ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በአዲስ አበባ ወደ ጎዳና እና ወንዞች የሚለቀቁ ፍሳሾችን መቆጣጠር የሚያስችል ህግና ደንብ እየተዘጋጀ ነው

በአዲስ አበባ ከመኖሪያ ቤት፣ ከሪል ስቴትና ከሆስፒታል ወደ ጎዳና እና ወንዞች የሚለቀቁ ፍሳሾችን መቆጣጠር የሚያስችል ህግና ደንብ እያዘጋጀ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሸን አስታወቀ።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም፥ ጽዳትና ውበት የከተማዋ መገለጫ መሆን አልቻሉም።

በተለይም ክረምትን ተከትሎ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከሪል ስቴትና ከሆስፒታል ወደ ጎዳና እና ወንዞች በሚለቀቁ ፍሳሾች ከተማዋ ስትበከል ይታያል፤ ይህም በነዋሪዎች ጤና ላይ እክል ሲፈጥር ይስተዋላል።

ችግሩን አይቶ ማለፍ እና ጉዳዩን የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጣቸው አካላት አስገዳጅ እርምጃ አለመውሰድም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ ባለፈም ተጠያቂነትን ማስፈንና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ የሚያስችል ህግና ደንብ አለመኖሩም ለችግሩ መንስኤ በሆኑ አካላት ላይ እርምጃ እንዳይወሰድ አድርጎት ቆይቷል።

የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ከተቋማት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ ይሰራ እንደነበር ጠቅሶ፥ አሁን ላይ ችግሩን መቆጣጠር የሚያስችል ህግና ደንብ እየተዘጋጀ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኢንጂነር አለም አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ጎዳና እና ወንዞች የሚለቀቁ ፍሳሾችን መቆጣጠር የሚያስችል ህግና ደንብ እየተዘጋጀ ነው።

ህግና ደንቡ በ2012 ተጠናቆ ወደ ተግባር እስከሚገባ ድረስም ለኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ቁጥጥር ይደረጋልም ነው ያሉት።

ከመኖሪያ ቤቶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ባለፈም፥ ኢንዱስትሪዎች በሚለቁት ተረፈ ምርት ብክለት እንዳይፈጠር ማጣሪያ እንዲገነቡ መደረጉን አስታውሰው፥ በዚህ ረገድም ኮሚሽኑ ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የቆዳ ፋብሪካዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፥ ማጣሪያ ሳይኖራቸው በሚሰሩ ነባር የቆዳ ፋብሪካዎች ላይም ኮሚሽኑ የማሸግ እርምጃ መውሰዱን አስረድተዋል።

ከወንዞች ልማት ጋር ተያይዞም የመጀመሪያው የሙከራ ፕሮጀክት የሆነው የሸራተን ማስፋፊያን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በታሪክ አዱኛ – (ኤፍ ቢ ሲ)

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ