“Our true nationality is mankind.”H.G.

‹‹የራሷ ቋንቋና ፊደል ያላት አፍሪካዊት ሃገር እያለችን ከቅኝ ገዥዎቻችን ቋንቋ ተውሰን ቻርተሩን መፈረም የለብንም፡፡›› የጊኒው ፕሬዝዳንት ሴክቱሬ

ዕለቱን በታሪክ!

 

ተግባሩ በታሪክ ማህደር ውስጥ ዘመን እንዳይሽረው ሆኖ ከተፈፀመ ልክ ዛሬ 56ኛ ዓመቱን ደፈነ።

ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም በአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ አይረሴው የአፍሪካውያን ታሪክ ተፃፈ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ድካም በኋላ ተሳክቶላቸው በነጻነት አርማቸው አዲስ አበባ የተሰባሰቡት 32ቱ ነፃ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ከግንቦት 14 እስከ 17 ቀን 1955 ዓ.ም ከመከሩ በኋላ ባለ 33 አንቀጹን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ አፀደቁ፡፡

በዕለቱም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ላይ ዕውን ሆነ፡፡ ያች ቀን ለአፍሪካ አህጉር አዲስ የድል ምዕራፍን አበሰረች፡፡ ለአፍሪካዊያንም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ተከፈተ፡፡ ያኔ አፍሪካዊያን መሪዎች የባርነት ቀንበርን በተባበረ ክንዳቸው ከትከሻቸው ሊያወርዱ ተማማሉ፡፡

በወቅቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ አፍሪካዊያን በደስታ ስሜት የሚጠብቁት፣ የመላው ዓለም ሕዝብ በቅርበት የሚከታተለው ጉባኤ፣ ከ500 በላይ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ጋዜጠኞች የሚሽቀዳደሙበት ውሳኔ እና በብዙ ሺህ ሕዝብ ዘንድ በቴሌቪዥን መስኮት የሚጠበቀው የ32ቱ ነጻ የአፍሪካ መንግስታት መሪዎች ጉባኤ ግንቦት 14 ቀን 1955 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነበር የተጀመረው፡፡

Related stories   ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች

የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመራጭ ሊቀ መንበር ኢትዮጵያዊው ንጉሰ ነገስት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ የሊቀ መንበርነት ምርጫቸው በሙሉ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ ረዘም ያለና ቀልብን ያዥ ንግግር ለጉባኤው አቀረቡ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀ መንበር ንግግር እንደተጠናቀቀም የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ተብማን እና የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አቦድ ተራ በተራ እየተነሱ ንግግራቸውን በአዳራሹ ለተሰባሰበው ጉባኤተኛ፣ ልዩ መልእክተኛ እና በቴሌቪዥን መስኮት ለሚጠባበቀው የዓለም ሕዝብ አደረሱ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ከአሜሪካ እስከ ሩሲያ፣ ከህንድ አስከ ምዕራብ ጀርመን ያሉ ሀገራት መሪዎች የመልካም ምኞት እና የደስታ መልዕክቶች ተስተጋቡ፡፡ በወቅቱ አሜሪካን በፕሬዝዳንትነት በመምራት ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በላኩት መልዕክታቸው እንዲህ አሉ ‹‹የእኔን እና የአሜሪካን መንግስት መልካም ምኞት ለእናንተ የአፍሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ለመግለጽ እድል ስለገጠመኝ ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ አፍሪካ ያለማቋረጥ ነፃነትን እና አንድነትን ለመጎናፀፍ የምታደርገው እርምጃ ለሰው ልጅ ክብርና ራስን ለማወቅ የሚደረገው ተጋድሎ ዋናው ክፍል ነው፡፡ አሜሪካ እና ሕዝቧ ስራችሁን ስትጀምሩ የተቃና ውጤት እንድታገኙ ይመኙላችኋል፡፡››

Related stories   “አቡነ ማቲያስ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም”

የመሪዎቹን ንግግር ለዓለም ዐይንና ጆሮ እንዲያደርስ አደራ የተባለው የያኔው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአሁኑ ኢቢሲ የብኩርና ስራውን ለሕዝብ አስተጋባ፡፡ ለአራት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ማጠናቀቂያ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ደግሞ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች በኢትዮጵያዊያን የተዘጋጀው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረቻ ረቂቅ ቻርተር ጉባኤተኛው ተወያይቶ እንዲያፀድቀው ቀረበ፡፡ ነገር ግን የጉባኤው መድረክ መሪ እና የወቅቱ የጊኒ ፕሬዝዳንት ሴኩ ቱሬ አዲስ ሃሳብ አቀረቡ፤ ‹‹የራሷ ቋንቋና ፊደል ያላት አፍሪካዊት ሃገር እያለችን ከቅኝ ገዥዎቻችን ቋንቋ ተውሰን ቻርተሩን መፈረም የለብንም›› የሚል፡፡

ሃሳቡም ተቀባይነትን አገኘና በጸኃፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ መሪነት ዶክተር ምናሴ ለማ፣ አቶ ማሞ ታደሰ፣ ክቡር አቶ ታደሰ ያዕቆብ፣ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩና በሌሎች ሚኒስትሮች ርብርብ በአንድ ሌሊት ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተረጎመ፡፡

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

የወቅቱ የግብፅ መሪ የነበሩት ጋማል አብደል ናስር አረበኛ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት የሚናገሩት ቋንቋ በመሆኑ ለምን በአረበኛም አይዘጋጅም በሚል ያቀረቡት ሃሳብ ብዙ ቢያከራክርም በመጨረሻ ይሁንታን አግኝቶ በአራት ቋንቋዎች የተተየበው እና በ33 አንቀፆች የተዋቀረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር በሙሉ ድምጽ ፀደቀ። በ36ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ በአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሰነድ እስኪተካ ድረስም አገልግሎት ላይ ቆዬ፡፡

ኢትዮጵያም ከሕዝቦቿ እስከ መሪዎቿ፤ ከቋንቋዋ እስከ ሰንደቋ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ አፍሪካ ህብረት ምስረታ ለአፍሪካዊያን መዲናና ተምሳሌት እንደሆነች ቀጥላለች፡፡

ምንጭ፡- የአፍሪካ ኅብረት ድረ ገፅ እና የኤርምያስ ጉልላት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እና ፓን-አፍሪካኒዝም መጽሐፍ

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0