም፤ ፓርቲዎች በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ በጠቅላላ ጉባኤያቸው ወስነው አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ ሆነው ሪፖርት በማቅረባቸው ፓርቲው አዲስ ሆኖ እንዲቋቋም ተደርጓል›› ሲል ኢዜማ አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፤ በመገናኛ ብዙሃን የተገለፁት ራሳቸውን አክሰመው አንድ ፓርቲ ለመመስረት ተሰባስበዋል የተባሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአርበኞች ግንቦት 7፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲና የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ ከስመው ወደ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ተጠቃልለዋል ቢባልም አንድም ፓርቲ ለምርጫ ቦርድ ከስሜያለሁ ብሎ አላሳወቀም፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ መቋቋሙ በመገናኛ ብዙሃን ቢገለፅም፣ ከቦርዱ ፓርቲውን ለማቋቋምና አባላትን ለመመዝገብ ያመች ዘንድ ህጋዊ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው ከመጠየቅ ውጭ እስከአሁን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳልተመዘገበ አማካሪዋ ተናግረዋል፡፡ የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ፓርቲዎች በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ በጠቅላላ ጉባኤያቸው ወስነው አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ ሆነው ሪፖርት በማቅረባቸው ከወረዳ ጀምሮ አባላትን በማዋሃድ ፓርቲው አዲስ ሆኖ እንዲቋቋም ተደርጓል፤ ምርጫ ቦርድ ሊያዝዘን አይችልም፤ ከአሁን በኋላ አባላት የሰማያዊ፣ የኢዴፓ… ተብለው ሳይከፋፈሉ ሁሉም የኢዜማ አባል ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ዶክተር ጫኔ ኢዜማ የመንግሥት ሥራ ውስጥ የፓርቲ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር እንደሚከላከል፤ በኢዜማ በኩል የፓርቲው ሊቀመንበር የፓርቲ ሥራውን ሲሠራ፤ የፓርቲው መሪ ደግሞ መንግሥታዊ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን ፓርቲ እና መንግሥት ተነጣጥለው የሚሠሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህ በሌላው ዓለምም የተለመደ ስለሆነ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ህዝብን ግራ በማያጋባ መልኩ የመንግሥት አደረጃጀት እና የፖለቲካ አደረጃጀት ቁልጭ ብሎ መታወቅ አለበት›› ያሉት ዶክተር ጫኔ፤ ይህንን የፓርቲውን አደረጃጀት በፓርቲያቸው በኩል በወረዳ ደረጃ ሳይቀር እንደዘረጉት አሳውቀዋል፡፡ ተግባሩ የመንግሥት አሠራር በፓርቲ ተፅዕኖ ውስጥ እንዳይገባ ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር እንዲኖር ታስቦ የተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011

ምህረት ሞገስ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የኢትዮጵያ “ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም” ተመስገን ትሩነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *