ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኤርትራ 28ኛ ዓመት ነፃነት ከየት ወደየት?

ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር ስለተደረገው ስምምነት ከኤርትራ በኩል ዝርዝር እንዲነገር ቢጠበቅም ጠብ የሚል ነገር የለም። ብዙዎች ያገራችንን ጉዳይ ለምን ከኢትዮጵያ መሪዎች አፍ እንሰማዋለን የሚል ቅሬታን በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች ገልፀዋል። ካለፈው ወር ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤርትራውያን ‘ይኣክል’ (ይበቃል) በሚል ሕዝባዊ ጥሪ በኤርትራ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖርና የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

BBC Amharic – ኤርትራ ከጣልያንና ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ መሰረት በ1946 ዓ. ም. ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትዋሃድ ተደረገች። በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አፄ ኃይለሥላሴ ፌዴሬሽኑን አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን እንዲፈርስ አደረጉት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንም ሳያማክሩ እንዲሁም የኤርትራ ፓርላማ ይሁንታ ሳይገኝበት ፌዴሬሽኑ መፍረሱ በኤርትራውያን ዘንድ ቅሬታን እንዲሁም ለትጥቅ ትግሉ መነሻ ሆነ። መስከረም 1953 ዓ. ም. የትጥቅ ትግሉ ሀ ተብሎ ተጀመረ።

የትጥቅ ትግሉ ውጤት

በትጥቅ ትግሉ የመጀመሪያ አስር ዓመታት የነበሩት ጥቂት ታጋዮች ሲሆኑ፤ ቀስበቀስ እያደገ ሲመጣ በተፈጠረ መከፋፈል በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩ ጥቂት ታጋዮች ከተሐኤ (ጀብሃ) ተገንጥለው ሕዝባዊ ሓይሊታት’ (ሻዕቢያ) የተሰኘ ቡድን አቋቋሙ።

በወቅቱ ሁለቱም ቡድኖች በሰው ኃይልና ልምድ በመጠናከራቸው፤ የታጋይነት መንፈስና የአመራር ብስለት ተጣምረው አብዛኞቹን የኤርትራ ከተሞች ነጻ ማውጣት ችለው ነበር።

ነገር ግን በ1974 ዓ. ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለገብ ዘመቻ ያካሂዳል። የታሪክ ተንታኞች እንደሚሉት ደርግ እንደ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ከፍተኛ ኃይል አሰልፎ አያውቅም። በዚህም የአየር፣ የምድርና የባህር ኃይሉን ነበር በጋራ ያሰለፈው። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ከተቆጣጠርዋቸው የኤርትራ ከተሞች ወደ ሳህልና ባርካ በረሃዎች ተገፉ።

የደርግ መንግሥት በከፍተኛ ዘመቻ ሻዕቢያም ሆነ ጀብሃ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ቢያደርስም ሁለቱን ቡድኖች ለማጥፋት አልቻለም።

ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ለዓለም ማህበረሰብ የኤርትራ ሕዝብ በሕጋዊ መንገድ የራሱን ዕድል በራስ እንዲወስን ጥሪ ቢያቀርብም ከደርግ በኋላ ተቀባይነት አላገኘም።

ኤርትራ በነፃነት ማግስት

ትግሉ ቀጥሎም በ1983 ዓ. ም. የደርግ ሠራዊት የተደመሰሰ ሲሆን፤ ሻዕቢያ አስመራን እንዲሁም አጋሩ ህወሐት አዲስ አበባን መቆጣጠር ቻሉ። በወቅቱም አዲስ አበባ ላይ የሽግግር መንግሥት ሲቋቋም ኢሳይያስ አፈወርቂ በታዛቢነት ተገኝተው ነበር።

የኤርትራ መንግሥትም ሕዝበ ውሳኔ በማካሄድ በ98.9 በመቶ ኤርትራ በነፃ አገርነት ከዓለም አገሮች ተርታ ተመደበች።

ለሦስት አስርት ዓመታት መራራ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የኤርትራ ሕዝብ በልጆቹ ድል ተደስቶ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ተቋቁሞ በሰላምም ለአገሩ አስተዋፅኦ ለማድረግ ተስፋን ሰነቀ።

በየውጭ አገራቱ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያንም በአዲስ ተስፋና መንፈስ ያላቸውን ሃብት ሰብስበው ወደአገራቸው መትመም ጀመሩ። ነገር ግን ያልታሰበው ሆኖ ጊዜያዊው መንግሥት ከዘረጋቸው የሕግ ማእቀፎች እና ፖሊሲዎች ጋር መስማማት ስላልቻሉ ወደየመጡበት መመለስ ጀመሩ።

ብዙዎቹ ያልጠበቁት ነገር ሆኖ ተስፋ ቢቆርጡም በሽግግር ወቅት እንደዚህ አይነት እንቅፋቶች የተለመዱ ናቸውና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት እስኪቋቋም በትግስት እንጠብቅ ያሉና በተስፋ መኖርን የመረጡትም ብዙ ናቸው።

የኤርትራ ነፃነት ቀን ሲከበርImage copyrightAFP

ከነፃነት በኋላ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጠንካራ ስለነበረ የሁለቱ አገራት ንግድ መሳለጥም ለኤርትራ ሕዝብ አንድ ተስፋ ነበር።

ብዙ ሳይቆይ በዚህ ተስፋቸው ላይ ውሃ ተቸለሰ፤ በቀጣይም ከጂቡቲ፣ ከየመን እንዲሁም ከሱዳን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷ የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንደከተታቸው ተሰማቸው። እንዲሁም በጦርነት የወደመች አገራቸውን እንገነባነለን ብለው 18 ወራት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሲያገለግሉ የነበሩ ወጣቶች መሞትና በከንቱ መባከን የኤርትራን ሕዝብ እጅግ ያስደነገጠ ክስተት ነበር።

በ1994 3ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ ያካሄደው ሻዕቢያ አገራዊ ሸንጎ አቋቁሞ የአገሪቷን ሕገ መንግስት የሚነድፍ ኮሚሽን ማቋቋሙ ጋር ተያይዞ፤ ሕዝቡ ሕገ መንግሥት ተረቆ የፖለቲካ ድርጅቶች ተወዳድረው ፖለቲካዊ ስልጣን የሚጨብጡበት ስርዓት ይገነባል የሚል ተስፋን አንግበው ነበር።

በ1991 ዓ. ም. ኢትዮጵያና ኤርትራ በድምበር ምክንያት ወደጦርነት ገብተው ከመቶ ሺዎች በላይ ሕይወታቸውን ማጣታቸው የብዙ ኤርትራውያንን ተስፋ ያጨለመ ነው።

ምንም እንኳን ጦርነቱ ተቋጭቶ አልጀርስ ላይ ስምምነት ቢፈረምም ሁለቱ አገራት ወደሰላም መምጣት አልቻሉም።

ከጦርነቱ በኋላም ፕሮፌሰር በረከት ኃብተሥላሴን ጨምሮ የኤርትራ ልኂቃን ‘ጂ-13’ የሚባለው ቡድን በርሊን ላይ በመሰባሰብ የኤርትራን መጪ ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ሀሳቦቻቸውን በደብዳቤ ወደፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቢልኩም ፍሬ አላፈራም።

ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ወታደራዊ አመራሮች፣ ጀኔራሎችንና ነባር ታጋዮች የወከለው ‘ጂ-15 የተሰኘው ቡድን በኢትዮጵያና በኤርትራ የተደረገውን ጦርነት ጨምሮ በተለያየ ጉዳዮች ለመመካከር ከፕሬዚዳንቱ ጋር ስብሰባ እንዲደረግ ጠየቁ።

ፕሬዚዳንቱ ምንም ምላሽ ሳይሰጧቸው በኤርትራ ቴሌቪዥን በኩል የቡድኑን ስም የሚያጠለሹ ፕሮፓጋንዳዎች መነዛት ተጀመሩ። በሌላ በኩል ደግሞ የግል ጋዜጦች የነሱን ሃሳብ ደግፈው መፃፍ ጀመሩ። በመጨረሻም በአገር ክህደት ተወንጅለው ቡድኑ ብቻ ሳይሆን የነሱን ሀሳብ የደገፉ ጋዜጠኞች ታሰሩ፤ ጋዜጦቹም ተዘጉ።

እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤትም አልቀረቡም፤ ያሉበትም አይታወቅም። በተለያዩ ጊዜያት ጠባቂዎቻቸው የነበሩና ከኤርትራ የወጡ ሰዎች አብዛኞቹ እስረኞች በበሽታና በንፁህ አየር እጦት ምክንያት እንደሞቱ ቢናገሩም፤ የኤርትራ መንግሥት ግን እስከቅርብ ጊዜ ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ግን የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ ከአንድ የፈረንሳይ ሚድያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ”ሁሉም በሕይወት አሉ። ጤንነታቸው በጥሩ ሁኔታ ይገኛል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የግለሰቦቹ መታሰር በኤርትራ ሕዝብ ዘንድ ጥቁር ጥላ የጣለ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ በአልጀርስ ስምምነት ትግበራ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እምቢተኝነት ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት ሕዝቡን ለመጨቆን እንደመሣሪያነት በመጠቀሙ የኤርትራውያን ሕይወት መራር አድርጎታል ብለው የሚተቹ ብዙዎች ናቸው።

የኤርትራ ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሲባል ብሔራዊ ወታደራዊ አገልግሎት መሳተፍ አለባችሁ ተብለው በግድ የተጋዙ፤ በሰላም ሠርተው መኖር ያልቻሉ ወጣት ኤርትራውያን እግራቸው እንዳመራቸው ስደትን መርጠው ሳይሆን ተገደው መንጎድ ጀመሩ።

ስደቱ እግር በግር ሳይሆን በውሃ ጥም፣ በሰሃራና በሲናይ ሽፍቶች የገደሏቸው፤ ባህር ውጦ ያስቀራቸው ኤርትራውያንን ቤቱ ይቁጠራቸው።

ጭቆናውና የመብት ጥሰቱ በመብዛቱ ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ኤርትራ ውስጥ ተፈጸመ የተባለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚመረምር ልዩ ቡድን አቋቋመ። ነገር ግን ቡድኑ ኤርትራ ውስጥ ገብቶ የማጣራቱን ሥራ እንዲሠራ የኤርትራ መንግስት ባለመፍቀዱ፤ ሦስት አባላት ያሉት መርማሪ ኮሚሽን አቋቋመ።

ኮሚሽኑ ከሁለት ዓመታት ምርመራ በኋላ የደረሰበት እንደሚያሳየው፤ በኤርትራ ውስጥ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙንና፤ ጥሰቱን የፈጸሙ የኤርትራ ባለስልጣናት ወደፍርድ ቀርበው እንዲጠየቁ ውሳኔ አቀረበ።

የኤርትራ መንግሥት ግን ከእውነት የራቀና ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለው እና የኤርትራ መንግሥትን ለማዳከም የተጎነጎነ ሴራ ነው ሲል ውሳኔውን ውድቅ አድርጎታል።

የኤርትራ ነፃነት በአል አከባበርImage copyrightALEXIS ORAND/GETTY IMEES

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ለኤርትራውያን ምን አመጣ?

በዚሁ ሁኔታ ላይ እንዳለ ባለፈው ዓመት ኢህአዴግ የአልጀርስ ስምምነቱን ያለቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበሉት በመግለጽ ከኤርትራ ጋር እርቅ ማውረድ እንደሚፈልጉ ውሳኔ ላይ ደረሱ።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስም በምላሹ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ የሚገመግም ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ ገለጹ። በቀጣይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በደማቅ አቀባበል አስመራ ገቡ፤ በዚህም የጥላቻ ግንቦች በፍቅር ፈረሱ። ተነፋፍቀው የነበሩ ቤተሰቦችና ሕዝቦች ተገናኙ፤ ሰላምም ተበሰረ፤ ብዙዎችም ደስታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው በእንባ ሲታጠቡ ነበር።

የሁለቱ አገራት መሪዎች የንግድ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን እንደተፈራረሙ መግለጫ መሰጠት ተጀመረ። ለአስርት ዓመታት ተዘግተው የነበሩት የሁለቱ አገራት ድንበሮችም ተከፈቱ። ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላም እነዚሁ ድንበሮች ተዘጉ።

ከእርቀ ሰላም በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳደረጉት፤ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ በፖለቲካዊ እይታ ምክንያት ከተራራቁዋቸው ኤርትራውያን ጋር አብረው እንዲሠሩ፣ የረቀቀው ሕገ መንግሥት እንዲተገበር፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ አሠራር እንዲተገበር ቢጠበቅም አንዳች ተስፋ የሚሰጥ ነገር አልታየም።

ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር ስለተደረገው ስምምነት ከኤርትራ በኩል ዝርዝር እንዲነገር ቢጠበቅም ጠብ የሚል ነገር የለም። ብዙዎች ያገራችንን ጉዳይ ለምን ከኢትዮጵያ መሪዎች አፍ እንሰማዋለን የሚል ቅሬታን በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች ገልፀዋል።

ካለፈው ወር ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤርትራውያን ‘ይኣክል’ (ይበቃል) በሚል ሕዝባዊ ጥሪ በኤርትራ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖርና የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

የዘንድሮውም 28ኛ የነፃነት በአል በኤርትራውያን ዘንድ ዝብርቅርቅ ባለ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው የሚከበረው።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ ዶላር ተያዘ
0Shares
0
Read previous post:
በሺህ የሚቆጠሩ አጭበርብረዋል የተባሉ የስራ አፈላላጊ ኤጀንሲዎች ታገዱ፤ የሚከሰሱ አሉ

ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙትን ኤጀንሲዎች ሽሽት በርካቶች ለስደትና ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል። የዛጎል አዘጋጅ ቀደም ሲል ባለው...

Close