የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሀገሪቱ ለሚገኙ 16 ባንኮች 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አከፋፍሏል። መንግስት ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲከሰትም ሆነ ለሌላ አላማ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በኩል የውጭ ምንዛሬን ገበያ ውስጥ ሲያስገባ ቆይቷል።

ለዚህ አላማ ማስፈጸሚያ ሲባልም የውጭ ምንዛሬውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ወደ ገበያ የሚያስገባው በፖሊሲ ማስፈጸሚያ ባንክ በኩል ብቻ ነው።

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ግን ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለግል ባንኮች ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ዘርፎችና ለሌሎች ጉዳዮች ለደንበኞቻቸው እንዲያቀርቡ የውጭ ምንዛሬን አቅርቧል።

ብሄራዊ ባንኩ በሀገሪቱ ላሉ 16 ባንኮች 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲያከፋፍል እንደየባንኮቹ ቁመና የተለያዩ መስፈርቶችን ተጠቅሟል።

ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ የተከፋፈለው የውጭ ምንዛሬ በግል ባንኮች ዘንድ እንደ በጎ ጅምር ሲወሰድ ለብሄራዊ ባንኩም አድናቆትን አስችሯል።

የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ ብሄራዊ ባንኩ ካከፋፈለው የውጭ ምንዛሬ ውስጥ ዳሽን ባንክ 15 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደደረሰው ተናግረዋል።

አሁን ላይ የታየው ጅምር በጎ ነው የሚሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው 100 ሚሊየን ዶላሩ ሀገሪቱ ውስጥ ላለው የምንዛሬ ችግር አጥጋቢ መልስ ባይሰጥም ለግል ባንኮች ጥሩ እይታ መጀመሩን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር የቦርድ ሊቀመንበርና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሀባ እርምጃው በጎ ጅምር መሆኑን ጠቅሰው፥ ለባንኩ ዘርፍም በጎ እይታ እየመጣ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ይላሉ።

ለ16 የግል ባንኮች 100 ሚሊየን ዶላር የተከፋፈለበት መንገድም ባንኮች ያላቸውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ያሰለፏቸውን ደንበኞች ብዛትን በዋናነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በማዕከላዊ ባንኩ የሚደረገው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ለመንግስት የፖሊሲ ባንክ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ በግል ባንኮች ላይ ብዙ ችግር ሲያስከትል ታይቷል፥ አዲሱ ጅምርም ለግል ባንኮቹ መልካም ነገርን ይዞ መጥቷል።

የግል ባንኮቹ ደንበኞቻቸው ከውጭ ማምጣት ለሚፈልጉት እቃ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ለምንዛሬው ተመጣጣኝ የኢትዮጵያ ብር ማስገባት ስለሚኖርባቸው፥ በግል ባንኮቹ ያስቀመጡትን ቁጠባ በሙሉ ያወጡት እንደነበር ይገልጻሉ።

ይህም በግል ባንኮች ላይ የገንዘብ እጥረትን እየፈጠረ ለቆጣቢዎቻቸው ገንዘብ መስጠት የተቸገሩባቸው ጊዜዎች ላይ አድርሷቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።

የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው፥ መንግስት የውጭ ምንዛሬ የሚያቀርብበት መንገድ አንድ ብቻ ስለነበር ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር ያነሳሉ።

ነባሩ የውጭ ምንዛሬ አለቃቀቅ ባልተገባ ሁኔታ የግል ባንኮችን የሚጎዳ እንደነበር በተደጋጋሚ ስንናገር ነበር የሚሉት ደግሞ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ናቸው።

ወደ አንድ አቅጣጫ ባዘነበለ መልኩ የውጭ ምንዛሬን መልቀቁም ውድድርን በአገልግሎት ሳይሆን በሌላ መንገድ የገበያ አሸናፊነትን የፈጠረ በመሆኑ ተገቢ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ለፖሊሲ ባንክ ብቻ የውጭ ምንዛሬ ተሰጥቶ የግል ባንክ ደንበኞች ለዚሁ ምንዛሬ ገንዘባቸውን አውጥተው ወደዛው ባንክ ባመሩ ጊዜ፥ የግል ባንኮች ባጋጠማቸው የተቀማጭ ገንዘብ እጥረት ምክንያት መልሰው ከብሄራዊ ባንክ የሶስት ወር ጊዜ ብድር እስከመውሰድ ደርሰዋል።

ይህም ቢሆን ከፍ ባለ ወለድ ስለነበር ሌላ ጫና እንደነበረውም አቶ አስፋው ያስረዳሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ አሁን ላይ ተመሳሳይ ችግር ሳይፈጠር ደንበኞቻቸው በአንድ ጊዜ ገንዘባቸውን እንዳያወጡ መደረጉ እጅግ አበረታችና በጎ ጅምር ነው።

ባለፉት አመታት በሀገሪቱ በኢኮኖሚ መስክ ከመጡ ለውጦች ውስጥ የግል ባንኮችም የራሳቸው አሻራ ያለበት መሆኑ ታውቆ የተጀመሩ ስራዎች ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።

አሁን በብሄራዊ ባንክ የተወሰደው እርምጃ በባንኮች ገበያ ላይ ሊኖር የሚችልን የአጭር ጊዜ መዛባት ሊያስቀር ቢችልም፥ በዋናነት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ግን አይታመንም።

ከዚህ አንጻርም ለውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር፥ የወጪ ንግዱ የገቢ ንግድን ብቻ እንዲያግዝ ያደረገ አዝማሚያ ስላለው ራሱን እንደ ዘርፍ አድርጎ በመውሰድ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ሊመቻቹለት ይገባል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አዲሱ ሀባም የችግሩን ዘላቂ መፍትሄ በተጠና መልኩ መፍታት አሁንም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ባይ ናቸው።

(ኤፍ ቢ ሲ)

በካሳዬ ወልዴ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *