ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአዴፓ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንንን በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዓለ ሲመት ላይ ያደረጉትን ንግግር በድምጽ መስማት ያልቻላችሁ ተከታታዮቻችን በጠየቃችሁት መሠረት ሙሉ መልዕክታቸውን በጽሑፍ አቅርበናል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በዓለ ሲመት ላይ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት፡፡ 
ባሕር ዳር ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም 
ክቡራት እና ክቡራን
ሁላችንም እንደምናስታውሰው . . . ከዛሬ አምስት ወራት በፊት በዚህች ውብ ከተማ በዚሁ ቦታ የወንድማችንን የዶክተር አምባቸው በዓለ ሲመት ሥነ-ስርዓት ላይ አብረን ታድመናል፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ማንኛችንም ባልጠበቅንበት ሁኔታ የጓደኞቻችንን ሕይወት ስንነጠቅ በመሪር ሐዘን ውስጥ ወድቀን እንባ ተራጭተናል፡፡
ነገር ግን . . . እንባ ተራጭተን፣ ሐዘን በብርቱ ክንዱ ደቁሶን፣ አንገታችንን ደፍተን አልቀረንም፡፡ አባቶቻችን ያወረሱንን ብልሀት ተጠቅመን፣ የሕዝባችንን ብርቱ የድጋፍ ድምፅ አክብረን፣ የአማራ እናት ማኅፀን የመሪ መካን አለመሆኗን ለማብሰር ዳግም ተገናኝተናል፡፡
ከሳምንታት በፊት ቅስም ሰባሪ ሐዘን ቢገጥመንም ከጥቁሩ ደመና በስተጀርባ አንዳች ተስፋ ይታየን ነበር፤ ዛሬም የአማራ ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድም ሕዝቦች ጋር ሆኖ ለታላቅ የእናት ሀገር ግንባታ ይዋደቃል፡፡ የጀመርነው ትግል . . . እንዲሁ በቀላሉ በጓደኞቻችን ሞት የሚደናቀፍ ጉዞ እንዳልሆነ ሁሉም ያውቃል፡፡
የሕዝባቸውን ሕይወት ለማሻሻል ሌት ተቀን ሲውተረተሩ በአጭሩ የተቀጩ ጀግኖቻችን ሁሌም በልባችን የተስፋ ፈርጦች እና አብነቶች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ ሕልፈት በኋላ ሕይወት ይቀጥላል እና … እነሆ በአዲስ የቁጭት መንፈስን ተነሳስተናል፡፡

አንዳንድ ፀሐፍት እንደሚሉት ኅብረተሰብ የሚያገኘው የሚገባውን መሪ ነው፡፡ መሪዎች የቱንም ያህል ታላቅ ሐሳብ ቢፀንሱ ካልታገዙና ካልተበረታቱ እጀ ሰባራ ይሆናሉ፡፡ መሪዎች ሲያጠፉም ጭምር የመሳሳት ዕድል በመስጠት በጊዜ ሂደት እየካበተ የሚመጣ የመሪነት አቅም እንዲገነቡ ልንፈቅድ ይገባል፡፡ 
መሪነት የልምምድ፣ የትጋት እና የመማር ውጤት እንደሆነው ሁሉ፤ መሪዎቹን የተረዳና ያላንዳች ስስት ትልልቅ ሐሳቦች ወደ ተጨባጭ ኅልው ሐሳቦች እንዲቀየሩ የኔ የሚሉት ኅብረተሰብ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በዚህ ዘመን ‹‹ለመሪነት የተፈጠረ ሰው›› ብሎ ነገር የለምና በአሁን ጊዜ በመሪነት እየተሳተፍን ያለን አመራሮች … ገና ከሕጻንነት ጀምሮ ለመሪነት ተዘጋጅተን የመጣን አልጋ ወራሾች አይደለንም፡፡ 
ስለሆነም መሪዎች የሚነሱትም ሆነ የሚወድቁት በኅብረተሰብ እንቅስቀሴና ጥያቄ ዙሪያ በሚፈጠሩት እርካታዎች ባሉ አሉታዊ እና አዎንታዊ ሚና በመሆኑ ለመሪዎቻችን ስኬታማነት ኅብረተሰቡ ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡

ክቡራት እና ክቡራን
በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ በእርካታ የሐዘን እና የፍስሐ ዘመናትን ዓይተናል፡፡ ተርበናል፤ ታርዘናል፤ በርካታ የደስታ ዘመናትን አሳልፈናል፤ በነፃነት ጮራ በዓለም አደባባይ ላይም ለአፍሪካ ቆመናል፡፡ በአጭሩ አግኝተን አጥተናል፤ ነገር ግን በዚህ ረጅም የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ሁሌም የኛ ሆነው የቀጠሉ ቀንዲሎች አሉ፤ ከነዚህም ዋነኞቹ ሀቀኝነት እና የሞራል ልዕልና ናቸው፡፡
አንደ ኅብረተሰብ ተሳስሮ የሚገመደው በሞራል እሳቤዎቹና እሴቶቹ ነው፡፡ ትክክል እና ስህተት ወይም እውነት እና ሀሰት ብለን በነገሮች ላይ ግለሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ብያኔዎችን የምናሳልፈው በእነዚህ አስተሳሰቦች ላይ ተመርኩዘን ነው፡፡

የሞራል እሳቤዎቻችን እና እሴቶቻችን የማኅበራዊዊ ጉዞ መነሻ እና መድረሻ የሚያሳዩ ካርታዎች ናቸው፡፡ አንድ ኅብረተሰብ እነዚህን ያጣ ዕለት መነሻ እና መድረሻውን ሳያውቅ ወደ ሩቅ ሀገር ለማቅናት የተነሳ፣ ቅጣንባሩ የጠፋበት ማኅበረሰብ ነው የሚሆነው፡፡
የአማራ ሕዝብ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የሞራል እሳቤዎች እና እሴቶችን የተላበሰ ማኅበረሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ያጋጠመንን ከባድ ችግርና ኪሳራን በእጅጉ በሚቀንስ እና ማኅበረሰቡን ከሚከፋፍሉ ነገሮች ራሱን ጠብቆ በጋራ ለመቆም አስችሎታል፡፡ 
ነገር ግን እነዚህ የኅልውና እና የማንነታችን መሠረት የሆኑ አንጡራ ሀብቶቻችን ነቅተን ካልጠበቅናቸው በዋዛ ፈዛዛ ከእጃችን ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ወቅት በጥቂቱም ቢሆን ከሩቁ እየታዩ ያሉት ምልክቶች የሞራል እሳቤዎቻችን እና እሴቶቻችን መሸርሸር ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡ ይህንን አዝማሚያ ገና ከማለዳው ልናርመው ይገባል፡፡ 
በመሆኑም እዚህ ያደረሱንና የምንታወቅበትን የሞራል ከፍታ ስለእውነት መቆምንና ሚዛናዊነትን በእጅጉ መጠበቅና ማጥበቅ ይኖርብናል፡፡ ይህንን የሚፈታተኑ አሰላፎችንና ውሎዎችን መግራትና ማከም ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ሁሉ ቁልቁለት ነው፡፡

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
እንደ ሀገር ምንም እንኳን የዚህ ቀጠና ዝሆን ብንሆንም አንድም ሀገር ወርረን አናውቅም፤ በወራሪዎችም ተደፍረን አናውቅም፡፡ ይሄ እውነታ በረጅም ታሪካችን ውስጥ ለሞራል ልዕልና ያለንን ቦታ በደማቁ ይናገራል፡፡ 
ይህን በውድ ዋጋ የጠበቅነውንና ከነጣቂዎችም ጭምር እየተከላከልን የኛ አድርገን ያቆየነው እሴት ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር ለትውልድ ልናሻግረው ይገባል፡፡
ጥላቻን፣ መገዳደልን፣ አሉባልታን ቅቡል የሚያደርግ አስተሳሰብ በእንጭጩ ካልተቀጨ፤ ዛሬ ማኅበረሳበዊ ባሕል እየሆነ የእያንዳንዳችንን ጓዳ እያንኳኳ ስለሆነ ጊዜ ሳይሰጠው ልናስቆመው፣ በእውነት አደባባይ ላይ ቆመን ልንፋረደው ይገባል፡፡ 
በዚህም እውነትና ፍትሕ ነግሠው፤ ዳር እስከ ዳር ለዜጎች የተመቸች፤ እኩልነት የሰፈነባት እና ዴሞክራሲ ያበበባት ሀገር የመገንባት ራዕይ ሰንቆ መጓዝ ይጠይቀናል፡፡ ወቅቱ ከዘረኝነት አጀንዳ ወጥተን የታላቅነት ትርክትና ራዕይ የምናውጀበት ወቅት ነው፡፡

በአመራር ታሪክ የቅብብሎሽ ሰንሰለት ውስጥ … በአስጨናቂ እና በአስቸጋሪ ጊዜ ሀገራቸውን ከማጥ መንጥቀው በመታደግ ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚወስዱ የጨለማ ጊዜ ብርሃኖች፤ የለውጥ አቀጣጣይ ኮኮቦች በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው፡፡ 
በኛ ምድር የተፈጠሩት ታላላቆቹ የሀገራችን መሪዎች ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ታላቅ ሀገር አስረክበውናል፡፡ ዛሬ በእርግጥም ከትናንት የተሻለ ቢሆንም መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች እየተጠላለፉ አገራችንን እና ክልላችንን እየተፈታተኑ ስለሆነ ትናንት ያጣናቸውን መሪዎች የሚተኩ አመራሮች መተካት የማይቀር የቤት ሥራችን ሆኗል፡፡
እነሆ ዛሬም ሕዝባችን የአመራር መካን ባለመሆኑ … የአመራሮቻችንን ኅልፈት ተከትሎ የተፈጠረብንን ክፍተት ለሟሟላት ተኪ አመራሮችን የማሟላት ሥራ አከናውነናል፡፡ 
በዚህ ወሳኝ የጉዞ ምዕራፍ ላይ የተተኩት አመራሮች እነ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ጓደኞቻቸው ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ከሕዝቡ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በስኬት እንደሚዘልቁ ሙሉ እምነት ያለኝ መሆኑንም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ 
የብርቱ አማራ አርሶ አደር ልጆች የሆኑት እነአቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ጓደኞቻቸው ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት በተግባር የተፈተኑ፣ በቀጣይ የክልላችንን ሕዝብ ስጋት፣ ፍላጎት እንዲሁም ቋሚ ጥቅም ለማስከበር ታጥቀው የተነሱ ናቸው፡፡
በዚህ ወቅት አመራሮቹ የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በውጤታማነት እንዲወጡ እና ከፊት ለፊት ለሚጠብቃቸው ብርቱ የለውጥ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆኑ ለክልላችንና ለታላቋ ኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የቆማችሁ ሁሉ ከጎናቸው እንድትሰለፉ ጥሪዬን ለማስላለፍ፡፡
ክቡራት እና ክቡራን!
በመጨረሻም በወንድሞቻችን ላይ በደረሰው ያልታሰበ ጥፋት ተከትሎ ክልላችን ከተጋረጠበት የሠላም እና የፀጥታ ስጋት በፍጥነት አገግሞ መደበኛ ሕይወት በተስፋ እንዲያንሰራራ ለተረባረባችሁ የክልላችን ሕዝቦች፤ የፌዴራል እና ክልል ፀጥታ አካላት እና የክልል መንግሥታት አመራሮችና ሕዝቦች ከልብ እያመሠገንኩ፤ ለአዲስ አመራሮች ውጤታማ
የሥራ ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

አመሠግናለሁ!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *