ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የቻይናው ሁጂያን ግሩፕ ፋብሪካዎቹን በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲተከል ስምምነት ተፈረመ

የቻይናው ሁጂያን ግሩፕ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የማምረቻ ፋብሪካዎቹን እንዲተክል የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈረመ።

በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካኝነት የኢንድስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ሁጂያን ግሩፕ መካከል ነው ስምምነቱ የተፈረመው።

ስምምነቱን የኢንዱሰትሪ ፓርኮች ልማክ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ እና የሁጂያን ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዣንግ ሁዋሮንግ ናቸው የተፈራረሙት።

በዚህ ስምምነት መሰረትም ኩባንያው 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሚሆን ካፒታል በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ፋብሪካዎቹን ያለማል። ኩባንያው በፓርኩ ውስጥ የጫማ እና የግንባታ እቃዎች ማምረቻዎችን እንዲሁም፥ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ይተክላል።

በተለይም የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካው 40 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ እንደሚያርፍ ነው በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተመለከተው። ፋብሪካዎቹ ወደ ስራ ሲገቡም ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድልን ይፈጥራል ተብሏል።

1 ነጥብ 5 ሚሊየን ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ61 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተገንብቶ ባለፈው ህዳር ወር ላይ ነበር የተመረቀው።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)