የተወደዳችሁ የሲዳማ ሕዝብ ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ ለፊቼ ጫምባላላ በዓል አደረሳችሁ -እንኳን አብሮ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡

ክቡራትና ክቡራን!!

የሲዳማ ሕዝብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ቀመር፣ “ወንሾ አምቦን” የመሰሉ የእርቅና የሽምግልና ስርዓት “ሉዋን” የመሰሉ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ስርዓት እና ሌሎች የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት የሆነ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች በዙሪያው አቅፎ የያዘ ሕዝብ ነው፡፡

የሲዳማዎች የዘመን መለዋጫ ፍቼ ጫምባላላ ዘመን ከዘመን የሚለዋወጥበት ዕለት ብቻ ሳይሆን ፋይዳው ብዙ የሆነ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ፍቼ ጫምባላላ ጉዱማሌ ላይ መገናኛ፣ መተጫጫ፣ መመራረቂያ፣መተሳሰቢያ፣የወደፊት ተስፋ መሰነቂያ፣ ከአንደበት ክፉ ቃል የማይወጣበት ፣እንስሳቱ ሳይቀር ከሰው እኩል የሚከበሩበት ፣እንግዳ የሚከበርበት፣ ትውድል የሚዘከርበት፣ለሀገር የሚበጀው ሁሉ የሚከወንበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ በድጋሜ በእኔ እና በመላው የኦሮሞ ሕዝብ ስም እንኳን ለዚህ ታላቅ በዓል አደረሳችሁ- አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡

ሁላችሁም እንደምታውቁት የሲዳማ እና የኦሮሞ ሕዝብ በመልካ- ምድራዊ አቀማምጥ ብቻ ሳይሆን በጋራ የአብሮነት ታሪክ፣ ዘመናትን በተሻገሩ ማህበራዊ፣ስነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ያሏቸው የተዋለዱ፣በፍቅር የተጋመዱ በተለያየ ቦታ የሚኖሩ-ግን ተነጣጥለው የማይታዩ ፤ አንዱ ከሌላው ጋር በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተዋደው- ፈቅደው ብሎም ተከባብረው በቋንቋ ተግባብተውና መስተጋብር ፈጥረው ለዚህ የደረሱ ጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ አንድነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡

Related stories   በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

የሲዳማ እና የኦሮሞ ሕዝብ ለመከፋፈል ግፋ ሲልም በወሰን አካባቢዎች ግጭት በማስነሳት እና ጦር በማማዘዝ በሁለቱ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ቅራኔ ለማኖር ሲሰራ የኖረውን ሴራ በተባበረ ክንድ በማክሸፍ፣ግጭቶቹን በማብረድ፣ቅራኔዎችን በሽምግልና በመፍታት እንደታሰበው ሳንለያይ እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር በመቀጠል ከታሰበለን በላይ የምናስብ ሕዝቦች መሆናችንን በተግባር አሳይተናል፡፡ ይሄም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የምናከብረው የፍቼ ጫምባላላ በዓል ከሀገራችን አልፎ የዓለም ሀብት ለመሆን ችሏል፡፡ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት ፍቼ ጫምባላላ በዩኒስኮ የማይዳሰሱ የዓለማችን ቅርሶች አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ የሲዲማ ሕዝብ እና ከሲዳማ ሕዝብ የወጡ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ መላው ኢትዮጵያዊ ከዳር ዳር በነቂስ ተንቀሳቀሷል፡፡ ከዚህም አንዱ ሕዝብ የአንዱን እሴት አምኖ ተቀብሎ እና ተደምሮ፣ በአንድነት ሲንቀሳቀስ ምን ያህል ውጤት ማምጣት..የቱን ያህል ፍሬ ማፍራት እንደሚችል ተመረንበታናል፡፡

Related stories   “በአጣዬ እና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ኮማንድ ፖስቱ

የ ፍቼ ጫምበላላ ባለው ታሪካዊ ባሕላዊና ድንቅ ይዘቱ አገራችንን ወክሎ የአለማችን ቅርስ እንዲሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በጋራ በመደመር እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በጋራ ተደምሮ የሚያከብረው በዓል እና የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሕብረት የአሸናፊነት ምልክት ጭምር ነው፡፡ ሁላችንም ስንተባበር እናሸንፋለን፡፡

በአንድ ላይ ስንቆም እናተርፋለን፡፡ በጋራ ስንታይ እንደምቃለን፡፡ ያለፈውን በይቅርታ ዘግተን መጪውን በፍቅር ስንሻገር ደግሞ ለትውልድ ቂምና ጥላቻን ባለማውረስ ታላቅ ገድልን እንፈጽማለን ማለት ነው፡፡

በሲዳማ ባሕል መሠረት በፍቼ ጫምበላላ በዓል በመጀመሪያው ዕለት የሚከበረዉ የፍቼ ስነስርዓት ሁሉም በየቤቱ በሀሴት ተሞልቶ ቡርሳሜ እና ሻፈታ እየበላና እየጠጣ ብሎም በዚህ ልዩ ቀን ባለፈው በአሮጌው ዓመት የተጣላ ሰው ይቅር ተባብሎ በመታረቅ ቂምን አስወግዶ በጋራ በአዲስ መንፈስ አዲሱን ዓመት በመናፈቅ ነው፡፡ የሲዳማዎች የዘመን መለዋጫ ፍቼ ጫምባላላ በዓል አሃዱ ብሎ የሚጀምረው በይቅርታ እና ዕርቅ መሆኑ ሲዳማዎች ለይቅርታ፣ ለእርቅ፣ ለፍቅር እና ለሰላም የሚሰጡትን ከፍተኛ ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም እንደ ሀገር ለተጀመረው “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር” ጉልበት ሆኖ የሚያገለግል ታላቅ ጉልበት ነው፡፡ ይህን የይቅርታ እና የዕርቅ ትዊፊት በቀን እና በአካባቢ ሳንወስንው ከሌሎች ሕዝቦች ጋርም በመጋራትም ፣በማጋራትም ለሀገር በሚበጅ መልኩ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

በቀጣይም ከራሳችን ነባር ዕውቀቶች ት/ት በመቅሰምም በሚያለያዩን.’.ማነህ ? ..ወዴት ነህ ?’ከሚያባብሉን ጉዳዮች ወጥተን እንደ ፍቼ ጫምባላል አንድነታችን በሚያጠናክሩ፣ አብሮነታችን በሚያስተሳስሩ ፣ከዞን፣ከክልልእና ከሀገር አልፈው በዓለም አደባባይ ስሞቻችንን በሚያስጠሩን የማንነት መገለጫዎቻችን፣ ዕሴቶቻችንና ባህላዊ መሰረቶቻችን ላይ ወገባችንን አሰርን በተባበረ ክንድ በመስራት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ዕውን እናደርግ ዘንድ ጥሬየን አቀርባለሁ፡፡አይዴ ጫምባላላ!!አመሰግናለሁ፡፡

ሽመልስ አብዲሳ

የኦሮምያ ብ/ክ/መ ምክትል/ ር/ መስተዳድ ር

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *