BBC Amharic -የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ. ም አጠናቆ መግለጫ አውጥቷል።

መግለጫው በርካቶችን ያስደነገጠ ሲሆን በተለይ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) መረር ያለ ምላሽ እንዲሰጥ አድርጎታል። ይህ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ባልተለመደ መልኩ መነቋቆርና በመግለጫ እስከመመላለስ መድረስ ምን ያሳየናል ስንል ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን እና የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌን ጠይቀናቸዋል።

ፓርቲዎቹ ለስም አብረው አሉ ቢባልም እንደተለያዩ የሚያምኑት ዶ/ር ዳኛቸው “ምንም እንኳን ከፌደራል መንግሥቱ የሚያገኙትን ነገር ሳያቅማሙ እየተቀበሉ ቢሆንም ትግራይ ሪፐብሊኳን ይዛ ለብቻዋ ነው ያለችው። ህወሓቶች ማዕከላዊውን መንግሥትም የተቀበሉት አይመስልም” ይላሉ።

በዚህ ሰዓት ከምክንያት ይልቅ ስሜት የሚሞቅበትና የሚገንበት ነው የሚሉት አቶ አንዷለም አራጌ በበኩላቸው ሁለቱም ፓርቲዎች ነገሩን የያዙበት መንገድ ተገቢ እንዳልሆነ ያስቀምጣሉ።

ህወሓቶች በጉልበትም ቢሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፊት ሆነን እንመራለን የሚሉ ስለሆኑ ይህንን ሃሳብ የሚመጥን መስከን፣ ስልጣኔና አርቆ አሳቢነት ከእነርሱ ይጠበቃል ይላሉ አቶ አንዷለም። ልዩነቶችም ሲኖሩ ልዩነቶችን በሰከነ ሁኔታ በፊት እንደሚያደርጉት ከመጋረጃ ጀርባ ከዚህም በበለጠ ደግሞ በብልሀትና በሆደ ሰፊነት ነገሮችን መያዝ ያስፈልግ ነበር ሲሉ ያስረዳሉ።

አዴፓ ህወሓት ካወጣው መግለጫ አንጻር የሰጠው መግለጫ ተገቢ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው የህወሓት መግለጫ በፓርቲው ውስጥ እየታየ የነበረውን ልዩነት የበለጠ እያሰፋው መሆኑንና ከፌደራል መንግሥቱ የተለየ አካል እየሆነ መምጣቱን ያመለክታል ብለዋል።

አዴፓ በግድያ አመራሮቹን ሲያጣ “ይህ ነገር በመከሰቱ እናዝናለን ከማለት ይልቅ ከእናንተ ጋር ለመስራት እንቸገራለን የሚል መግለጫ ማውጣት ስህተት ነው፤ የሚያበሳጭ ነገር ነው ለዚህም አጸፋ ከአዴፓ ተገቢውን ምላሽ ያገኙ ይመስለኛል” ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸው።

ልዩነቶቻቸውን ተገማግመውና ተሞራርደው በአግባቡ መያዝ ሲገባቸው ህወሓት እንዲህ አይነት መግለጫ ቀድሞ ማውጣቱ ከብልህነት አንፃር ተገቢ ያልሆነ፤ ነገር ግን አጭር እይታ ላይ የተመሰረተ እና ምናልባትም አድብቶ ነገሮችን የማድረግ ይመስላል ያሉት ደግሞ አቶ አንዷለም ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በአዴፓ በኩል የማየው በጣም የበዛ መቆሳሰል እንዲሁም የበዛ ለተመልካች፣ ለሰሚ፣ ለሀገሩ ብዙም የተጨነቀ የማይመስል እልህ የመወጣት የሚመስል ውዝግብ ነው በማለት በአጠቃላይ የኢህአዴግን ስብስብ የብቃትና የአርቆ አሳቢነት ደረጃን የሚያሳብቅ ነው ሲሉ ይተቻሉ።

ኢህአዴግ በግንባርነት የመቆያ ጊዜው እያበቃ እሆን?

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከዚህ በፊትም “ይህንን ለውጥ ለማሳካት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፈተና የሚሆነው የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎችን በአግባቡ ማስተዳደር ነው” ማለታቸውን አስታውሰው፤ ይህ አለመስማማት ከዚህ በፊትም በመካከላቸው የነበረ ነው በማለት መነሻው የጋራ ግብ አለመኖሩ ነው ይላሉ።

“ለውጡን እንዴት ማስኬድ አለብን? እስከ የትስ እናስኬደዋለን? ብለው ከመስማማታቸው በፊት የገቡበት ይመስለኛል” የሚሉት ፕሮፌሰሩ ኢህአዴግ ይህንን ለውጥ ብቻውን ለማስኬድ መምረጡ እንዳይስማሙ እንዳደረጋቸው በመግለፅ በዚህ መልኩ ከቀጠሉ አንዱ ሌላውን ሊያፈርስ ይችላል ይላሉ።

የህወሓት መግለጫና አቋም አዴፓን ብቻ የሚያብጠለጥል ሳይሆን የፌደራል መንግሥቱንም ጭምር የሚመለከት እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶ/ር ዳኛቸው በበኩላቸው “ከአዴፓ ጋር አንሰራም ሲሉ አንሰራም እያሉ ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም ነው” ይላሉ።

አንዷለም አራጌ በበኩሉ የኢህአዴግ ጊዜ እያበቃ ሊሆን ይችላል ይላል። “ከዚህ በፊት የከረረ ጉዳይ ሲኖራቸው ለቀናት ወይም ለሳምንታት በውስጣቸው ይዘው በመነጋገር ለመገናኛ ብዙሀን እንኳ የማይገልጡበት ሁኔታ ነበር። አሁን ግን ኢህአዴግን ያጣበቀው ሙጫ እየደረቀ፣ እየተፈረቀቀ ይመስለኛል” በማለት ያክላል።

አሁን እየታየ ያለው በእራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በተለይ ደግሞ ህወሓት “ለውጡ ለእኔ ሳይሆን በእኔ ላይ ነው የመጣው” በማለት ከመጀመሪያው ያቄመ ይመስለኛል የሚሉት አቶ አንዷለም ለውጡን ለማደናቀፍ እየሰራ ይሆን የሚል ጠንካራ ጥርጣሬ አለኝ ይላሉ።

“አሁንም እነዶክተር ዐብይ ብቻቸውን ህዝብን ሊያሸጋግሩ አይችሉም” የሚሉት አቶ አንዷለም “ሀገርን ህዝብን ሊያሸጋግር የሚችለው የብዙኀን ተሳትፎ ነው” ሲሉ አስረግጠው ይናገራሉ።

“የመሪነቱን ኃላፊነት እነርሱ ቢወስዱም ህዝቡን በብዛት ማሳተፍ አለባቸው። እያንዳንዱ ጡብ ማቀበል አለበት እንጂ ሀገርን ወደ ዲሞክራሲ የማሸጋገር ሥራ ጥቂቶች ጀምረው የሚጨርሱት አይደለም።”

“ሀገር ለለውጥ በምትዳክርበት እና ብዙ አርቆ አሳቢ በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት የአጭር ጊዜ ህልምን ለማሳካትና የግል ቁርሾህን ለመወጣት ግብግብ የምትገጥምበት አይመስለኝም” ይላሉ አቶ አንዷለም።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ሌሎች አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ከፍ ያለ ማስተዋልን፣ ሰፊ ልብና የመንፈስ ልዕልናን የሚጠይቅ መሰባሰብ፣ መወያየት ከአቋራጭና ጊዜያዊ ድሎች፣ ተራ ብሽሽቆች እንዲሁም ዘለፋዎች እርቀን ሀገራችንን ወደተሻለ የፖለቲካ ሥርዓትና ዘመን የምናሸጋግርበት፤ አርቆ አሳቢነትና ብልህነት የሚጠይቅ ዘመን ላይ እንገኛለን ሲሉም ይመክራሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኩል ያለው ቀና ሀሳብ በካድሬዎቻቸው ዘንድ እንኳ ተቀባይነት እንዲኖረው ለለውጥ የተመቸ ሁኔታ መፍጠሩ ላይ በጣም ይቀራል የሚሉት አቶ አንዷለም ኢህአዴግ ራሱ ችግሩን ቢፈታ ለለውጡ አንዱ እገዛ ይመስለኛል ይላሉ።

በአመራር በኩል የሚደረግ ለውጥ የተወጠረውን ሊያላላና የተፈጠረውን መቋሰል ሊያሽር እንደሚችል ሃሳብ የሚሰነዝሩት ዶ/ር ዳኛቸው ህወሓትን የሚመሩት ሰዎች ለረጅም ዘመናት የቆዩ መሆናቸውን በሚተቹት ወጣቶችን ወደ አመራር የሚያመጡ ከሆነ ብዙ ነገሮች የሚለወጡና የሚሰክኑ ይሆናሉ ብለው ያምናሉ።

የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች አብረው ባይቀጥሉ ምን ይሆናል?

በኢህአዴግ ታሪክ “በዚህ መልኩ ወደ አደባባይ ወጥቶ አንዱ ሌላውን መተቸት የመጀመሪያ ነው። ይህ ደግሞ ምን ያህል ስር የሰደደ ችግር በመካከላቸው እንዳለና የሃገሪቷ እጣ ፈንታ አደጋ ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና።

አቶ አንዷለም ደግሞ አሁን ባለው አሰላለፍ ህወሓት ከግንባሩ ቢወጣ እንኳ ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አብረው ይቀጥላሉ የሚል ሀሳብ አላቸው። ስለዚህም በቅርብ ርቀት “ሌሎቹን አባል ፓርቲዎች ያጣበቀው ሙጫ ይላቀቃል” ብሎ እንደማያስብ ይናገራሉ።

“ያ ሙጫ የስልጣን፣ የዓላማ ወይንም ሌላ ሊሆን ይችላል” የሚለው አንዷለም የተወሰነ ጊዜም ቢሆን አብረው እንዲጓዙ እንደሚረዳቸው ያሰምርበታል።

በአንድ ጊዜ በአንድ ሃገር ውስጥ ሁለት መንግሥት ሊኖር አይችልም የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው “መጥራት ያለበት ነገር ይጠራል” በማለት “ህወሐት ሁሉን ነገር ተቆጣጥሮ ስለያዘው የምንሰማው የእነሱን እንጂ የትግራይን ህዝብ ድምጽ አይደለም የህዝቡ ድምጽ ታፍኗል” ይላሉ። ስለዚህ ህዝቡ እዚህ ውስጥ ስለሌለበት ወደ እርስ በርስ ግጭት የሚወስደን ነገር እንደሌለም ያምናሉ።

የትግራይ ህዝብ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ያፈነግጣል የሚል ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም ጉዳዩ ፓርቲው ጋር ነው ያለው” በማለት ይናገራሉ።

“የትግራይ ህዝብ ፍትህን ያውቃል ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ይወዳል ስለዚህ የህወሓት የበላይነት እንዲቀጥልለት ወደ ጦርነት ይገባል ብዬ አላስብም” በማለትም በህዝቡ ላይ ያላቸውን ተስፋ ይገልፃሉ።

ህወሓት እያለመ ያለው የሚመስለኝ በሽግግሩ ላይና በሽግግሩ ሂደት ብቻ ሳይሆን ከሽግግሩ በኋላ ሊኖረው የሚችለውን ነገር ጭምር ይመስላል የሚለው አንዷለም “ሌላ አይነት የፖለቲካ ቀመር ለማምጣትና ይመቹኛል የሚላቸውን አጋሮች እየፈለገ” ይመስለኛል ይላል።

“ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች፤ ሕዝቧም ትልቅ ነው” የሚለው አንዷለም “ያለንበት ችግር የተወሳሰበ ቢሆንም የማይለያይ የተቆራኘ ማንነት አለን ብዬ አምናለሁ” በማለት የኢትዮጵያ ሁኔታ ችግር አይገጥመውም ባይባልም ችግሩን የማለፍ አቅም አለው ብሎ እንደሚያምን ያስረዳል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *