‹‹ከነባር ተገዳዳሪዎቻችን እና ከአዳዲስ ተስፈኞች የሚመጣውን ዙሪያ መለስ ፈተና በጽናት አልፈን የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማስጠበቅ የማንከፍለው መሰዋዕትነት የለም፡፡›› አቶ ተመስገን ጥሩነህ

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሰይሟል፤ ርዕሰ መስተዳድሩ ኃላፊነታቸውን በቃለ መሐላ ከተረከቡ በኋላም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በንግግራቸው ዳስሰዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹ኃላፊነቴን ስቀበል ግለሰባዊ ጥቅምን እና ክብርን ወደጎን በመተው ለሕዝብ ክብር ለመሥራት ነው›› ብለዋል፡፡ በሰኔ 15 ቀን ተከስቶ የነበረው ድርጊት በሕዝቡ እና በፀጥታ ኃይሉ ርብርብ መክሸፉን አስታውሰው መሪዎቹ የከፈሉት መሰዋዕትነት ታሪክ የማይረሳው የጀግኖች ገድል እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ጥፋቱን ለመቆጣጠር መሰዋዕትነት ለከፈሉ የፀጥታ ኃይል አባላት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ዕውቅና እንደሚሰጥና ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ከእኔ ቀድመው ሀገራችን ሲያስተዳደሩ የነበሩ መሪዎች ጀግኖች ነበሩ፤ ሀገራቸውን የማያስደፍሩ፣ ዓለም የሚደነቅበት ቅርስ ጥለው ያለፉ ጠቢባን፣ ብልሆች፣ ሥርዓትና ማዕረግ ያበጁ ብልሆችና በፍርድ አሰጣጥ ሂደት የተካኑ ነበሩ›› ብለዋለው የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት እያመሠገኑ እንደሚወጡት ቃል ገብተዋል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ‹‹እንኳን ሰው ወፍ አልመድላሁ›› የሚል ጀግናና አቃፊ መሆኑን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹ከየትም የሚመጣን ተማሪ በማንነቱ ሳያገልል እንጀራ እና ዕውቀት ሲመግብ የኖረ ነው፤ ዝምታው ከንግግሩ በላይ የሚያስፈራ፣ ትዕግስቱ እንደጣና ሰፊ፣ ታሪኩ እንደ ዓባይ ረጅም፣ ጥበቡ እንደዋድላ ቅኔ የረቀቀ፣ … የቱባ ባሕል ባለቤት ነው›› ብለዋል፡፡ ሕዝብ በቁርጠኝነትና በሚመጥነው ልክ መሪ እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ መለያዬት ሳይሆን አንድነት፣ ግለኝነትን እና ጀብደኝነትን ሳይሆን አብሮ መኖር እና እኩልነትን በማስፈን የጋራ ችግርችን በጋራ ለመፍታት የሚጣርበት ወሳኝ ጊዜ ላይ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ ‹‹ወቅቱ የችግር ቢሆንም የማንወጣው ፈተናና የማናልፈው ስንክሳር አይኖርም›› ነው ያሉት፡፡ የክልሉ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ደራጃ በደረጃ እንደሚፈቱም አስታውቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ ትኩረት የሚደረግባቸውን ሐሳቦችም በንግግራው አንስተዋል፡፡ ‹‹ቀጣይነት ያለው ሠላም ለሕዝባችን ሁለንተናዊ ዕድገት እና ለልማት መሠረት የሚጣልበት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የሠላም መናጋት፣ በቀልን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች፣ መፈናቀሎች የማኅበረሳባችን ሥርዓት ሲያናጉ ቆይተዋል›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፡፡ በየአካባቢው የሚፈጸሙ ተራ ወንጀሎች እየሰፉ በመምጣታቸው ለክልሉ ስጋት መሆናቸውንና ሲሰበክ የነበረው የውሸት ትርክርት አሁንም የአማራን ሕዝብ ለፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም የሚጥር እንዳለ አመላካች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት እንደማይዳርጉና ጥያቄዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተባበሩ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የሕግ የበላይነትን ማስፈን የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ወሳኝ ተግባር ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ሕዝቦች ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ያላቸው መስተጋብር ዘላቂ እንዲሆንም በትኩረት እንደሚሠራ አስገንዝዋል፡፡

Image may contain: one or more people, people sitting and indoor

ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ የክልሉን ሰፊ ሀብት ለሰፊው ማኅበረሰብ ለማዳረስም በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ 
‹‹ክልላችን የአፍሪካ የውኃ ማማ ሆኖ ሳለ ዛሬም ድረስ በዝናብ ብቻ ጥገኛ የሆነ አርሶ አደር አለ›› ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደራጃ የሚካሄዱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንዳሉ ሆነው የሥራ ዕድል ፈጣራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ድህነት ተኮር ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ‹‹የቢሮክራሲ አሠራሮችን በማስቆም የክልሉ ተቋማት እንደ አንድ ይቆማሉ›› ነው ያሉት፡፡

በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጨምሮ የቡሬ እና የሞጣ የግብርና ምርቶች ማቀነባሪያዎች በፍጥነት ተገንብተው ወደሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ የመሠረተ ልማት እና የመንገድ ግንባታ በትኩረት እንደሚሠራ እና ዲስፖራው ወደ ክልሉ ገብቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
‹‹ክልላችን ወደላቀ እምርታ ለማሸጋገር የሚጥሩ ምሁራንን አቅም አሟጠን ለመጠቀም ዝግጁ ነን›› ያሉት አቶ ተመስገን ‹‹በክልሉ ያሉ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን እናስተዋውቃልን፤ አመች እንዲሆኑም እንሠራለን›› ብለዋል፡፡

‹‹ያለው የለውጥ ጉዞ ስንዴ እና እንክርዳዳድ ይዞ መጥቷል›› ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ‹‹ስንዴውን እየተንካከብን እንክርዳደሩን እየነቀልን እንቀጥላለን፡፡ እንክርዳዱን ስንንቅል ስንዴውን እንዳንነቅል ጥንቃቄ እናደርጋለን›› ነው ያሉት፡፡ ‹‹ከነባር ተገዳደሪዎቻችን እና ከአዳዲስ ተስፈኞች የሚመጣውን ዙሪያ መለስ ፈተና በጽናት አልፈን የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማስጠበቅ የማንከፍለው መሰዋዕትነት የለም›› ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፡፡ የክልሉ አርሶ አደሮቹ ሀገራችን እና የክልላችን የህልውና መሠረቶች እንደሆኑ ገልጸው ‹‹የአካባቢችሁን የሠላም ጉዳይ ለድርደር እንዳታቀርቡ›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለአፍታም ከአጠጋብቸው እንደማይለይም ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹ከእናንተ ውጭ ምንም ነን፡፡ የእናንተ ጥበብ አሸናፊ ነው፤ የበጎ ነገር መነሻዎች እናንተ ናችሁ፡፡ በክልላችን የደረሰብንን ችግር እንደትታገሉ አደራ እላለሁ›› ሲሉም ለአርሶ አደሮች ጥሪ አቅበዋል፡፡

‹‹እናንተ ያልተሳተፋችሁበት ታሪክ የለንም፤ ከእናቶቻችሁ በወረሳችሁት አስተዋይነት እና ጥበብ የክልላችን ችግር እንደትፈቱ አደራ›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለፀጥታ ኃይሉ አባላትም ‹‹የሚፈጠሩ ችግሮችን በሕዝብዊ ወገኝተነት እንድትታገሉ›› ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብና መንግሥትም በየትኛውም የግዳጅ ስምሪት ከጎናችሁ አይለይም ብለዋል፡፡ የተፎካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እህት ድርጅቶች እና ሌሎችም ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲሠሩ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ለታላቁ የአማራ ሕዝብ እና ለታላቋ ኢትዮጵያ ስንል ታላቅ እና የሚያኮራ ሥራ እንሠራለን›› ያሉት አቶ ተመስገን ለሀገረችን ክብር ስንል ጥርስ እና ከንፈር እንጂ ዓይን እና ናጫ፣ የምንደጋገፍ እንጂ የምንነቃቀፍ መሆን አይገባንም፤ የምንተባበር እንጂ የምንሰባበር መሆን አይጠበቀብንም›› ብለዋል፡፡ ‹‹በግ ባለበት ተኩላ ዶሮ ባለበት ሲላ እንደማይጠፋ የታወቀ ነው›› ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ገና ለገና መሰዋዕትነት ያስከፍለናል ተብሎ በዝምታ የሚታለፍ ጉዳይ እንደማይኖርም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ወፍ ፈርተን ዘንጋዳ ሳንዘራ የምንቀር ሞኞች አይደለንም›› ብለዋል፡፡ 


የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ልምድና ቀደምት ግለ ታሪክ በጨረፍታ፡

አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወረዳ ወይራ ቀበሌ ነው የተወለዱት፡፡ ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ፌዴራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል፡፡

በትምህርት ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀያቸው በጎተራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የመለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በብቸና በሚገኘው የበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ዘርፍ እና የሁለተኛ ዲግሪቸያውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በአማራ ክልል እና በሀገር ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፤ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሠርተዋል፡፡ 
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መስሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነትም አገልግለዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ  አማራ መገናኛ 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *