የአንድ ሰው ማንነት የተገነባው ከቤተሰቡ ጠባብ ክበብ ካስተዋላቸው ወይንም ከወረሳቸው ባህርያት፣ ከአካባቢ ማኀበረሰብ ከቀሰማቸው ልምምዶች፣ ከሚኖርበት ሰፊ ኅብረተሰብ ከተማራቸው ዕውቀቶችና ጥበቦች፣ ከአድማስ ማዶ ያለው ዓለም ካበረከተለት የዕውቀትና የክህሎት ተሞክሮና ግኝቶች ከተቀዱ ምንጮች ነው፡፡

ኅብሩ የሰመረው የተፈጥሮ ክስተት፣ የባህሉ፣ የወጉና የልማዱ ውበት፣ የተወለደበት ወይንም የኖረበት ቋንቋዎች መስተጋብር፣ የሃይማኖቱና የዕምነቱ ብርታት፣ ደስታውና ሃዘኑ የተገለጠባቸው የሕይወቱ ውጣ ውረዶች፣ የቀረፀው የትምህርት ሥርዓትና ሀገሩ ያለፈችበት የዘመናት የታሪክ ጉዞ ወዘተ… እነዚህ ሁሉ ግብዓቶች ያንን አንድ ዜጋ ይቀርፁትና ማንነቱን ያበጁለታል፡፡ እርሱ ከሌላው፣ ሌላውም ሰው ከእርሱ መለየቱን ወይንም መመሳሰሉን ያረጋግጡለታል፣ በመተባበር ያኖሩታል፣ ለክፉ ካዋለውም ለግጭት ሊዳርጉት ይችላሉ፡፡

የሀገር ዳር ድንበር ታጥሮ ሉዓላዊነት የሚከበረው፣ የሥልጣኔ ብርሃን በሀገር አድማስ ላይ ቦግ ብሎ የሚፈካው፣ ለዘመናት የተጣባን የድህነት እድፍና የቡቱቷችንን ክንብንብ ከራሳችን ራስ ላይ ለማውለቅና የእኔነትን ስግብግብ ባህርይ ለማራገፍ የሚቻለው በዋናነት የግልን “የአርበኝነት ተግባር” መፈፀም ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ቅድሚያ ለወገኔ አሰኝቶ ከራስ በፊት ሕዝብን አስቀድሞ ግለኝነትን በመስዋዕት ማቅረቢያ መሰዊያ ላይ ለማስቀመጥ ዜጋውን የሚያደፋፍረው ያ አንድ መሠረታዊ ማብላያና ቅመም በዘርፈ ብዙ መገለጫዎች የሚተነተነው የሀገር ወዳድ ዜጎች የአርበኝነት ወኔና መንፈስ ነው፡፡

የአርበኝነት ፅንሰ ሃሳብና የቃሉ ጥንተ አመጣጥ

አርበኛ (Patriot) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘው “አባት ሀገር” ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል ሲሆን የቃሉ ሥረ መሠረት ደግሞ የግሪክ (የጥንታዊ ፅርዕ) ቋንቋ ነው፡፡ አርበኛም ሆነ አርበኝነት (Patriotism) በመዝገበ ቃላት ውስጥ ተካቶ በስፋት አገልግሎት ላይ የዋለውና በእንግሊዝ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ ሰርፆ ሊገባ የቻለው የኤልሳቤጣዊያን ክፍለ ዘመን (Elizabethan Era, 1558 – 1603) እየተባለ “በወርቃማነቱ” በሚንቆለጳጰሰው ዘመን ነበር፡፡ ይህ ዘመን እንግሊዝ በሥልጣኔዋ ታላቅነት በዓለም ፊት ቁንጮ ሆና ለመታየት ከሌሎቸ ሀገራት ጋር ፉክክር ውስጥ የገባችበት፣ የተራቀቁ የኪነ ጥበባትና የሥነ ጥበባት ሥራዎች የተስፋፉበት፣ ዊሊያም ሼክስፒርን የመሳሰሉ አስደማሚ የሥነ ጽሑፍ ልሂቃን የገነኑበት፣ ስፖርታዊ ጨዋታዎች የደመቁበት፣ ኢኮኖሚያቸው የተነቃቃበት፤ በአጠቃላይም “በእንግሊዝ ፀሐይ አትጠልቅም” የሚለው የተስፋፊነትና የእኔ እበልጣለሁነት ፍልስፍና ያቆጠቆጠበት ዘመን ነበር

ከኤልሳቤጣዊው ዘመን ቀደም ብለው አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አዳዲስ ቅኝ ግዛቶችን ለመያዝና ለመቀራመት በአሳሾቻቸው አማካይነት ዓለምን ዳር እስከ ዳር ያሰሱበትን ዘመናት በቁጭት በማስታወስም ፊት ቀዳሚ ለመሆን እንግሊዝ ተጠናክራ የተነሳችነበት ዘመን ነበር፡፡ ለምሳሌ፤ ከኤልሳቤጣዊው ዘመን ቀደም ብሎ ቫስኮ ዳጋማን (1460–1524) እና ፈርዲናንድ ማጂላንን (1480 – 1521) የመሳሰሉ ፖርቹጋላውያን አሳሾች የመርከቦቻቸውን መልህቅ ነቅለው በአጥናፈ ምድር ውቂያኖሶች ላይ እየቀዘፉ ሀገራትን የበረበሩበት፣ ለቅኝ ግዛት ተስፋፊዎችም በሩን ወለል አድርገው የከፈቱበት ወቅትም ነበር፡፡ የፖርቹጋላዊው የቫስኮ ዳጋማ ልጅ (እ.አ.አ 1516 – 1542) ክርስቶፎል ዳጋማ 400 ስልጡን ወታደሮችን እየመራ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በኦቶማን ኢምፓየር ተደግፎ ሀገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ያመሳቀላትን የኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋዚ (በተለምዶ አህመድ ግራኝ እየተባለ የሚጠራውን) ለመመከት ለዓፄ ገላውዲዎስ የድረሱልን ጥሪ ምላሽ በመስጠት አጋርነቱን አረጋግጧል፡፡

በዚያን መሰሉ ቅድመ ኤልሳቤጣዊ ዘመን ቀዳሚዎቹ የአውሮፓ አሳሾችና የቅኝ ግዛት ተስፋፊዎች የነበራቸው ዝናና ገናናነት እንግሊዝን እረፍት ነስቷት ስለነበር፤ እርሷም በተራዋ ኩራቷን በይበልጥ ለማግነን በመሻት “Patriot, Patriotism” የሚሉት ቃላት በሕዝቧ ውስጥ ሰርፀው ይበልጥ እየተዋወቁ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴአቸው ውስጥ ሁነኛ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ያደረገችበት ወቅት ነበር፡፡ ለታላቋ እንግሊዝ ኩራትና ልዕልና፣ በጦር ሜዳ ፍልሚያም ሆነ በተለያዩ ሌሎች የኪነ ጥበባትና የሥነ ጥበባት፣ የንግድና የሃይማኖት ዘርፎች ግንባር ቀደም ለሆኑት ልሂቃን አርበኞቿ “Partiot” የሚለውን ክብርና ሽልማት በስፋት በመስጠት የሀገራቸውን ገናንነት እንዲያፋጥኑ ወኔአቸውንና ሞራላቸውን በማነሳሳት ዜጎቿ የታላቋ እንግሊዝ ታላላቅ አርበኞች መሆናቸውን በስፋት ማስተማር ጀመረች፡፡

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው አርበኝነት (Patriotism) የሚለው ፅንሰ ሃሳብ የጦር ሜዳ ድል አድራጊነትን አካቶና ከፍ ብሎ ለሀገርና ለወገን በኪነ/ሥነ ጥበባት፣ በእርሻ፣ በንግድና በኢንዱስትሪ ወዘተ… ዘርፎች ተሰማርተው ፋይዳ ያለው ውጤት ላስመዘገቡ ዜጎች የአርበኝነት ክብር መሰጠት የተጀመረው፡፡

“አርበኝነት” የሚለው ፅንሰ ሃሳብ እያደር ለብዙ የዕውቀት ዘርፎች ልሂቃን የመወያያ አጀንዳ እየሆነ በልዩ ልዩ ገፅታዎቹም መተንተኑ አልቀረም፡፡ አንዳንድ የፍልስፍና ጠቢባን አርበኝነትን የሚተነትኑት ከብሔረተኝነት ጋር በማነፃፀር ነው፡፡

ለምሳሌ፤ ጆርጅ ኦርዌል የተባለው ታላቅ ደራሲ “አርበኝነት ለአንድ ውስን ሁኔታዎችና የሕይወት እንቅስቃሴ ከልብ መሰጠት ነው፡፡ ይህ መሰጠት ደግሞ በዓለም ላይ እንደዚህ የተሻለ ጉዳይ አይኖርም ብሎ እስከ ማሰብ ያደርሳል፡፡ ይህ ጠንካራ እምነት ከራስ መሰጠት ባለፈ በሌላው ላይ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚያነሳሳም አስረግጦ ይገልፃል፡፡ እንደ ኦርዌል አገላለጽ አርበኝነት በባህሪው ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊም ሆነ ባህላዊ ጥቃትን የመከላከል ጠንካራ እምነት እንደሆንም አስረግጦ ይገልጻል፡፡

ጀርመናዊው ማርክስ ደግሞ በወዛደራዊ ዓለም አቀፍነት መርህ መሠረት፤ “ዓለም የሠርቶ አደሩ” ስለሆነች በውስን ድንበር ተከልሎ ከሚገለፅ አርበኝነትን የማቀንቀን ስሜት ሠራተኛው መደብ ነፃ ሆኖ የዓለም ማኅበረሰብ አንድ አካል እንደሆነ ማመን አለበት የሚል ፍልስፍናውን አስተዋውቋል፡፡ ትሮቲስኪና አለን ውድስን የመሳሰሉ ልሂቃንም ይህንን የማርክስን ተመሳሳይ ፍልስፍና በማቀንቀን “ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት የሀገሮችን ድንበር በማፍረስ ከጨቋኞች ብዝበዛ ነፃ የሆነ አንድ ብሩህ ሶሻሊስታዊ ዓለም መፍጠር ነው” በማለት በክልል የሚወሰን አርበኝነትን በመፃረር ተሟግተዋል፡፡

ለትውስታ ያህል “ያ ትውልድ” እየተባለ የሚጠቀሰው የ1960ዎቹ የሀገራችን ወጣት አብዮተኛ ትውልድ “እንደነ ሆቺሚን እንደ ቼጉቬራ!” እያለ ይዘምር የነበረው ያንን ዓለም አቀፋዊ የኮሚዩኒዝም ፍልስፍና ለመግለጥ ጭምር ይመስላል፡፡

አርበኝነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በሀገራችን የተዋወቀበት ወቅትና ዐውድ

አርበኝነት “Patritotism” ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ መተዋወቅ እንደጀመረ የሚታመነው በዓፄ ዐምደ ጽዮን ዘመን (1314 – 1344 ዓ.ም) እንደሆነ ግምት አለ፡፡ ለግምቱ ማጠናከሪያ የሆነውም ንጉሡ የመንግሥቱን ግዛት ለማስፋፋት ከአካባቢ ሀገራትና ኃይላት ጋር ጦርነት እየከፈተ ወደፊት በሚገፋበት ወቅት “ሐርበኛ” እያለ በግጥም ይሞካሽ ነበር ወይንም ራሱን ያሞካሽ ነበር፡፡ በታሪክ ተመዝግቦ በሚገኘውና እርሱን በሚያሞግሰው ዘለግ ባለ ግጥም ውስጥ “ሐርበኛ ዐምደ ጽዮን፣ መላላሽ የወሰን፣ ውá እንደ ወሰን . . . ምን ቀረሽ በወሰን . . .” የሚለው ሃሳብ በስፋት ተጠቅሷል፡፡

ይህ ግጥም በኮሌጅ ደረጃ ለመማሪያነት የሚያገለግል ሲሆን በሥነ ጽሑፍ ምሁራን ዘንድም አማርኛ ቋንቋ ለሥነ ጽሑፍ ቋንቋነት ማገልገል የጀመረበት ዘመን እንደሆነ ግምታቸውን ይሰጣሉ:: ከዚህ እውነታ የምንረዳው የኤልሳቤጣዊያን ዘመን አርበኝነትን (Patriotism) በስፋት ከመተዋወቁ ሁለት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ቃሉ በእኛ ቋንቋ ዐውድ ውስጥ አገልግሎት ላይ ውሎ እንደነበር ነው፡፡

አርበኝነት “Patriotism” በዋናነት የዲፕሎማሲና የጦር ሜዳ አሸናፊነትን በማስተዋወቅ በሀገራችን ተዘውትሮ መገለፅ የጀመረው ከ1888ቱ የዐድዋ ድል በኋላ ቢሆንም፤ በዘርፈ ብዙ አገልግሎቱ አርበኛ ወይንም አርበኝነት በስፋት አገልግሎት ላይ እንደዋለ የሚታመነው ግን በአምስቱ ዓመታት የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት (ከ1928 – 1933 ዓ.ም) እና ከዚያም በኋላ ባሉት ዓመታት እንደሆነ በአንዳንድ ጥናቶች ውስጥ ተመልክቷል፡፡

ይሄው አርበኝነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በሀገራችን ትርጉሙን እያሰፋ በመሄድ ለብዙ ጉዳዮች በገላጭነት መዋል ከጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ “አርበኝነት” ማለት በአንድ ታሪካዊ ወቅትና ጊዜ የአንድን ሉዓላዊ ሀገር ክብር በመዳፈር ድንበር ጥሶ የመጣን ባዕድ ወራሪ ወይንም የሀገርና የሕዝቦችን ልዕልና አደጋ ላይ ለመጣል የተሰለፈን አጥፊ ኃይል ተፋልሞ ለመርታት በጦር ሜዳ የሚተወን የተዋጊነትና የጀግንነት ተግባር ብቻ አለመሆኑም በሚገባ ግንዛቤ ተገኝቶበታል፡፡

አርበኝነት ከራስ ምቾትና ጥቅም ይልቅ በፖለቲካው፣ በማኅበራዊውና በኢኮኖሚው ዘርፍ የሀገርንና የወገንን ልዕልናና ክብር የማስቀደም ታላቅ የዜጎች የመንፈስ ለጋስነት የሚታይበትና በተግባር የሚረጋገጥበት እውነታ ነው፡፡

የአንድ መንግሥት የአወቃቀር ሥርዓት አሃዳዊም ሆነ ፌዴራላዊ፣ ወይንም ሌላ፤ ዘመናዊም ቢሆን ወይንም ባይሆን፣ ሀገርንና ወገንን በአንድ ላይ አቅፈውና አስማምተው ወደፊት ከሚያራምዱትና አፅንተው ከሚያቆሙት ጠንካራ አምዶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአርበኝነት የመንፈስ ውርስ ነው፡፡

አርበኝነት የሀገርንና የሕዝቦችን ክብር የማስጠበቅና የማስቀጠል ታላቅ ብሔራዊ ግዴታና የዜግነት ማረጋገጫ ከመሆኑ አኳያ ግለሰቡ የተገኘበት ብሔር ወይንም ጎሳ፣ ባህሉ ወይንም ቋንቋው፣ ፖለቲካዊ አመለካከቱ ወይንም እምነቱ ወዘተ… በአርበኝነቱ መንፈስ ላይ ጥላ አጥልቶበት “አያገባኝም” በሚል ውሳኔ ገለልተኛ ሊያደርገው እንደማይገባም ይታመናል፡፡ ከግል የተዛባ እምነትና ፍልስፍና በመነጨ ውሳኔም “በግለኝነት ስሜት ብቻ” ከሕዝቡ ጎራ ተለይቶ የሀገርን ጥቃት፣ ድህነት፣ ችግርና መከራ በሩቁ ሆኖ ለመመልከት መሞከር ወይንም የጥፋቱ አጋር ሆኖ መተባበር ትርፉ ከማኅበረሰቡ ባይተዋር ሆኖ መገለል ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊ፣ ህሊናዊና ሕጋዊ ቅጣቱም ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡

አርበኝነትን የሚያሰርፁና የሚያፀኑ መሠረታዊ ዓምዶች

አርበኝነት ራስን ለሀገርና ለወገን ሁለንተናዊና ሉዓላዊ ክብር አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ አርበኝነት የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ በደመቀ ኀብረ ውበትና መዛነቅ የተዋበ ነው፡፡ ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና ልምምዳቸው ሳይገድባቸው የሀገራችን ብሔረሰቦች በሙሉ የተጋመዱት በጋራ እሴቶችና መዛነቆች ተሳስረው ነው፡፡

የደጋው፣ የወይና ደጋውም ሆነ የቆላው ነዋሪ ወገናችን ለዘመናት ተሳስሮ የኖረው ተፈጥሮ በለገሰችው መኖሪያው ያፈራውንን የግብርናንም ሆነ የዕደ ጥበባት ውጤቶችን እየሸጠና እየተለዋወጠ ነው፡፡ ፡፡

ከዓለማችን በሞቃታማነቱና ከምድር ወለል በታች በዝቅተኛነቱ ክብረ ወሰን ከጨበጠው ዳሎል ጀምሮ እስከ የተራሮች ንጉሡ ራስ ዳሸን፣ ከስምጥ ሸለቆ የመሬት ስብርባሪ ገጽ እስከ ታላላቆቹ የወንዞቻችን ተፋሰሶች ኑሮውን ያደላደለው ኢትዮጵያዊ ወገን የዓየር ንብረት ለውጥ ሳይበግረው፣ የመልክዓ ምድር መዥጎርጎር ሳይገድበው ለዘመናት የኖረው እርስ በእርስ ተከባብሮና ተደጋግፎ ነው፡፡ የባህሉና የቋንቋው ኅብር ትስስሩን ይበልጥ አጥብቆለታል፡፡ በችግር ዘመን መደጋገፉ፣ በርሃብ ዘመን መረዳዳቱ፣ በመልካም ዘመን መደጋገፉ ባህሉ ነው፡፡

ሦስቱ ዋና ዋና ኃይማኖቶች (ክርስትና፣ ይሁዲነት እና እስልምና) በኢትዮጵያ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሕዝባችን እርስ በርሱ ተከባብሮ እንዲኖር የጣሉት መሠረትም እጅግ መልካም ነው፡፡ ይህ መዛነቅ በሰላም ጊዜ መደጋገፊያና መተሳሰቢያ፤ በችግር ጊዜ ደግሞ መረዳጃና የሀዘን መመከቻ በመሆን ለሕዝባችን የአርበኝነት መገለጫ እንደ መልሕቅ አንድነታችንን አጥብቆ ያቆራኘ መሠረታዊ እሴት ነው:: ስለዚህም ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር ሕዝባችን እንደ ንብ ሠራዊት ሆ እያለ የሚተመው፣ ጦሩን እየነቀነቀና ሰይፉን እያወናጨፈ በጀግንነት ወራሪ ጠላትን ፊት ለፊት እየገጠመ የሚመክተው፣ በችግር ዘመንም የሚደጋገፈው ከላይ የተዘረዘሩት ንብርብር ዕሴቶቹ በአንድ የሀገር ፍቅርና የአርበኝነት መንፈስ ስለቃኙት ነው፡፡

የአርበኝነት ዋና ዋና መገለጫዎች

አርበኝነት መልከ ብዙ እንደሆነ ከላይ በዝርዝር ተገልጧል፡፡ ድንበር ዘለል ወራሪን ለመመከትም ሆነ ራስን ለሀገር ጥቅምና ክብር አሳልፎ መስጠት የአርበኝነት ተቀዳሚ መገለጫ መሆኑ ተጠቋሟል፡፡ አርበኝነት በሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ ውስጥም እንደሚገለጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት አማካይነት ለሀገራችን ሞዴል አርሶ አደሮች፣ ለስኬታማ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ለአምራቾችና የፈጠራ ባለሙያዎች “በአርበኝነት” ማዕረግ ዕውቅናና ሽልማት መሰጠቱ በመልካምነቱ የሚጠቀስ ተግባር ነው፡፡

በማኅበራዊ ተሳትፎ ውስጥም “አርበኝነት” የሚገለፅባቸው ዘርፎች ብዙ ናቸው፡፡ የፍትህና የርትዕ ሥርዓት እንዳይዛባ በፅናትና ያለ ይሉኝታ ዘብ መቆም፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን የድርሻን በቀዳሚነት ማበርከት፣ በአርዓያነት ራስን ማሳወቅ፣ በበጎነት መልካም ተግባርን ማከናወን፣ ለተጎዱትና ድጋፍ የሚያሻቸውን መታደግ፣ በተሰማሩበት ተግባራት ሁሉ መልካም ተግባር በመፈፀምና ለሀገርንና ለሕዝብ ክብር ተፃራሪ ከሆነው የድህነት ውርደት ለመታደግ መጨከን ዋነኞቹ የዜጎች የአርበኝነት መገለጫ ተግባሮች ናቸው፡፡

የአርበኝነትን ስሜት የሚያደበዝዙ ተግዳሮቶች

 ስለ አርበኝነት የጻፉ ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት አርበኝነት መጀመሪያውኑ የተቀሰቀሰበት ምክንያት ሲረግብ ስሜቱ እየቀዘቀዘ የመሄድ አደጋ ይጠናወተዋልና መንፈሱ እንዳይላላ ከሥር ከሥሩ እየተኮተኮተ በመደበኛ ትምህርት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ጥበባት፣ በሙዚዬም፣ በሐውልታትና በመሳሰሉት አማካኝነት ዘመኑን በሚመጥን እሳቤ እና ማስታወሻዎች እየታደሰ ህልውናው እንዲጠበቅ መደረግ አለበት፡፡ ወጣቱ ስለአርበኝነት ስልታዊና ማኅበራዊ በሆነ ዘዴ ካልቀረበለት በስተቀር በአለፍ አገደም በሚደርሰው የቃል መልዕክትና አደራ ብቻ ግንዛቤው አያድግም፣ በመንፈሱ ውስጥም አይሰርፅም፡፡

የአርበኝነት ስሜት መልካም ፍሬ እንደሚያፈራ ዛፍ ሊመሰል ይችላል፡፡ ከተከለው ዛፍ መልካም ፍሬ የሚጠብቀው ገበሬ ለዛፉ እንክብካቤ ማድረግ ያለበት ገና ከችግኝነቱ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ተፈጥሮ ራሷ ታስተምረናለች፡፡ ችግኙ ለም አፈር፣ ተስማሚ አየር፣ ማዳበሪያና ውሃ በተገቢው ሁኔታ ማግኘት ካልቻለ አይደለም ፍሬ መጠበቅ የችግኙ ህልውና ራሱ አደጋ ላይ ወድቆ ለድርቀት ሊጋለጥ ይችላል፡፡

አርበኝነትም እንዲሁ በአንድ ወቅት ቢፈጠርም ለተከታታይ ትውልዶች በመንፈስ ቅርስነት በተገቢው ሁኔታ እንዲተላለፍ ባለድርሻ ነኝ የሚል አካል ሁሉ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግለት ይገባል፡፡

የአርበኝነትን መንፈስ እንደ ህልውና እስትንፋሳችን በየሰኮንዱና በየደቂቃው ሊነቃቃና ሊታደስ ይገባል፡ ፡ የአርበኝነትን ስሜት በወቅት ወለድ ክስተቶች ብቻ ወስነን እንደ ክት ልብስ ከተጎናፀፍነው እርሱ አርቴፊሻል የስሜት ሙቀት ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ለውጥ ላያመጣ ይችላል፡፡ አርበኝነት በፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜት በተሰለፉበት መስክ ሁሉ “ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ብሎ ማኩረፍ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን በጎ ተግባር ፈፀምኩ” ብሎ ራስን መጠየቅና ወቅቱ ለሚጠይቀው ሕዝብ ተኮር አደራ መስዋዕት ለመሆን እስከ መወሰን መጨከንን ይጠይቃል፡፡

በዕለት ከዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያችን፣ በተቀመጥንበት የአመራር ወንበር፣ ፍትሕን ለማስፈን ለማልነው መሃላ፣ በግል ጥቅም ልክፍት የሀገርን ክብር ከማዋረድና ከማሳፈር ከንቱ ድርጊት ራሳችንን በመጠበቅ ለሀገራዊ አጀንዳና ለሕዝቦች ልዕልና ተሟጋችና ምሳሌ ስንሆን ያን ጊዜ እውነተኛው የአርበኝነት ስሜት ያለ ገላጭ ቋንቋ በተግባራችንና በእርምጃችን ይገለጣል፡ ፡ በሀገርና በሕዝብ ላይ አደጋና ችግር ሲጋረጥ “እኔ ምን አገባኝ” በማለት የጲላጦስን ማስታጠቢያ አስቀርቦ እጅን መታጠብና ከአጥፊው ጋር ግንባር ፈጥሮ ለአደጋው መባባስ አባሪ ተባባሪ መሆን እውነተኛውን የአርበኝነት ስሜት ማሳደፍ ነው፡፡ የሀገርንና የሕዝቦችን ልዕልና የማስከበርን ጉዳይ ወደ መንግሥት ብቻ ጣትን እየጠቆሙ አያገባንም ማለት አይደለም፡፡ ዜጎች “እኔ ምን አገባኝ” ማለት ከጀመሩ በአርበኝነት ስሜት ላይ አደጋ እንደተጋረጠ ማረጋገጫ ሊሆን ችላል፡፡

የተወሰነ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ባህል ያልተጫነውን የአንድ ሀገር ብሔራዊ (ሁሉን አቀፍ) የአርበኝነት መንፈስ በዜጎች ውስጥ ለማስረፅ የሚፈታተኑ ተገዳዳሪ ሁነቶች በርካታ ቢሆኑም የዘርፉ ጠበብት በቀዳሚ ተርታ የሚያስቀምጡትን ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ብቻ እንደሚከተለው ለአብነት ማመልከት ይቻላል፡፡

ፅንፍ የያዘ ብሔረተኝነት – አርበኝነት አንዳንድ ጊዜ ከብሔረተኝነት ጋር በተለዋጭነት ግልጋሎት ላይ ይዋል እንጂ ሁለቱ የተሸከሙት ፅንሰ ሃሳብ በእጅጉ የተራራቀ ነው፡፡ አርበኝነት አመለካከቱ ሰፊ፣ አምነቱ ሕዝባዊነት፣ ትኩረቱ ሉዓላዊነት፣ አተገባበሩ ሁሉን አቀፍ፣ ግቡ ሀገራዊ ነው፡፡ በአንፃሩ ፅንፈኛ ብሔረተኝነት በአመለካከት ጭፍንነት፣ የራስን ብቻ በማግነን ባህሉንና ውርሱን “እኛና እነርሱ” በማለት እያነፃፀረ የራሱን ገናናነት የሚያውጅና ሌሎቹን ዝቅ የሚያደርግ አመለካከት ነው፡ ፡ ይህን መሰሉ አመለካከት ሥር እየሰደደ የሚሄድ ከሆነ ሀገራዊ የአርበኝነትን ስሜት ማደብዘዙ አይቀርም፡፡

አፈንጋጭ ቡድናዊ ስሜት – ይህን መሰሉ ስሜት ክበቡ ጠባብ ይምሰል እንጂ በሀገራዊ የአርበኝነት መንፈስ ላይ የሚያጠላው ጥላ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ አፈንጋጭ ቡድን አንዳንዴ የሚያነሳቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ውሃ የማይቋጥሩ ይምሰሉ እንጂ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ግን በቀላሉ ሊታዩ የሚገባቸው አይደሉም፡ ፡ “አርበኝነት በአንድ ወቅት የተፈጠረ ታሪካዊ ክስተት ስለሆነ ለእኔ ትውልድ ረብ የለውም” በማለት የሚሟገትና አርበኝነትን ከጦር ሜዳ ፍልሚያ ጀግንነት ጋር ብቻ በማያያዝ የሚከራከር ቡድን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ ባይታመንም ሃሳቡ ግን ይብዛም ይነስ ጥቂቶችን ማሸፈቱ አይቀርም፡፡

“ብዙኃኑ የሚዘምሩት አርበኝነት እኔና ቡድኔን ጎዳን እንጂ ምንም አልጠቀመንም” የሚል የቡድንተኝነት ቅስቀሳም ውሎ አድሮ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ አፈንጋጭ ቡድንተኝነት ዓላማውን ለማሳካት በተደራጀ መልኩም ሆነ በቡድኑ አባላት አማካይነት ስለሚቀነቀን ተልዕኮውን ለማሳካት ወቅትና ጊዜ አይመርጥም፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ አመለካከቶች በእጅጉ የተጣመሙ ቢሆኑም ውሎ አድሮ ግን ለሰሚዎችና ለተመልካቾች የአርበኝነትን መሠረታዊ ድንጋጌ በማዛባት በሕዝቦች መካከል መቃቃርን መፍጠራቸው አይቀርም፡፡

አርበኝነትና የዘመነ ሉላዊነት (Globaliazation) ተግዳሮቶች

ሉላዊነት የነፃ ንግድ ሥርዓትን፣ የካፒታል ዝውውርን፣ የዕውቀትና የሕዝቦችን እንቅስቃሴ “አርነት አውጥቶ” ዓለምን በአንድ መነፅር የመመልከት ወቅት ወለድ ፍልስፍና ነው፡፡ የፍልስፍናው ዋና ማስፋፊያ ደግሞ የተራቀቁት የመገናኛና የኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና በፈጣን ሁኔታ እየተዋወቁ ያሉ ሳይንሳዊ ግኝቶች ናቸው፡፡

ዛሬ ዓለማችን እያስተናገደችው ያለው የቅኝ ግዛት ወረራ በመደበኛ የጦር ሠራዊት የሚመራ ሳይሆን ስልቱ ያነጣጠረው የኢኮኖሚና የባህል ወረራ ላይ ነው፡ ፡ የጦርነቱ ፊት አውራሪ አዝማቾችም መገናኛ ብዙኃን፣ በቢሊዮን ቁጥር የሚገመቱ የድረ ገፅ ወረራዎች፣ ኢንተርኔት፣ ስፖርት፣ ሙዚቃና ፊልሞችን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

የዘመነ ግሎባላይዜሽን ተፅዕኖ ከሚገመተውና ከሚታሰበው በላይ እጅግ የረቀቀና የተወሳሰበ ነው፡፡ የአጥናፈ ዓለምን ወቅታዊና ቅፅበታዊ ውሎ አዳር በሁለት ጣቶቻችን ውስጥ አስገብተን በረበርናት ወደማለቱ ፍልስፍና ዘልቆ ከተገባ ሰነባብቷል፡፡

ዛሬ ዓለማችን በጣታችን መሃል ገብታለች የሚለው ፍልስፍና መሠረቱ የሉላዊነት መርቀቅ ውጤት መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ሉላዊነት የዓለም ሀገራትን ያመሳቅላል፣ ያቀላቅላል፣ ካልሆነለትም የማጥፋት አቅም አለው፣ ከበዛም ለታላላቅ ሀገራት ታናናሽ ሀገራትን የመስዋዕት በግ አድርጎ ያቀርባል፡፡

የኢኮኖሚ ወረራ ብቻ ሳይሆን የባህል ወረራም አንዱ የሉላዊነት መገለጫ ነው፡፡ ዛሬ በየትኞቹም ሀገራት የሚኖሩ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ወጣቶች የሀገራቸውን የአርበኝነት ታሪክ፣ የድልና የነፃነት ዓመታት ወይንም አንዳች ታሪካዊ ክስተቶች የተፈፀሙባቸውን ኩነቶች አስታውሶ በክብር ከመዘከር ይልቅ ስለ ቫለንታይን ቀን፣ ስለ ሃሎዊን ቀን፣ ስለ ክሬዚ ቀን፣ ስለ ከለር ቀንና ስለመሳሰሉት ቀናት መተረክና መዘከር ይቀላቸዋል፡፡ የሀገራቸውን የአርበኝነት ገድል ከማንበብና ከማጥናት ይልቅም የሆሊውድን ተዋናዮች፣ የእንግሊዝን የእግር ኳስ “ጀግኖች”፣ የፋሽን ዲዛይነሮችንና የፊልም ባለሙያዎችን ታሪክ፣ ገድልና የግል ህይወት ቢያነቡና ቢያደንቁ ይመርጣሉ፡፡

የዓለምን ዋና ዋና የንግድ ተቋማት በሞኖፖል ለመቆጣጠር እየተጉ ያሉት ማይክሮ ሶፍትን፣ ማክዶናልድስ፣ ናይክ፣ ሆሊውድ የመሳሰሉት ታላላቆቹ ኩባንያዎችና ታላላቅ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ዋነኛ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱት ለዚሁ የሉላዊነት ፍልስፍና ተልዕኮ አስፈፃሚነት እንደሆነ ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

በሉላዊነት ፍልስፍናና የፍጥነት ጉዞ ዙሪያ የሚደረጉት ውይይቶችና ክርክሮች እጅግ የተለያዩ ፅንፎችን የያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች የሉላዊነትን ጠቀሜታ አግዘፈው ለማሳየት ሲሞክሩ፣ አንዳንዶች ደግሞ አደጋውንና ተግዳሮቱን አግንነው ይከራከራሉ፡፡ ሉላዊነት እንደ ብዙ ምሁራን አገላለፅ (A Blessing in Disguise) ወይንም በእኛው አገላለፅ “በረከተ መርገም” እንደምንለው ነው፡፡ ጥቅሙ ላቅ ያለ ጉዳቱም የገነነ ሆኗልና፡፡

እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ዳቮስ ተደርጎ በነበረው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ የወቅቱ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ስለ ግሎባላይዜሽን ሲናገሩ “ነፃ የገበያ ውድድርና ሉላዊ ማኅበረሰብ (Global Society)ን በዓለም ላይ ብናሰፍን የሀገሮችን የተመጣጠነ ብልፅግና እናረጋግጣለን፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ሀገራት የሚመሩበትን የሉላዊነት መርህ መፍጠርና ማስፈፀም ይኖርብናል” በማለት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውሳኔ አከል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡

ከዓመታት በኋላ ወጤቱ ሲታይ ግን እንኳንስ የተመጣጠነ የሀገራት ዕድገት ሊመዘገብ ቀርቶ ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ትርምስ ውስጥ እንደገባች መረዳት ይቻላል፡፡ የአውሮፓን ኅብረት የመሠረቱት ሀገራት የሉላዊነቱ “በረከተ መርገም” አልጣጣም ብሏቸው ወደ መናቆርና ወደ መደናቆር እየወሰዳቸው ይገኛል፡፡ የእንግሊዝን ከኅብረቱ ለመውጣት ማኮብኮብ ተከትሎ ብዙ ቀውሶች እየተከተሉ ነው፡፡ ከኅብረቱ ለመውጣት ወፌ ቆመች እያለች ያለችው እንግሊዝም ወደ ጥንቱ “የዘርፈ ብዙ አርበኝነቴና ገናናነቴ” መመለስ አለብኝ ወደሚለው የቀዳሚ ዘመን ፍልስፍናዋ ለመመለስ ያሰበች ይመስል የጠነከረ አዋጅ በማወጅ ስሟን ከUnited Kingdom ወደ Great Britain ለውጣለች፡፡ የሀገሯ ሚዲያዎችና ተቋማትም ይህንኑ ስሟን እንዲያስከብሩላት ጥብቅ መመሪያ አውጥታለች፡ ፡ አሻፈረኝ ብለው በቀዳሚ ስሟ ካልጠራሁ ብለው የሚያንገራግሩትንም እንደምትቀጣ ውሳኔዋን በይፋ አስታውቃለች፡፡

የአፍሪካ መሪዎችም እ.ኤ.አ በ2063 በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ጥላ ሥር ለመሰባሰብ የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡ መሪዎቻችን በወሰኑት አህጉራዊ ውሳኔ ላይ ሂሳዊ ክርክር ለመክፈት ወቅቱ ያለፈ ቢሆንም ከአርበኝነት አንፃር የዓለም አቀፉን አካሄድና የመሪዎቻችንን ውሳኔ አጠቃሎ ማየቱ ግን አግባብ ይሆናል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በጋራ የተስማሙት አንድ የተባበረ የፖለቲካ ማኅበረሰብ፣ የተጠናከረ የጋራ ባህል፣ ውርስና ዕሴቶች ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ ህልም ደግሞ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትም በየአህጉራቸው ክልልና ቀጣናዎቻቸው ሊተገብሩት የሩቅና የቅርብ ዕቅድ ነድፈው ለተግባራዊነቱም በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ አንድ የመሆን ፍላጎት እውን ተግባራዊ ቢሆንና በየሀገራቱ ፈጥኖ ቢተገበር ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል? የእኛ የምንለውና በዘመናት ውስጥ ሥር የሰደደው የአርበኝነት መንፈስ ሊደበዝዝ አይችልም? መልካም ብለን አክብረን የያዝናቸው ሀገራዊ ዕሴቶቻችንስ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል? በዜጎቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን የማንነት ቀውስስ እንደምን መቋቋም ይቻላል፡፡ ሉላዊነትን ከሀገራዊ አርበኝነትስ ጋር አዛምዶስ እንደምን መጓዝ ይቻላል? ውይይት ሊደረግበት ይገባል፡፡

የአርበኝነትን ክብር ለማስጠበቅና ለማስቀጠል ከማን ምን ይጠበቃል?

የሀገራችን ዘርፈ ብዙ አርበኝነት መንፈስ በአግባቡ እየጎለበተ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚከተሉት ተቀዳሚ ባለድርሻ አካላት ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡

ዋናው ባለድርሻ መንግሥት ነው – መንግሥት የሕዝብን የሥልጣን አደራ ተቀብሎ የሚያስተዳድር ስለሆነ የዜጎች የአርበኝነት መንፈስ እንዳይቀዘቅዝ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባዋል፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ተቀብሎ ምራኝ ብሎ ሕዝቡ ለመንግሥት ስልጣኑን በአደራ ጭምር ያስረከበው የዕለት ዳቦ እንዲያቀርብለት፣ የሀገሩን ሉዓላዊ ክብር እንዲያስጠብቅለት፣ ደህንነቱን እንዲጠብቅለት፣ የዲፕሎማሲ ተግባር እንዲያከናውን፣ የትምህርትና የልማት ሥራዎችን እንዲያሳልጥ ብቻ አይደለም፡፡ ዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ማድረግም ግድ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት የሕዝቡን ባህላዊ ውርስ ማስጠበቅ፣ የአርበኝነትን መንፈስ መንከባከብ፣ የቋንቋውንና የባህሉን የህብር ውበት ማስቀጠል ይጠበቅበታል፡፡

የአንድ ሀገር ዘርፈ ብዙ የአርበኝነት ስሜት ከሕዝብ መንፈስ ውስጥ ከጠፋ ተስፋው ይደበዝዛል፣ ኩራቱም ይመነምናል፣ ብሔራዊ ስሜቱም ይቀዛቀዛል፡ ፡ በውጤቱም ልማትም ሆነ ሀገራዊ የዜጎች ደህንነት ለአደጋ መጋረጡ አይቀርም፡፡

የአርበኝነት መንፈስ የሚጠበቀውና ቀጣይነት የሚኖረው ዜጎች በየተሰማሩበት የተግባር መስክ ከራስ ባለፈ ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ፈጽመው ለሚያበረክቱት የአርበኝነት አስተዋጽኦ መንግሥት በዕውቅናና በሽልማት አጅቦ በይፋ ሲያመሰግናቸውና ለልዩ ልዩ ዘርፎች አርበኞች ባበረከቱት አስተዋፅኦ ልክ “ጀግኖቻችን” በማለት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕዝቡ ስም አክብሮቱን ሲገልፅላቸው ነው፡፡ የሲቪክስ ትምህርት ድርሻም እንደገና ተቃኝቶ ሊተገበር ይገባል፡፡

ወጣቶች ትምህርታቸውን ጨርሰው በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ወደ ሥራ ከመሠማራታቸው አስቀድሞ ቀደም ብሎ በሀገራችን ይደረግ እንደነበረው የብሔራዊ አገልግሎት ግዳጃቸውን እንዲወጡ ሥርዓት ቢዘረጋ ወቅቱ ለሚጠይቀው የአርበኝነት መንፈስ መነቃቃት ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ መስራት ይቻላል፡፡

የሲቪልና የሙያ ማኅበራት – የሲቪልና የሙያ ማኅበራት በዋናነት የተቋቋሙበትን ዓላማ የሚያስፈፅሙት በወገንተኝነት ለቆሙለት ቡድን ከመሆኑ አኳያ በየዘርፋቸው ከሚወክሉት ቡድንና ሙያ በምሳሌነት የሚጠቅሷቸውን የሀገር የሕዝብ ጀግኖችን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ፣ በአቅማቸው ልክና ከመንግሥት ጋር በመተባበር ዕውቅና ሊሰጧቸው፣ ሊሸልሟቸውና በስማቸው መታሰቢያ እንዲቆምላቸው አጥብቀው ሊሟገቱና ሊተጉ ይገባል፡፡

የምርምርና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት – እነዚህን መሰል ሀገራዊ ተቋማት የአርበኝነትን መንፈስ ለማስረፅ የኃላፊነታቸው ወሰን የተመቻቸ ስለሆነ “የክብር ማዕረግ” መስጠቱን አጠናክረው ሊሠሩበት ይገባል፡፡

አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት – አብዛኛውን የሀገሪቱን ሠራተኞች አቅፈው የያዙት እነዚህን መሰል ተቋማት በልዩ ሁኔታ ለምርታማነታቸው ስኬትና ለአገልግሎታቸው ውጤታማነት በትጋት የሠሩትንና አዳዲስ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋወቁትን ባለሙያዎቻቸውን በይፋ ያለ ስስትና ያለ አድልኦ ሊያከብሯቸውና ሊሸልሟቸው ይገባል፡፡

የግልና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት- በየሙያ መስኩ ሀገራዊ የአርበኝነት መንፈስ ለማነቃቃትና የየሙያውን ተጠቃሽ አርበኞች ተግባራት ለአደባባይ ማብቃት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል፡፡

ከራሳችን ተሞክሮ በዘለለ ሌሎች ሀገሮች ያለፉበትንም ልምድ ማየቱ ብልህነት ስለሆነ ሲንጋፖር ጥሩ ማሳያ ስለሆነች የእርሷን ተሞክሮ በአርዓያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዘመናት ውስጥ በተለያዩ ወራሪዎችና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ስትመሳቀል ኖራ በኋላም ቅርቧና ቤተኛዋ ከሆነችው ከማሌዥያ ውህደት በመፋታት በ1965 ዓ.ም ሙሉ ነፃነቷን የተጎናፀፈችው ሲንጋፖር ዛሬ በዓለም ማሕበረሰብ ዘንድ የምትታወቀው “የምድር ገነት ”First World Oasis in a Third World” እየተባለች ቢሆንም እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሷ በፊት አያሌ ውጣ ውረዶችን መቋቋም ግድ ብሏት ነበር፡፡

ሲንጋፖር እንደ ሉዓላዊ ሀገር ከማሌዥያ ሪፐብሊክ ጥገኝነት ተላቃ ራሷን በቻለችበት በ1965 ዓ.ም የሕዝቧ ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን አይበልጥም ነበር፡፡ 63 ያህል ደሴቶች ተጣምረው የፈጠሯት ሲንጋፖር ነፃ በወጣችበት ዓመት ይህ ነው የሚባል ኢኮኖሚ ያልነበራት፣ ዜጎቿ በትምህርት ኋላ የቀሩ፣ ሊመነዘር የሚችልና ከድህነት ሊያላቅቃት የሚችል የሚያኮራ የተፈጥሮ ሀብትም አልነበራትም፡፡

ይህንን ያስተዋሉት ሩቅ አሳቢ መሪዎቿ ሀገራቸውን በአጭር ዓመታት ለማሳደግ በቆራጥነትና በትጋት መስራት ጀመሩ፡፡ ከዓለም ማኅበረሰብ ጋር በቀላሉ ለመቀላቀል እንዲረዳቸውም የተዥጎረጎረውን የማንድሪን፣ የማሌይ እና የታሚልን ቋንቋዎች እንደነበሩ አኑረው ብሔራዊ የሥራና የትምህርት ቋንቋቸውን ወደ እንግሊዝኛ ለወጡ፡፡

ዜጎቻቸውም ወደ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ሄደው እንዲማሩ በሩን ወለል አድርገው ከፈቱላቸው፡ ፡ በተለያዩ ሀገራት ሄደው የመስራት ፍላጎት ያላቸውንም ሁኔታዎቹን አመቻቹላቸው፡፡ እያንዳንድ ዜጋ ሲሸኝም የሀገሩ እዳ እንዳለበትና ተምሮም ሆነ ሰርቶ እንዲመለስ በአደራ ቃል አሰሩት፡፡

ከዓመታት በኋላ ወደ ተለያዩ ሀገራት የተበተኑት ዜጎቿ እንዲመለሱ ሲንጋፖር “የእናት ሀገር ጥሪ አወጀች” ጥሪውን በመቀበልም በርካታ ዜጎቿ ዕውቀታቸውንና ሀብታቸውን ሰብስበው ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው ገቡ፡፡

ነገር ግን ተመላሽ ዜጎቿ ሀብት እንጂ ብሔራዊ ስሜታቸው ቀዝቅዞ፣ ዕውቀት እንጂ የክብራቸው ጉዳይ ላሽቆ የማንነት ቀውስ ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ የሀገራቸው አርበኝነት ታሪክ ደብዝዞ፣ የታሪክ ኩራታቸው ደብዛው ጠፍቶ “ባዕድ ባለሀገር” ሆነው አረፉት፡፡ ከሀገራቸው ታሪክ ይልቅ የኖሩበትንና የተማሩባቸውን ሀገራት ታሪክ ማነብነብ ይቀላቸው ጀመር፡፡ በአባት በአያቶቻቸው የተከፈለው መስዋዕትነት ተዘንግቶ እስከ መረሳት ደረሰ፡፡

ይህንን መሰሉን የዜጎቻቸውን ውጥንቅጥ ማንነት ያስተዋሉት ጥበበኛ መሪዎቿ ዜጎቻቸው የገጠማቸውን የማንነት ቀውስ ለመፈወስ አዳዲስ ስልቶችን መቀየስ ነበረባቸው፡፡ ዜጎቻቸው ብሔራዊ ስሜታቸው እንዲያገግምና የአርበኝነት መንፈሳቸው እንዲያንሰራራ በአእምሯቸው ላይ አጥብቀው መስራት ጀመሩ፡፡ “ወደ ቋንቋችንና ወደ እሴቶቻችን እንመለስ” በሚል መሪ መፈክር እየተመሩ ቀን ከሌት በሕዝባቸው አእምሮና መንፈስ ላይ መሥራት ቻሉ፡፡

የሕዝባቸው ብሔራዊ ስሜት እንዲያብብም በመላው ሀገሪቱ የተለያዩ የውይይትና የትምህርት መድረኮች ተመቻቹ፡፡ የትምህርት ቤቶችና የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት አርበኝነትና ብሔራዊ ፍቅር ላይ አተኮረ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቻቸውና ፓርላማቸው በራሷ ዕሴት፣ ባህል፣ ቋንቋዎችና ብሔራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተች አዲሲቷን ሲንጋፖር ለማነፅ ተግተው መረባረብ ጀመሩ፡፡ ቤተ እምነቶች ሳይቀሩ ለአዲሲቷ ሲንጋፖር የአዋላጅነታቸውን ሚና አጥብቀው ተወጡ፡ ፡ ኪነ ጥበባቸው፣ ፊልሞቻቸው፣ ጋዜጦችና ሚዲያው በጠቅላላው ትጋታቸው ወደ ራስ ብሔራዊ ክብር ላይ መመለስና ዜጎቻቸው በሙሉ በየሙያ ዘርፋቸው የሀገራቸው የሲንጋፖር አርበኞች እንደሆኑ ባለመሰልቸት ማስተማር ቀጠሉ፡፡ የውይይቶቹ ርዕስ በመሉ “ለሲንጋፖር መሞት ወይንም ከሲንጋፖር ጋር አብሮ መሞት” የሚል ነበር፡፡

ጥረታቸው አልመከነም በተከናወነው ታሪካዊ ተግባራት የዛሬይቱ ሲንጋፖርን የመሰለች አዲስ ሀገር ግራ ከተጋባቸው ሲንጋፖራውያን ውስጥ ተወልዳ እነሆ “የምድር ገነት”፣ “የአንበሶች ከተማ”፣ “ሚጢጢዬዋ ቀይ ነጥብ” በሚሉ የክብርና የቁልምጫ ስሞችን ልትጎናጸፍ በቃች፡፡

የአርበኝነት መንፈስ ይታደሳል? በትክክል፡፡ ከግሎባላይዜሽን ትሩፋቶች እየተጠቀሙ የራስን ማንነት ማስጠበቅ ይቻላል፡- በትክክል? በአህጉርም ደረጃ ሆነ በዞን ደረጃ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠሩ እንደተጠበቀ ሆነ የራስን ብሔራዊ ጥቅም፣ ባህል፣ ቋንቋና የአርበኝነትን መንፈስ አስቀጥሎ መጓዝ ይቻላል? በሚገባ ይቻላል፡፡ ግን ብዙ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያም እያንዳንዱ ዜጋ በተሰለፈበት የሙያ ዘርፍ በአርበኝነት መንፈስ እንዲነቃቃ ሁሉም የድርሻውን ቢወጣ የምንመኛትን ዓይነት ኢትዮጵያ፣ ለሕዝቦቿ ምቹ የሆነች እናት ዓለምን በቅርብ ዓመታት እንደምናዋልድ እርግጠኛ መሆን አይገድም፡፡ ሰላም ይሁን፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2011

 ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *