በስምምነቱ 200 ሚሊየን ዶላሩ ለታዳሽ ሃይል ማሻሻያ ፕሮግራም የሚውል ሲሆን፥ 350 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል የሚውል ነው። ከዚህ ውስጥ 270 ሚሊየን ዶላሩ ድጋፍ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ብድር ነው።

በሃይሉ ዘርፍ የተደረገው 200 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ መንግስት በሃይል ዘርፍ ለሚያከናውነው የማሻሻያ ፕሮግራምና በታዳሽ ሃይል የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ለሚያከናውነው ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ነው ተብሏል።

ድጋፉም በሃገሪቱ እየተካሄዱ ካሉ የሃይድሮ ፓወር ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች ባለፈ፥ ከፀሃይና ነፋስ 1 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት ለሚካሄደው ፕሮጀክት ይውላል። ከዚህ በተጨማሪም በሃይሉ ዘርፍ የግሉን ሴክተር አቅም ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛልም ነው ያለው ባንኩ።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ፕሮግራሙ፥ በዘርፉ ለሚሰማሩ የግሉ ዘርፍ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ፈሰስ ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከሃይሉ ዘርፍ ባለፈም የአርብቶ አደሮችን ህይዎት ለማሻሻል የሚያስችል የ350 ሚሊየን ዶላር ብድርና ድጋፍም አጽድቋል።

ከዚህ ውስጥ 70 ሚሊየን ዶላሩ እርዳታ ቀሪው ደግሞ ብድር ሲሆን፥ የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ህይዎት ለማሻሻል እንደሚውል ተገልጿል።

ስምምነቱ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ የሆኑና በዝቅተኛ አካባቢዎች የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

የአርብቶ አደሮችን የአየር ንብረት ተጋላጭነት በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ፣ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ቅድሚያ የሚሰጧቸውን አካባቢያዊ የልማት ፕሮግራሞች በመለየትና በማስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የፕሮግራሙ አካል መሆኑን፥ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ገልጸዋል።

ምርታማነትን ማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር፣ የልማት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንዲሁም ተጠቃሚዎችን እንደ አፈርና ውሃ እቀባ ባሉ የአካባቢ ጥበቃዎች ላይ ማሳተፍም የፕሮግራሙ አካል ነው ብለዋል።

ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖና ተጎጅነት በመቀነስ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እና መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም ፕሮግራሙ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ዘመናዊ አሰራርን ተደራሽ በማድረግና የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ፥ በአምራችና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የገበያ ትስስር ማሳደግ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

(ኤፍ ቢ ሲ) 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *