አዴፓ ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለኢትዮጵያ አንድነት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የሥራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴው በክልሉ ወቅታዊ እና በለውጥ ስራዎች ላይ ሲመክር ሰንብቶ ዛሬ ሐምሌ 08/2011 ዓ.ም መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በሁለቱም መድረኮች ባለፈው አንድ ዓመት ከታዩ ለውጦች እና ችግሮች ፣ምን እንማር? በሚሉ ጉዳዮች ላይ መክሮ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ለውጡ ከመታየቱ በፊት የመደራጀት፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የታገደ እንደነበር አስታውሰው የለውጡ ሂደት የዴሞክራሲ ምኅዳርን ማስፋት ላይ ያተኮረ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የዴሞክራሲው ምኅዳር በየትኛውም አቅጣጫ እንዳይደናቀፍ መሠራቱንና ለአማራ ሕዝብ ጥያቄ ትርጉም ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለውጡን በመምራት በኩል ጉድለቶች ነበሩ ያሉት አቶ አብርሃም የሰላም እጦት፣ የህግ የበላይነት አለመከበር፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ግጭት እና ጸረ-ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መከሰት እና ወደ ክልሉ የሚገቡ ባለሀብቶች አስተማማኝ ዋስትና ማጣትን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ሰኔ 15 /2011 ዓ.ም የተፈጸመው ድርጊት የህግ የበላይነት አለመከበር የመጨረሻውን ጫፍ የነካበት እንደነበር የተናገሩት አቶ አብርሃም ክልሉ ከፍተኛ ፈተና ገጥሞት በጽናት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡ በመሪዎቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ለአማራ ሕዝብ የመጨረሻው አስጸያፊ እና አሰቃቂ ድርጊት እንደነበርም ነው ያስታወሱት፡፡

አዴፓ እና የክልሉ መንግስት ሕዝቡን ማዕከል አድርገው ህግን የማስከበር ሥራ አጠናክረው እንደሚሰሩና በማንኛውም ሚዛን ህግ እንዲጣስ አድል የሚሰጥ የፖለቲካ ስርዓት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

ለህግ የበላይነት መከበር የክልሉ ሕዝብ ከፍተኛውን ኃላፊነት ይወስዳል ያሉት አቶ አብርሃም የክልሉን ሕዝብ አንድነት ማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የክልሉን ሕዝብ ለመነጣጠል በሚጥሩ አካላት ላይ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ቁጥጥር እንደሚደረግም ነው የተናገሩት፡፡

የክልሉን ልማት ለማፋጠን እና ለስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት እንደሚሰጠው፣ በገበያ ላይ የሚታየውን አሻጥር ለመቅረፍም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥር እንደሚደረግበት አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በተጀመሩበት ሂደት እንደሚቀጥሉ የተናገሩት አቶ አብርሃም ‹‹የክልሉን ሕዝብ ወክለን ስንቀመጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን የመሸፋፈን ሥራ ልንሰራ አንችልም፤ ለሕዝብ ጥያቄ የምንሰራ የሕዝብ ልጆች ነን፤ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች የማንደራደርባቸው እና ትግል የምናደርግባቸው ናቸው›› ብለዋል፡፡

‹‹ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ከተፈጠረው ችግር በኋላ አማራን ለመከፋፈል የሚታትሩ አካላት አሉ፤ በተለይም ከክልሉ ውጭ ያሉ አካላት የአማራ ክልል ሕዝቦች እንዲዳከሙ ሲጥሩ ተስተውለዋል፤ የእነዚህ ጸረ አማራ ተግባር የሚሳካው ሕዝቡ በሰጡት አጀንዳ እና በሚፈልጉት መንገድ ሲፈስላቸው ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡ ሕዝቡም አንድነቱን እንዲያስጠብቅ መክረዋል፡፡

የአማራን ሕዝብ ለማዳከም የሚደረግን ማንኛውም ጉዞ በመከታተል እርምጃ እንደሚወሰድም ነው አቶ አብረሃም ያሳሰቡት፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው የሃሰት ትርክት ትክክል እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና አጋር ፓርቲዎች እያረጋገጡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹ለአማራ ሕዝብ ህልውና፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት እና ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን›› ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ፓርቲው የአማራ ሕዝብ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በጽናት እንደሚታገልም ነው የገለጹት፡፡

ምንጭ፦ አብመድ fbc

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *