«በ1999 ዓ.ም የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅቱ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ዳይሬክተር ነበሩ፤ እኛን ካገኙን በኋላ በጊዜው የሰራነውን በሚገባ አይተው ሥራው ተቋማዊ እንዲሆን እገዛ አደረጉልን፡፡ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመነጋገርም ለተሞክሮ ወደ ዱባይ እንድንሄድ አደረጉን፡፡ ዱባይ ሄደን አገሪቷ ያለችበትን የእድገት ደረጃ እና ዓለም እንዴት እንደሚኖር በአእምሯችሁ ቀርፃችሁ መጥታችሁ ይህን ሥራችሁን ወደተግባር ትቀይራላችሁ የሚል ሃሳብ ሰጡን፡፡…» የሚሉት ሸህ አብዱልሀሚድ አህመድ ናቸው፡፡

ሸህ አብዱልሀሚድ በቅርቡ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የኡላማ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ እኚህ አባት በጅማ ከተማ በሻሻ ከተማ ውስጥበሃይማኖት ሳቢያ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ከሌሎች የእምነት አባቶች ጋር በመሆን ችግሩን የፈቱበት ተሞክሮና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ

አዲስ ዘመን፡– እስልምና ሃይማኖት በርካታ እሴቶች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ እሴቶች ውስጥ የመቻቻል፣ አብሮ በጋራ የመኖር እናየመተባበር እሴቱ እንዴት ይገለፃል?

ሸህ አብዱልሀሚድ:- የእስልምና ሃይማኖት ከሌሎች እምነት አጋሮች ጋር አብሮ እንዴት መኖር እንዳለበት ግልፅ ሃይማኖታዊ አስተምህሮት አሉት፡፡ በተለይ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር እንዴት አብሮ መኖር እንዳለብን መጀመሪያ ከቁርዓን እንማራለን፡፡ በዚህ ረገድ ዋና መሠረታችን ቁርዓን ነው፡፡ ቀጥሎ የነብዩ መሐመድ አሊየሰላት ወሰላም ሀዲስ ነው፡፡

ነብዩ መሐመድ መዲና ከተማ ኖረው ነው ወደ አኺራ የሄዱት፡፡ በመዲና ከተማ ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት የሰማያዊ እምነት ተከታዮች፣ አለል ኪታቦች የመፅሀፉ ባለቤቶች አብረው አንድ ላይ ይኖሩ ነበር፡፡ አይሁድ፣ ክርስቲያን እና ሙስሊሞች አንድ ላይ ይኖራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ መነሻችን፡፡ ሁለተኛው እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስናይ የነብዩ መሐመድ ሰሀቦች/ባልደረቦች/ እዚህ አገራቸው በሰላም መኖር አቅቷቸው ሃይማኖታቸውን ማስኬድና ማስፋፋት ተቸግረው የተሰደዱት ወደ እኛ ሀገር ኢትዮጵያ ነው፡፡ በወቅቱ የሀበሻ ንጉስ የሚባለው ነጃሺ ክርስቲያን ነው፤ አማኝ ነው፡፡ በመሆኑም ‹እዚህ ሀገር ላይ አትበደሉም› በሚል በትክክል ማስተዳደር የሚችል ዳኛ ነው፡፡ በዚህም ወደ እሱ እንዲሸሹ አድርገዋል፡፡ ከዚህም በኋላ መጥተው አብረው ኖረዋል፡፡

እናም አብሮ መኖር በዚህ ዘመን የተጀመረ አይደለም፡፡ በቀደምት ዘመን ጀምሮ የመጣ ነው፡፡ አዲስ አይደለም፡፡ አንዱ ቤት ሙስሊም ከሆነ ግድግዳው ወይም ጎረቤት የክርስቲያን እምነት ተከታይ ነው፡፡ ስለዚህ በሠርጉም፣በደስታውም ሆነ በኀዘኑና በበዓላት ጭምር በመጠያየቁም በእያንዳንዱ የሕይወት ሂደቶች ውስጥ አብረን ስንኖር የነበርን ሰዎች ነን፡፡ ይህ አሁንም በዚህ ትውልድ መቀጠል አለበት፡፡

በቁርዓን ላይ ‹ለሙስሊሙ ይበልጥ ቅርብ ሆነው የምታገኛቸው ክርስቲያን ወገኖቻችሁ ናቸው› ይላል፡፡ እነዚያ ቄሶች ቀሳውስቶች ነን የሚሉት ሰዎች ይበልጥ ለሙስሊሞች ቅርብ ሆነውና ፍቅር ርህራሄ ኖሯቸው እንደዘለቁ አላህ በቁርዓን ገልጾልናል፡፡

አዲስ ዘመን፡– በእርስዎ እይታ ይህ ዘመናት የተሻገረው የአብሮነት እሴታችን አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ይላሉ?

ሸህ አብዱልሀሚድ:- ከቅርብ ዓመታት ውስጥ አብዛኛው ሁኔታችን ሆድና ጀርባ የመሆን ባህሪ በግልፅ ይታያል፡፡ በእርግጥ የፖለቲካው ምህዳር መስፋት በራሱ ይህን ችግር ለመፍጠሩ እንደ አንድ ምክንያት ሊነሳ ቢችልም በሰዎች መካከል ግን አሁን አሁን የሚታየው መስተጋብር ችግር ያለበት ነው፡፡ ሰው ወደ ግል እምነት በማግነን የእኔ ይበልጣል የሚል የከረረ ነገር ውስጥ የገባበት ሁኔታና ወቅት እንገኛለን፡፡ ይህ በፊት ከነበረው ለየት ያለ ነው፡፡

ይህ በእርግጥ አገራችን ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ ያለች በመሆኗ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጭ አገር የትምህርት ዕድል አግኝተው የሚሄዱ ምሁራን የሄዱበትን አገር ባህል ቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ በቀጥታ በማምጣት ተፅእኖ የሚፈጥሩ አሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን ከሄዱበት አገር ይዘው ሊመጡ የሚገባቸው ጉዳይ እውቀቱን ብቻ መሆን ሲገባቸው እዛ ጋር ያለውን የእምነት ተፅዕኖ ቀጥታ እዚህ አገር ላይ አሳርፋለሁ በሚሉበት ወቅት መለያየት ወይም ሆድና ጀርባ መሆን አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ሁኔታዎችን እየቀያየረ እየተስፋፋ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡

ከዚህ ቀደም ኢስላም ክርስቲያኑም በጋራ ባቋቋሙት እድር ውስጥ የተቸገረ መርዳት፣ የታመመ መጠየቅ ይህን አልፎም ሰውየው ወደ ፈጣሪው ከሄደ/ከሞተ/ አንድ ላይ ሆኖ በኀዘን መሸኘት በስፋት ነበር፡፡ አሁን ይህ ለእየቅል እየሆነ ነው፡፡ አሁን አብዛኛው በጋራ ከመኖር ይልቅ የግል ጉዳዩን እያስከበረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ በግልፅ ይታያል፡፡ ጥሩም አይደለም፡፡

ለአብነት በተለያዩ የትራንስፖርት አውታሮች ላይ ስትሳፈር አንዱ የሌላውን ሞራል የአለመጠበቅ ዓይነት ሁኔታ ይታያል፡፡ ሙስሊም ሹፌር ከሆነ ቁርዓን እና መንዙማ ሲከፍት ሌላው ወገን ላይስማማው ይችላል፡፡ በሌላ ሁኔታ ደግሞ ሹፌሩ ክርስቲያን ሆኖ ከተገኘ የክርስቲያን መዝሙር ይከፍታል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ቅሬታ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህን መሰል ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም የተለያዩ እምነቶችን ለማስተላለፍ በቲሸርት ጭምር መልዕክቶች ይተላለፋሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ በማህበራዊ ሚዲያ ሳይቀር አላስፈላጊ መልዕክት ያላቸው ሃሳቦች ይተላለፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ድሮ ከነበረው የተለዩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ቅሬታዎችን እና መለያየቶችን እያመጡ ያሉ ይመስለኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡– እነዚህን ወቅታዊ ችግሮች ለማስተካከል ቤተ እምነቶች በጋራም ሆነ በተናጠል ምን እየሰራችሁ ነው?

ሸህ አብዱልሀሚድ:- እንደገለፅከው እንደ የግል ቤተ እምነታችን በተለይም ደግሞ በእስልምና ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር ተሳስረን እንዴት መኖር እንዳለብን መጽሔቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ለዚህም በሰበካ ላይ ምዕመናኑ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር እንዴት አብረው መኖር አለባቸው፣እንዴትስ በጋራ አገር በማልማት ጭምር ይሰራሉ፡፡ እዚህ ላይ ምንም እንኳ ቀኖናችን የተለያየ ቢሆንም፣መጽሐፋችን ለእየቅል ቢሆንም በአብሮነት ላይ፣ መቻቻል፣የተቸገሩትን በመርዳት ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሰራ በጋራ የተቀረፀ ነገር አለ፡፡

በመሆኑም የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከአዲሱ አመራር አራት አባላት ወደ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ልኳል፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ በአገሪቷ የፖለቲካ፣ የድህነት አንዱ አንዱን የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ ነዋሪው ቀዬውን ለቆ እንዲወጣ የሚፈፀሙ ተግባራትን በአጠቃላይ ለማስቀረት ሰባት ቤተ እምነቶችን አቅፎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም እኛም ቦታ ወይም ድርሻ አለን፡፡ በጉባኤው የበላይ ጠባቂያችን ሀጂ ሙፍቲ ናቸው፡፡

ጉባኤው ሁኔታውን በትክክል ማስረዳት የሚችል ሆኖ እስልምና ከሌሎች የእምነት ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን አብሮ መኖር እንዴት እንዳለበት በሚገባ እየሰራን እንገኛለን፡፡ የሃይማኖት ጉባኤው የዱባይን ምርጥ ተሞክሮ በሚገባ ለመውሰድ አስቧል፡፡ ዱባይ በቅርብ ጊዜ ያደገች አገር ናት፡፡ ይቺ አገር የሁሉንም ቤተ እምነት መብት ጠብቃ በኢኮኖሚው በኩል ሕዝቦች ዱባይ መጥተው አገሪቱን እንዲያሳድጉ የተደረገውን ሁኔታ እንድናይ ያደርገናል፡፡

ከእስልምና እምነት ተከታይ ከሆኑ አገራት ውስጥ ዱባይን ከዚህ ውጭ ደግሞ አሜሪካንን በተሞክሮ ለመውሰድ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ አሜሪካ ከተለያዩ አገራት በዲቪ ጭምር ከዓለም በመውሰድ የእነዚህን የተለያዩ አገራት ዜጎች አእምሮ በመጠቀም አገሪቱ ሀብታም እንድትሆን ያደረገው ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ እኛም በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም የሚያጣላን ነገር የለም፡፡

ቅዱስ ቁርዓን ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አብራችሁ መስራት አትችሉም የሚል አንቀፅ በውስጡ የለም፡፡ ይልቁኑ ቁርዓን ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞቻችን ጋር አብረን እንድንሰራ እና እንድንኖር ብዙ ፈርጀ ብዙ አንቀፆች አሉ፡፡ በዚህ ላይ በስፋት ለመስራት ቤተ እምነ ታችን በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡– ይህን የተባረከ ሥራ ለመስራት የሌሎች ቤተ እምነቶች እና የመንግሥት የድጋፍ እና ቀናኢነት እንዴት ይገልፁታል?

ሸህ አብዱልሀሚድ:- ይህን ሥራ ከዚህ በፊት መስራት የጀመርነው ጅማ ነው፡፡ እዚያ በወቅቱ የነበሩት ቤተ እምነቶች አምስት ነበሩ፡ይህን ሥራ ስንሰራ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ሃሳባችን ለሰላም እና ተያያዥ ሥራዎች በመሆኑ በገንዘብ ይደግፈን ነበር፡፡ በዚህም የቢሮ ዕቃዎችን አሟልቶ በሰላምና በመቻቻል ላይ እንድንሰራ ብዙ ረድቶናል፡፡ ሥራችንም ፍሬ ባፈራ ወቅት ሰብዓዊ መብት የሰላም አምባሳደር አድርጎ ሹመት ሰጥቶናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሃይማኖት ተቋማት ለሦስት ዓመት ከዩ.ኤስ.አይ.ዲ ጋር በመፈራረም ባደረገልን የገንዘብ ድጋፍ የሴቶችን እና ወጣቶችን የሰላም ሚና ግንባታ በሚል በጅማ አካባቢ ሰርተን አምስቱም ቤተ እምነቶች በስፖርታዊ ሥራዎች ላይ ማሊያም ኳስም ገዝተን ስለሰላም ስንሰብክ ውጤታማ ሆነን እዚህ ደርሰናል፡፡

በአሁን ወቅት በእየቤተ እምነቶች የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የለም፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት እንደሚያስፈልገው ያውቃል፡፡ መንግሥት ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ የማይፈታውን ነገር የሃይማኖት አባቶች መፍታት እንደሚችሉ በትክክል ያረጋገጠበት ሁኔታ ስላለ ያለ ጣልቃ ገብነት በቅንነት ድጋፍ እያደረገልን ይገኛል፡፡ በዚህም ቤተ እምነቶች ራሳችንን ችለን በአገሪቱ ብዙ ሥራ እንድንሰራ ከጎናችን ቆሞ ይገ ኛል፡፡

ሌሎች ቤተ እምነቶች ለዚህ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ቀናኢ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የሁሉም ቤተ እምነቶች አስተምህሮ ይህን አብሮ አገርን ማልማትና ሰላም ላይ አብሮ መስራት አይከለክልም፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ቤተ እምነት አብሮ ለመስራት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡን ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ብዙ ምሳሌዎች ቢኖሩም የጅማውን ልንገርህ፡፡

ጅማ ላይ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች የመቃብር ቦታ የላቸውም ነበር፡፡ እየጠየቀላቸው የነበረው ሙስሊሙና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ በዚህም ጥረታችን መካነ መቃብር ቦታ አሰጥተናቸዋል፡፡ የእኛ አጀንዳ መቃብር ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ኃይል ኖሮን ወደ መንግሥት እንድንቀርብ አድርጎናል፡፡ ስለዚህ ይህ ይበልጥ መበረታታት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መልክ አብረን መስራት ከቻልን ነው እድገቷም ሆነ ሰላሟ ሊቀጥል የሚችለው፡፡ ይህን በዚህ መልክ ካልሰራን ትውልዱ ይበላሻል፡፡

አዲስ ዘመን፡– የሰላም አምባሳደር የሆኑበት መልካም ሥራና ተሞክሮ ቢያጫውቱን?

ሸህ አብዱልሀሚድ:- ጅማ ውስጥ ሦስት ቤተ እምነቶች ላይ በአመራርነት ስንሰራ ነበር፡፡ ቀሲስ ሊቀትጉሀን ታጋይ ታደለ ይባላሉ፤ በአሁኑ ወቅት መጋቢ ዘሪሁን የሥራ መልቀቂያ አስገብተው /ተሸኝተው/ ርክክብ አድርገዋል፡፡ መጋቢ ፓስተር ታምራት እኚህ አባት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ ሸህ አብዱልሀሚድ አህመድ አንድ ላይ ሆነን ጅማ ላይ ስንሰራ ነበር፡፡

የተገናኘነው በአጋጣሚ በሻሻ በምትባል ከተማ በሙስሊም እና በክርስቲያን መካከል አለመግባባቶች ተፈጥረው በተፈፀመው ግጭት ቤተክርስቲያን ሳይቀር ተቃጠለ፤ የአንድ ቄስ ሕይወትም አለፈ፡፡ ይህ በሚከሰትበት ወቅት እጅግ በጣም አፈርን፡፡ በተግባሩም አንገታችንን ደፋን፡፡ የአካባቢያችን እና የከተማችን ገፅታ ተበላሸ፡፡ ከተማም ስንመጣ እናፍር ጀመር፡፡

shki abdulhamid

ይህን እንዴት መስበር አለብን በሚል ሦስታችንም ተስማማን፡፡ ሦስታችንም እዛው ተወልደን ያደግን በመሆናችን ችግር አልሆነብንም፡፡ በወቅቱ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ተለያይቶ ነበር የሚሄደው፡፡ የከተማው ሕዝብ እኛን እንዲያይ በካፍቴሪያ እየገባን አንድ ላይ ስንጠቀም ማህበረሰቡ እንዲያይ አደረግን፡፡ ‹እነዚህ ሰዎች አብረው እየሄዱ ነው፤ ሦስቱም የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎች ሆነው አንድ ላይ እየተጓዙ ነው ያሉት› ብለው ሲሉ የነበረውን ገፅታ ለመቀየር ጥረት አደረግን፡፡ በአንድ ሞተር ሳይክል በአንድ ባጃጅ በአንድ መኪና እየተጓጓዝን በተለያዩ የእምነት ቦታዎች ሳይቀር እየተገኘን በፀሎት በመክፈትና በፀሎት በመዝጋት አብረን በመመራረቅ ልዩ ሥራ ሰራን፡፡

ከዚህ ሥራችን በኋላ በ1999 ዓ.ም የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅቱ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ዳይሬክተር ነበሩ፤ እኛን ካገኙን በኋላ በጊዜው የሰራነውን በሚገባ ካዩ በኋላ ሥራው በሙሉ ተቋማዊ እንዲሆን እገዛ አደረጉልን፡፡ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመነጋገር ወደ ዱባይ እንድንሄድ አደረጉን፡፡ ዱባይ ሄደን አገሪቷ ያለችበትን የእድገት ደረጃ እና ዓለም እንዴት እንደሚኖር በአእምሯችሁ ቀርፃችሁ መጥታችሁ ይህን ሥራችሁን ወደተግባር ትቀይራላችሁ የሚል ሃሳብ ሰጡን፡፡

በዚህም መሰረት ለ14 ቀናት ዱባይ ጉብኝት እንድንሄድ ካደረጉን በኋላ ሥራችንን ያማከለ አንድ መፅሔት ታዘጋጃላችሁ ብለውን ስለነበር «ፍቅር ልቆ ሲታይ» የሚል መፅሔት በ2003 ዓ.ም ታተመ፡፡ መፅሐፉ ሲታተም ለመጀመሪያ ጊዜ እጅ ለእጅ ተያይዘን በተነሳነው ፎቶ የመፅሔቱ ሽፋን ሆኖ ሦስት ቤተ እምነቶች ፅሑፍ አቅርበን ዶክተር አብይ አንብበው በሚገባ ገምግመው የትኛውንም እምነት ተከታይ የማይነካ መሆኑ ስለተረጋገጠ መታተም ይችላል በማለት ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠይቀው እንዲታተም አድርገውልናል፡፡

መፅሔቱ ከታተመ በኋላ ሕዝብ ጋር እንዲደርስ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሃይማኖቶቹን ምክንያት አድርገው ሊመጡ የነበሩ ችግሮችን ማስቀረት ቻልን፡፡ ሰው ውስጥ የነበረውን ዝምታ መስበር የቻልነው በእኛ መቀራረብ ነው፡፡

በእምነት ጉዳይ አንዳንድ ችግሮች ይከሰቱ ነበር፡፡ ሙስሊም እና ክርስቲያን በአንዲት ስንዝር መሬት በግል ጥቅም ይጋጩና አንዱ ሲሸነፍ ወደ ሃይማኖት ይቀይረዋል፡፡ አጀንዳውን ወደ ሃይማኖት ይለውጠዋል፡፡ ካጋጠሙን ውስጥ አንድ ሸቀጥ ነጋዴ ከአዲስ አበባ ሙሉ የመፅሐፍ ቅዱስ ለህትመት የተዘጋጀ ደላሎች ሽጠውለት ለሸቀጥ ጠቅልሎ እያሸገ እንዲሸጥበት አደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቆማ ደረሰን፡፡ ያን ጥቆማ ይዘን በመሄድ ግለሰቡን ስንጠይቀው እኔ አላወኩም አላስተዋልኩም አለን፡፡ ሁኔታውን ካስረዳነው በኋላ ነጋዴው ተደናግጦና በጉዳዩ አዝኖ መፅሐፉን በኪሳራ መለሰው፡፡ በወቅቱ ሰውዬውንም ሆነ ሁኔታውን ሳናጋልጥ ፈታነው፡፡

ይህ ትልቁ ትምህርት እጃችን ላይ ያለው መስጊዱ ላይም ሆነ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማይኩም ሆነ ሌላው የሕዝብ መድረክ በእጃችን ነው ያለው፡፡ ሕዝብን ስሜታዊ አድርገን ወደ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ መክተት እኛው ጋር ነው ያለው፤ ሕዝቡንም ደግሞ ወደ ሰላም ለማስገባት በእጃችን ስላለ እና መድረኩም ለሃይማኖት አባት በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት ተጠያቂ ነው፡፡ በፈጣሪም ዘንድ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሰው መጨፋጨፍ የለበትም፡፡

ሰዎች ከትምህርት ቤት አንድ አጀንዳ ይዘው ቢመጡ ዩኒቨርሲቲና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ሊበርዙ እንደሆነ ሲገለጽልን ችግሩን ለመፍታት በጋራ እንሰራለን፡፡ በዚህም መሠረት የፖሊስን እና የአቃቢ ሕግ ሥራ እናቃልላለን፡፡ እንደ እኛው ቤተ እምነቶቹ ሳይራራቁ አብረው መስራት ከቻሉ አገሪቱ ውስጥ ያሉ የደም መፋሰስ በማስቀረት መንግሥትንና ሀገርን መርዳት ይቻ ላል፡፡

አዲስ ዘመን፡– አሁን እየተከሰቱ ካሉ አገራዊ ችግሮች አኳያ ለመንግሥት አመራሮች እና ለምዕመኑ ምን የሚያስተላልፉት መል ዕክት አለ?

ሸህ አብዱልሀሚድ:- አሁን ያሉት አመራር በግልም የምናውቃቸው ናቸው፡ እንዲያ መሰግኑንም ሳይሆን በዕድሜያችን ከደረስንበት መንግሥት አኳያ በተለይ የእምነት አባቶች በአንድ እምነት ውስጥ ሆነው ሁለት ጎራ የተከፈሉ ቤተ እምነቶች ይበዙ ነበር፡፡ አንድ እምነት ግን በተለያዩ አጀንዳዎች ለሁለት ተከፍለው ነበር፡፡ አንዳንዴ የሞተ ሰው አስክሬን እንኳ እዚያ መስጂድ ውሰዱት፤ አይደለም እዚያኛው ውሰዱት እየተባለ የሚንገላታበት ጊዜ አልፏል፡፡ ይህ ወቅት የሚያሳፍር ነበር፡፡

በኦርቶዶክስም ሆነ በሙስሊሙ ሁለት ጎራ ተከፍሎ ነበር፡፡ እነዚህ ቤተ እምነቶች የራሳቸውን የውስጥ ችግር ችለው አንድ ሆነው ሁለንተናዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ነው ከመንግሥት ያለው አቋም እና ድጋፍ፡፡ ይህ ከእኛ መሆን ነበረበት፤ መንግሥት እንዲህ ብሎ መለመን አልነበረበትም፡፡ ጥሩ እይታ አለው፤ ደም መፍሰስ የማይፈልግ በመሆኑ ከመንግሥት ጎን ሆነን መርዳት አለብን፡፡

ስለዚህ ሁለት ጎራ የነበረውን አንድ በማድ ረግ እዚህ ደረጃ ላይ እንድንመጣ አድርጎ ናል፡፡ አመራሩ ይህ አንድ የሆነ አመራር መጀመሪያ መግባባት አለበት፡፡ ስለዚህ ሕዝበ ሙስሊሙ የሚፈልገውን በአንድ ድምፅ መመለስ አለ በት፡፡ የሃይማኖት አመራሩ ወደ ሕዝቡ ከመውረዱ በፊት መጀመሪያ መግባባት አለበት፡፡ መከፋፈል የለበትም፡፡ በዘርም ሆነ በጥቅም መለያየት ሳይሆን አንድ መሆን አለ በት፡፡ በአካባቢና በቀበሌ መለያየት የለብንም፡፡ እዚህ ላይ ኃላፊነት አለ ብን፡፡

ሁላችንም የተስማማነውን ነው ወደ ሕዝቡ ማውረድ ያለብን፡፡ እንደ መንግሥት ደግሞ አሁን የጀመረውን መንገድ መቀጠል መቻል አለበት ዴሞክራሲን በጣም አስፍቷል፡፡ ለእምነት አባቶች ደግሞ ቅድመ ሁኔታ ሳይቀመጥ (ሳንሱር ሳይኖር) የፈለግነውን መናገር እንድንችል፡፡ ከዚህ በኋላ ሰላይም እንደሌለብን ሰፋ አድርጎልናል፡፡ ይሄን ማስቀጠል መቻል አለበት፡፡እኛ ደግሞ ይሄን መብት አግኝተናል ብለን ያልሆነ ነገር ወስደን ሕዝቡ ውስጥ መጫን የለብንም፡፡ ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር፣ ሕፃናት ከቀያቸው እንዳይፈናቀሉ፣ ትምህርት እንዳያቋርጡ ሴቶች እንዳይደፈሩ፣ አረጋውያን ከቀያቸው እንዳይፈናቀሉ፣ ሕዝቡን አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር መስራት መቻል አለብን፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን አንድነት አስቀጥላለሁ ብሏል፡፡ ሁሉም የራሱን ቋንቋና ባህል ማሳደግ መብት ሆኖ ነገር ግን ስለኢትዮጵያ አንድነት እንዲያስብ በመንደር ውስጥ ወደታች ወርዶ እንድነትን በሚገባ ማስተማር ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡

ለአመራር የማስተላልፈው መልዕክት የታሰሩ ትን መፍታት፣ ሰውን ያለመግደል፣ ሰው የጎደለው ነገር ካለ በሰላማዊ መንገድ በሥርዓት እንዲጠይቅ መገፋፋት እንዲሁም በሰላማዊ ሰለፍ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እና የሚቻለውን ነገር ይቻላል፡፡ የማይቻለውን ደግሞ ለመፍታት ጊዜ እንዲሰጠው ማሳወቅ ነው፡፡ ሌላው ምርጫ በሚቃረብበት ጊዜ ግልጽ የሆነ አሠራር ሰፍኖ ሰው የፈለገውን እንዲመርጥና በትክክል የመረጠው ሰው በፓርላማ ላይ ስለእርሱ እና ስለልማቱ እንዲናገርለት መደረግ እንዳለበት ነው መልዕክቱ፡፡

የእምነት ተከታዮቻችን አንደኛ እርስ በእርሳችን መዋደድ፣ ከራሳችን ቤተእምነት አልፈን የሌላውንም ቤተእምነት መብት መጠበቅ ይገባል፡፡ አንዳንድ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በጠረጴዛ ዙሪያ ቤተእምነቶቹ መፍታት እና ወግ ባህል ማሳደግ መቻል አለብን፡፡ አንዳንድ የማህበራዊ ድረገጽ መልዕክቶች ወይም ደግሞ ውጭ ሀገር ተምረው የውጭ ሀገር ዓላማ ይዘው መጥተው ሊያጣሉንና ሊያለያዩን ለሚፈልጉ አጀንዳ መክፈት የለብንም፡፡

የዚህ የጾም ወቅት የተከበረ ወር ነው፡፡ከእስልምና ማዕዘናት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሙስሊሞች ጀምበር ጎህ ከቀደደ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ በጾም ያሳልፋሉ፡፡ ምሽትና ሌሊት ላይ ደግሞ ለአምላካቸው ጸሎት በማድረግ ይቆማሉ፡፡ ይሄ የግል ነው፡፡

ስለዚህ ምን ማድረግ አለባቸው የተቸገሩና የታመሙ ሰዎችን፣ወላጅ አልባ ሕፃናትን በማብላትና ለትምህርታቸው ከዘካ ላይ ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ በመስጠት ኅብረተሰቡን መርዳት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም የተለያየን ሕዝብ ከሚያገናኝ፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ፣ ጎረቤት ሀገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ካደረገ መንግሥት ጎን በመቆም በገንዘብ፣በሃሳብና በተለያየ ነገር መደገፍ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011

ሀብታሙ ስጦታው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *