የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በፈተና ውስጥ የማለፍና የዳበረ የአማራር ልምዱን ተጠቅሞ በክልሉ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር በመቋቋም ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ በቁጭት እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው በወቅታዊ የክልሉ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመው ግድያ ፓርቲውን፣ የአማራ ክልል እና የኢትዮጵያን ህዝብ ክፉኛ የጎዳ ነው፡፡

በተለይም አመራሮቹ የመምራት ክህሎትን ያዳበሩ፣ የተሻለ የሥራ ትጋት፣ እውቀትና ልምድ ያላቸው እንዲሁም የህዝብ ችግር የሚያንገበግባቸው  የነበሩ መሆናቸው የጉዳት መጠኑን ከፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ችግሩ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በህዝብ ዘንድ መደናገር እንዳይፈጠር ጉዳዩን ግልጽ የማድረግ፣ የማረጋጋትና  በድርጊቱ የተሳተፉ ወንጀለኞችን የመያዝ ስራዎች እየተሰራ መሆኑንም አቶ ዮሐንስ  ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው ያለው አመራርም የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል የማወያየት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁንም ከአምስት ሺህ በላይ አመራሮችን ለማወያየት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

“በውይይቱም በአመራሩ ዘንድ እልህ፣ ቁጭትና ወኔ ተፈጥሯል” ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ በተሻለ ጥንካሬ በመሰራቱ ወንጀለኞችን በፍጥነት ለህግ ለማቅረብ እንዳስቻለ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ በፍጥነት ሰላምና መረጋጋት በማስፈን የመደበኛ ልማት ሥራዎች በተለመደው አግባብ መከናወን እንዲቀጥሉ መደረጉን ነው የገለጹት።

“የተፈፀመው የጥፋት ድርጊት የአማራን ህዝብ ጥያቄ የሚመለስ ሳይሆን አዴፓን የማጥፋት ብሎም ክልሉን የትርምስ ቀጠና የማድረግ ዓላማ ያለው ነው” ብለዋል።

ለክልሉ ተቆርቋሪ በመምሰል የህዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዳያገኙ የማደናቀፍ አጀንዳ የያዙ አካላት እድሉ የተዘጋ መሆኑንም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

የአማራን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ አዴፓ አቋም ይዞ እየሰራ ባለበት ሁኔታ ከፊሉ አመራር ለክልሉ ተቆርቋሪ ከፊሉ ደግሞ የማይቆረቆር ተደርጎ እየቀረበ ያለው ሃሳብ ፍፁም የተሳሳተ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንዳሉት በህዝቡ ጥያቄና ተጠቃሚነት ላይ በአመራሩ መካከል ተመሳሳይ አመለካከትና አቋም ተይዞ እየተሰራ ነው።

“አዴፓ የአማራን ህዝብ ችግር ለመፍታት በፈተና ውስጥ ያለፈና ጠንካራ ታጋዮችን ከጎኑ እያጣ በጥንካሬ ዛሬ ላይ የደረሰ የበሳል አመራር እጥረት የሌለበት ፓርቲ ነው” ሲሉም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

በመሪዎቹ ላይ የደረሰው ያልታሰበ የሞት አደጋ ሁሉንም ያሳዘነ ቢሆንም የእነሱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ  እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የፓርቲውን ውስጣዊ አንድነት ከመጠበቅ ባለፈ የቀደመ የአመራር ብስለቱን ተጠቅሞ ለውጡ ግቡን እንዲመታ በተሻለ ጥንካሬ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል።

በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ ለውጡን አያደናቅፈውም ያሉት ኃላፊው፣ አዴፓ የህዝቡን የቆዩና ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በእልህና በተቆርቋሪነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የገጠመውን ወቅታዊ ፈተና በብቃት ለመሻገርም ወጣቱ፣ ምሁራን፣ የመንግስት  ሠራተኛውና መላው የአማራ ህዝብ ከፓርቲው ጎን በመቆም ሊደግፍ እንደሚገባ   ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ENA

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *