የሃገራችን ፖለቲካ ብሄርን መሰረት ያደረገና በአማራው ሕዝብ ጥላቻ ላይ የተቸከለ ሆኖ ቆይቷል:: ካለው ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታና ከአማራ ጠል የጽንፈኛ ሃይሎች የሃይል አሰልለፍ አኳያ ወደፊትም የሚያስከትለው አደጋ ለመገመት የሚከብድና እጅግ አደገኛ ነው::
ከዚህ አኳያ የአማራው ሕዝብ የራሱን ህልውና ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዐላዊነትና የህዝቡን አንድነት ለማረጋገጥ በሁለገብ ሁኔታ አቅሙን ማጠናከር እንዲችል አዴፓን ማገዝና ማጠናከር ይኖርበታል::
እያየለ የመጣውን የጽንፈኛ ሃይሎችን የፀረ አማራ የፀረ አንድነትና የፀረ ኢትዮጵያዊነት ትንቅንቅ ውስጥ የአማራው ህብረተስብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሕልውናውን ከጥቃት ለመከላከልና በሃይል አሰላለፉ ውስጥ ሚዛኑን የጠበቀ  ተገቢ ቦታ አዴፓ እንዲኖረው የመላው ህብረተስቡ ድጋፍ ያስፈልገዋል::
ከዚህ አንጻር በየትም ያለ የአማራው ተወላጅ በሚቻለውና ባለው አቅም የተቃጣበትን የሕልውና አደጋ ለመከላከል በአዴፓ ዙሪያ ተሰባስቦ ትግሉን ለማጠናከር ከታች የቀረቡት ማድረግ ቢችል ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ::
1, የአማራውን አንድነት ከሚከፉፍሉ አፍራሾችና ከጎጠኛ አስተሳሰብ እርቆ በጋራ ጥቅሞቹ ዙሪያ በመሰለፍ ጥንካሬውን መገንባት
2, አዴፖ ከቀድሞ የፖለቲካና የርዕዩተ-ዓለም ቅርቃሩ ወጥቶ በአማራው ወግና ባህል : ትውፊትና ስነልቦና ልክ ቁመና እንዲኖረው ምሁራን ገንቢ ሂስ በማቅረብ ድርጅቱን ማረቅ አመራሩን ማጠናከር
3, የሶሻል ሚድያ ብሎገሮች አክቲቪስቶችና የአማራ ፖለቲካ አቀንቃኞች አዴፖን እንደ ድርጅት ከሚዘረጥጥ አመራሩን ከሚያዋርድና ከሚከፋፍል አቅጣጫ ወጥታችሁ በወገናዊ አቀራረብ በጨዋነትና በብስለት ድርጅቱ የሕዝብን ጥያቄ እንዲመልስና ሕዝባዊነት እንዲላበስ የተቀናጀ ዘመቻ ማካሄድ
4, መሪ የሚፈልቀው ከሕዝብ አብራክ በመሆኑ ወደ አመራር የሚመጡ ፖለቲከኞችን ሞራል በመስጠት ዕገዛ በማድረግ ብቁ እንዲሆን መርዳት:: በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በስሜት ከግንዛቤ እጥረትና ከፖሊሲ አተናተን አኳያ የሚከሰት የአደባባይ ስህተትን በደቦ ስድብና ዘመቻ ሳይሆን በምክርና በተግሳጽ እንዲታረም እድል መስጠት::
5, በአዴፓና በአብን መካከል ጤናማ የሆነ አብሮነት እንዲፈጠር መርዳት:: በአማራ ሕልውና እና በጥቅሞቹ ዙሪያ በጋራና በትብብር እንዲሰሩ ማቀራረብ
6,አዴፖ የአማራው ሕዝብ ያለው ትጥቅ የመያዝ መብት እንዲያከብር:: የአማራው መታጠቅ ለአዴፖ አመራሮች ሞገስ ለሕዝቡ ሕልውና መጠበቂያና ብሎም ኢትዮጵያን ሊታደግ የሚችል መሆኑ ማሳወቅ::
7, በውጭ ያለው የአማራ ተወላጅ እራሱን በተለያየ መስክ  በሃገር ውስጥ የሚካሄደውን ትግል ሊያግዝ በሚችልበት መንገድ ማደራጀት :: በዲፕሎማሲ በሎቢና በእውቀት ሽግግርና ዘርፍ ድጋፍ ሊያደርግ የሚችልበትን መስመር ማበጀት::
8, የአማራውን ሕዝብ ተደራሽ የሚያደርጉ የሚድያ ተቋማትን በእውቀት በገንዘብና በምችለው አቅም ማጠናከር::
9, የአማራው ልሂቅ ሶሻል ሚድያ ላይ ተጥዶ ዝና ከመገንባትና ውዳሴ (ላይክ) ከማሳደድ ወጥቶ የተደራጀ ምሁራዊ ድጋፍ መስጠት ወደሚችልበት ምዕራፍ መሸጋገር
10, ከጥቂት ግዜ ወዲህ የአማራን ፖለቲካ በሶሻል ሚድያ የሚያቀነቅኑ ከአማራው ባህል ወግና ስነምግባር ያፈነገጡ ጦማሪያን ከዚህ ሕዝባችንን ከማይመጥን ነውረኛ ተግባር እንዲቆጠቡ መምከር:: ትውልዱ ሃሳብን በሃሳብ የመታገልን ስልጡንነትና ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲያዳብር መርዳት
11, በኢትዮጵያ አንድነት ጽኑ አቋም ያላቸውን ብሄረሰቦች ከአማራው ሕዝብ ጋር ቆመው ሃገራቸውን ከጥፉት ለመከላከል ከሚፈልጉ የደቡብ, የአፋር የጋንቤላ, የሶማሌ, የትግራይና የኦሮሞ ሕዝቦች ጋር በጋራ በሃገር ሉዓላዊነትና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ትብብር መፍጠርና ማጠናከር እንዲችል አዴፖን መቀስቀስ መርዳት::
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *