አንድ አሳ በማስገር የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ቅዳሜ ቅዳሜ ከሰዓት ሁለት ውሾቹን ይዞ ወደ ከተማ ይሄዳል፡፡ የዚህ ሰው ውሾች ቀለም ነጭ እና ጥቁር ነበሩ፡፡ ውሾቹ እርስ በእርሳቸው በትዕዛዝ እንዴት መፋለም እንዳለባቸው በደንብ አሰልጥኗቸዋል፡፡ በባለቤታቸው ትዕዛዝ እንዴት እንደሚጋጠሙ አስተምሯቸዋል፡፡ ሁልጊዜ ቅዳሜ ከሰዓት ከተማው ላይ በሚገኘው ትልቁ አደባባይ በርካታ ሕዝብ ይሰበሰባል፤ ሁለቱ ውሾች እርስ በእርስ ይፋለማሉ፤ ባለቤታቸው አሳ አስጋሪው ደግሞ በከፍተኛ ገንዝብ ይወራረዳል፡፡

አሳ አስጋሪው የሚወራረደው አንዴ “ጥቁሩ ውሻ ያሸንፋል” ብሎ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ “ነጩ ውሻ ያሸንፋል” በማለት ነው፡፡ የሚገርመው ግን አሳ አስጋሪው ሁልጊዜም ውርርዱን ይበላል፡፡ ተሸንፎ አያውቅም፡፡ በአንዱ ቀን ‘ጥቁሩ ውሻ ያሸንፋል’ ብሎ ከተወራረደ በእርግጠኝነት ጥቁሩ ውሻ ያሸንፋል፤ በሌላ ቀን ደግሞ ‘ነጩ ውሻ ያሸንፋል’ ብሎ ከተወራረደ በእርግጠኝነት ነጩ ውሻ ያሸንፋል፡፡ በዚህም ምክንያት አደባባዩ ላይ የሚሰበሰው እና ትርዒቱን የሚከታተለው ሕዝብ በዚህ ጉዳይ በጣም ይገረም ነበር፡፡ “እንዴት ሁልጊዜ ይህ አሳ አስጋሪ ሊያሸንፍ ይችላል?” እያሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡

አንድ ቀን የአሳ አስጋሪው የልብ ጓደኞች ይህ ሁኔታ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ለመጠየቅ ወደ ቤቱ ሔዱ፡፡ እንዲህም በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ፡- “ውድ ጓደኛችን አንተ ሁልጊዜም ጥቁሩ ውሻ እንደሚያሸንፍ ከተወራረድህ ጥቁሩ ውሻ ነው የሚያሸንፈው፤ ነጩ ውሻ ያሸንፋል ብለህ ከተወራረድህም ነጩ ውሻ እንደሚያሸንፍ አየን፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብታስረዳን? እባክህ ሚስጥሩን ንገረን…” ብለው በተደጋጋሚ ይጠይቁታል፡፡

አሳ አስጋሪውም የሕዝቡ እና የጓደኞቹ ጥያቄ ሲበዛበት ሚሲጥሩን እንዲህ ብሎ ይነግራቸዋል፡- “ወዳጆቼ እንዴት መሰላችሁ….ወደ ከተማ ስመጣ ነጩ ውሻዬ እንዲያሸንፍ ከፈለግሁ፣ ነጩን ውሻ በደንብ እመግበዋለሁ፤ ጥቁሩን ውሻ ደግሞ ምግብ እንዳይበላ እከለክለዋለሁ፡፡ ጥቁሩ ውሻየ እንዲያሸንፍ ከፈልግሁ ደግሞ ጥቁሩን ምግብ አብልቼ ነጩን እተወዋለሁ፡፡ ሁልጊዜም የበላው ውሻ ጠንካራ ይሆናል፤ ግጥሚያንም ያሸንፋል፤ ምግብ ያልበላው ውሻ ደግሞ ደካማ እና ልፍስፍስ ይሆናል፤ በጨዋታውም ይሸነፋል” በማለት አስረዳቸው፡፡ ጓደኞቹም በጣም ተገርመው ወደመጡበት ተመለሱ፡፡

ይህ አሳ አስጋሪ ሴረኛ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን ታሪክ ወደ ወቅቱ ፖለቲካችን እንውሰደው፡፡ ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ነገር የሴራ ፖለቲካ አሸናፊ እና ተሸናፊ ቀድሞ የሚወሰንበት ነው፡፡ አሁን በሀገራችን የምናየው ልክ እንደ ውሾቹ ባለቤት አካሄድ ነው፡፡ ዳጎስ ያለ ጉርሻ ያገኘው ውሻ፣ እንዳይበላ የተከለከለውን ውሻ እንዳሸነፈው ሁሉ ቀለብተኞች ለጊዜውም ቢሆን አሸናፊ ይሆናሉ፤ በሌላ ጊዜ የተራቡት የጠገቡ እለት ደግሞ ሚናው ይገለበጣል፤ አሸናፊዎች ተሸናፊ ይሆናሉ፤ ተሳዳጆች ያሳድዳሉ፤ ምክንያቱም ነገሮች ባሉበት ሁኔታ ለዘላለም አይቆዩምና፡፡ ትላንት ሀያላን የተባሉት ሁሉ ዛሬ በመንበራቸው አላገኘናቸውምና፡፡ ሁልጊዜ እያሸነፉ መቀጠል አይቻልም፡፡ በማናችንም አሸናፊነትም ሆነ ውድቀት የሚያተርፉ አሳ አስጋሪዎች ግን እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለት ምርጫዎች አሉን፡፡ አንደኛው ይህ አሳ አስጋሪ የሚሰራውን ሴራ በአደባባይ እየተገኙ መመልከት እና መደመም፤ ሁለተኛው ደግሞ ይህ አሳ አስጋሪ እንዴት ሁልጊዜ እንደሚያሸንፍ ሚስጥሩን በአግባቡ መረዳት እና ከጀርባ ያለውን ሴራ ተረድቶ ቢያንስ አለመሸወድ ነው፡፡ ሴራውን ቀድመን ካወቅነው ቢያንስ አንወራረድም፤ ቀድሞ አሸናፊነቱ ለተረጋገጠ ጉዳይ በተቃራኒ ቆመን ሀብታችንን አናባክንም፡፡

ሴራውን ለመረዳት በአንድ ላይ ሆነን ካልመረምርነው እና ካላጠየቅነው ያ አሳ አስጋሪ ሁልጊዜም እያሸነፈ ይኖራል፡፡ በእኛ መፋለም የራሱን ኪስ ያደልባል፤ የፖለቲካ ትርፍ ያገኛል፤ ሁሌም የእኛን ፍልሚያ እንደፊልም እየኮመኮመ እግሩን ዘርግቶ ይስቃል፡፡ በእኛ መፋለም መከራ ይበዛል፤ ሰቆቃ ይበረታል፤ ሌላ የማንወጣው አዙሪት ውስጥ እንገባለን፤ በመጨረሻም አገርና ሕዝብ እንጎዳለን፡፡

ልዩነታችንን አጣጥመን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በጋራ ተባብረን መስራት እና ከእኛ የሚጠብቀውን ውጤት በማስመዝገብ እንወክለዋለን የምንለውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻል የወቅቱ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅብን ጉዳይ ነው፡፡

እንግዲህ ምርጫው የራሳችን ነው! የአሳ አስጋሪው መና ሆነን እንቀጥላለን ወይስ የአሳ አስጋሪውን ሴራ ተረድተን ራሳችንን እና ሕዝባችንን ከጥፋት እናድናለን?

ቸር ይግጠመን!

Asemahagn Aseres

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *