በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን) የክልል እንሁን ጥያቄን በአግባቡ መምራት ላይ ያለው ክፍተት ካልተፈታ አገሪቱን ለከፋ አደጋ እንደሚያጋልጣት የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ።

የፖለቲካ ምሁር የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደሚናገሩት፤አዴፓና ህወሓት ከተቋቋሙ ረጅም ዓመት ሆኗቸዋል።አብረውም መሥራት ከጀመሩ እንደዚያው።ሄደው ሄደው ግን ወደበለጠ አንድነትና መዋሃድ ሳይሆን ወደ መለያየትና መፈረካከስ የሚወስድ መንገድ እየተከተሉ ነው።ይህ ችግር ካልተፈታ ደግሞ በቀጣይ አገሪቱን ወዳልተፈለገ አዘቅት ውስጥ ሊከታት ይችላል።

እንደ አቶ ልደቱ ገለጻ፤ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በነበረውና ለዚህ ለውጥ ምክንያት በሆነው የህዝብ ትግል ምን ዓይነት ጥያቄዎች ተነሱ? ህዝቡስ ምን ይደረግልኝ፣ ምን ይለወጥልኝ አለ? የሚለውን በደንብ አድርጎ ለመመለስ መሞከር መፍትሔ ያመጣል። ለውጡም ይህንን የረሳው ይመስላል። አንደኛ ‹‹እኔ ብቻ ነኝ›› መፍትሔ የማመጣው ብሎ ሁሉንም ነገር መቆጣጠሩ ስህተት ነው። ሁሉን አቀፍ የሆነና አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ኃይል ማሰባሰብና አብሮ መሥራት አለበት።

በህገ መንግሥቱ መሰረት የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ አካላት መብት አላቸው የሚሉት አቶ ልደቱ፤ ነገር ግን ይህ የክልል እንሁን ጥያቄ የት ቦታ ነው መቆሚያው የሚለው መታየት እንደሚገባው ይናገራሉ። ስለዚህ ይህ ጉዳይ እየተበረታታ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርብ ከሆነ እንደ አገር ሰባ እና ከዚያ በላይ ክልሎች ሊኖሩን እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የክልል መሆንን መብት ካገኙም በኋላ ጥያቄያቸው ይቆማል ማለት አይደለም የመገንጠል መብት ሊጠይቁ እንደሚችሉ ያመለክታሉ። ህገ መንግሥት የሚረቀቀውና የሚጸድቀው አገርን ለማፍረስ ሳይሆን የአገርን አንድነት ለማጽናትና ለማረጋጋት እንዲሁም ህዝብን አንድ አድርጎ ለመቀጠል ነው። የአገሪቱ ህገ መንግሥት የረቀቀውና የጸደቀው ግን ከዚህ በተቃራኒ መሆኑን እየመጡ ያሉ ጥያቄዎች ማሳያ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ዳንኤል መኮንን እንደሚናገሩት፤ በኢህአዴግ ውስጥ የሚገኙት ሦስት ድርጅቶች ውስጥ የተከሰተውን ሁኔታ በአፋጣኝ መፍታት ካልተቻለ አገሪቱን ስጋት ውስጥ ይከታታል። በአዴፓና በሕወሓት መካከል ያለው ሲታይ ሕወሓት ከዓመት በፊት የራሱን መንገድ ይዞ እየሄደ ያለ ፓርቲ ነበር።

አዴፓ ደግሞ የነበሩበትን ችግሮች ለመፍታት እየሠራ ይገኛል። በዚህ መካከል ግን ነገሮች ተካረዋል። ከለውጡ መምጣት በኋላ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ክፍተቶች ይታያሉ። እንደበፊታቸው አብረው መሥራት አቅቷቸዋል። ይህ ደግሞ ወደ ቃላት ጦርነት ወስዷቸዋል።

“ደኢህዴን በበኩሉ የራሱ ውስጣዊ ችግሮች አሉበት፤ በዚህም ክልሉን ማስተዳደር እያቃተው ይገኛል” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በደቡብ ውስጥ ክልል እንሁን የሚሉ ጥያቄዎች በመብዛታቸው ክልሉ መረጋጋት እንዳቃተው ይገልጻሉ። የአዴፓና የሕወሓት ሁኔታ የስልጣን ሽኩቻ ወይም ፉክክር ሲሆን ቀድሞ የነበረ አለቃና ምንዝር የነበሩ ድርጅቶች ዛሬ እኔ ነኝ መሪ የሚል ፍትጊያ ውስጥ መግባታቸው አደገኛ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

እንደ አቶ ዳንኤል ማብራሪያ፤ የደኢህዴን ጉዳይ ውስጣዊ ችግር ሲሆን በተለይ አስተዳደሩ በህዝቡ ዘንድ ቅቡል ያለመሆን ነገር ይታያል። አዴፓና ሕወሓት ግን በህዝቦቻቸው ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት አላቸው። በደቡብ አንዳንድ ወረዳዎች ለዞን ታዛዥ ያለመሆን ነገር አለ።ይህ እንደ ፓርቲ ሲወሰድ በጣም አስቸጋሪ ነው።በዚህም ኢህአዴግ በአግባቡ እየመራ አይደለም ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

በቀጣይ ይህ ሁኔታ ከቀጠለ አስፈሪ ነው። ምክንያቱም ኢህአዴግ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ሆኖ አገር እያስተዳደረ እንደመሆኑ መጠን በጥምረቶቹ መካከል ክፍተት ከተፈጠረ ወደመጡበት ክልል የመመለስ ሁኔታዎች ስለሚኖሩ የደህንነት ስጋት ይፈጥራል።ስለዚህ ሦስቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ችግር የኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ጭምር ነው።ስለዚህ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ኢህአዴግ ተቀምጦ መወያየት መቻል አለበት።

ህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ(ሕወሓት) ድርጅታዊ ስብሰባው ካደረገ በኋላ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። ህወሓት በመግለጫው አዴፓ በክልሉ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነት ወስዶ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ሲል አዴፓ በበኩሉ ህወሓት በአገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች ዋነኛ ተጠያቂ መሆን አለበት በማለቱ ከፍተኛ ውጥረት ነግሦ እንደነበር ይታወቃል።

በዚህም ሁለቱ ፓርቲዎች አብረው መቀጠል እንደማይፈልጉም በመግለጫቸው አሳውቀዋል።የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን) በሚመራው ክልል ውስጥ የሚገኙ አስር የሚሆኑ ዞኖችም ክልል መሆን አለብን የሚለውን ጥያቄ እያነሱ በክልሉ ላይ የሰላም ስጋት ፈጥሯል።

እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ የኢህአዴግ ውስጥ ያሉት አራቱ ፓርቲዎች አብረን አንቆይም ብለው ከተበተኑ የመንግሥት መውደቅ ይከሰታል።ከአራቱ ውስጥ ሦስቱ አንፈልግም ብለው ቢወጡ ከፍተኛ ድምፅ ያለው መንግሥት ለመመስረት ግዴታ 51 በመቶ ድምፅ ያስፈልገዋል።

በአሁን ወቅት ከአራቱም የትኛውም ፓርቲ ይህንን አያሟሉም።መንግሥት ከመመስረት ፍልስፍና ተወጥቶ ሁኔታው ቢታይ የተሻለ ይሆናል።ፓርቲዎቹ የሚወክሉት የራሳቸውን ብሄር ነው።አንዱ ፓርቲ ከሌሎች ጋር ሆኖ መንግሥት ቢመሰርት እንኳ አገሪቱ ወዳልሆነ መንገድ ታመራለች።በአገሪቱ ያሉት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሲሆኑ ፌዴራል መንግሥቱ በጥምር ቢያዝ ክልሎች ወደ ኮንፌዴሬሽን ሊገቡ ይችላሉ።ስለዚህ ከአራቱ አንዱ ቢወጣ ክልሉ ሄዶ መንግሥት ስለሚመሰርት ከፍተኛ ስጋት ሊፈጥር ይችላል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2011

መርድ ክፍሉ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *