በሀገራችን አሁን ከተጀመረው የለውጥ ሂደት ጋር ተያይዞ እየተነሱ ያሉ ሰፊ የሕዝብ ፍላጎቶች አሉ። እነዚህም ውስጥ ከልማት፣ ሰላምን ከማስፈን፣ እራስን በራስ ከማስተዳደር፣ ከፍትሐዊነት አኳያ ሕገ መንግሥቱ ከሚሰጠው መብት ጋር ተያያዥ ናቸው። እነዚህ ፍላጎቶች ታዲያ አንዳንዴ ተገቢ በሆነም ባልሆነም መንገድ እየተገለፁ የሀገሪቱን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ ሲፈታተኑ ተስተውሏል። ከተጀመረው የለውጥ ሂደት ወዲህም እንደ ሀገር በርካታ ጥያቄዎች እየተመለሱ ያሉ ቢሆንም ግልፅነት እና ህጋዊነትን የሚጠይቁ ጥያቄዎችንም እንደ ባህሪያቸው ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ መሥራትም የከበደ ፈተና ሲሆን ይታያል።

እንደሚታወቀው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 56 ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ ነው። ክልሉ የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት ነው ። በተለይም ህዝቦቹ፣ በቋንቋ፣ በባህልና በማህበራዊ መስተጋብር የተሳሰሩና ለረዥም ጊዜ በአብሮነት የኖሩ አንድነታቸውንም ሰላማቸውንም ጠብቀው የዘለቁ እንደሆኑ የሚታወቅ ነው። የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ በተገኘው ነፃነት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኙ አንዳንድ ዞኖች ለዓመታት ያነሱት የነበረውን የክልልነት ጥያቄ መድረክ ይዘው ወጥተዋል።

እየገፉ የመጡትን ጥያቄዎች ለመመለስም የክልሉ መንግሥት ‹‹ዛሬ ያለ በቂ ጥናት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ነገ ሀገራዊና ታሪካዊ ስህተቶችን እንዳያመጡ ተጠንተው፣ የተመከረባቸውና የተዘከረባቸው ውሳኔዎችን እንዲሆኑ የክልልነት ጥያቄውን በሳይንሳዊ መንገድ ይጠኑ›› ሲል ወስኗል።

የደኢህዴን ውሳኔ ክልል ሆኖ ተደራጅቶ የመውጣት ጥያቄዎችን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ በመመለስ የፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ከመስጠት ከህዝቦች በመነጨ መሰረታዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ መልስ መስጠት እንደሚገባ በማመን 56 ቱንም ብሔረሰቦች ባሳተፈ መንገድ ጥናት ማጥናትና የህዝቦችንም ስሜት አዳምጦ መወሰን እንደሚገባ በድርጅቱ 10ኛ ጉባኤ ላይ ወስኗል። ድርጅቱ እንዲህ ባለ አብይ ጉዳይ ላይ በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፉ ውሳኔዎችን በመወሰን ስህተት ላለመሥራት ያደረገው ጥረትም ታሪካዊና አስተማሪም እንደሆነ የጥናት ቡድኑ አባላት ይናገራሉ።

ይህንንም ተከትሎ ማዕከላዊ ኮሚቴው አንድ ላይ በመሰብሰብ ውይይት በማድረግ ጥናቱ በምን መልክ መደረግ እንዳለበትና እንዴት ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ማካተት እንደሚቻል ከተወያየ በኋላ በሥራ አስፈፃሚው አማካኝነት የአጥኚው ቡድን እንዲቋቋም ተደረገ ።

የአጥኚው ቡድን አደረጃጀት

አጥኚው ቡድን የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚያውቁና በጥናት ዘርፍ ልምድ ያላቸውን አንጋፋ ምሁራንን ማቀፍ እንደሚገባም በማመን በዚሁ መሰረት ከዶክትሬት ዲግሪ /ፒ ኤች ዲ/ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው 20 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል። የጥናት ቡድኑ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያላቸው አባላትን ያቀፈ ለማድረግ ከአንትሮፖሎጂ፣ ከታሪክ፣ ከፖለቲካ ሳይንስ፣ ከሥራ አመራር፣ ከሕግ፣ ከፌደራሊዝም፣ ከልማት ጥናት የተውጣጡ ምሁራን እንዲካተቱ መደረጉን ቡድኑ አስታውሷል።

የጥናት ቡድኑ ካለማንም ጣልቃ ገብነት የራሱን ዕቅድ አውጥቶ በክልሉ ላይ ለሰባት ወራት የፈጀ ጥናት ካደረገ በኋላ የደረሰበትን ውጤት በማሰባሰብ ባገኘው ግብረ መልስ መነሻነትም ምክረ ሀሳቦችን አስቀምጧል፤ ለህዝብም ይፋ አድርጓል።

የጥናቱ ትኩረት በደቡብ ክልል የተነሳውን የአደረጃጀት ጥያቄ ለመፍታት ያለመ እንደመሆኑ የጥናት ቡድኑም ተከታዮችን ጥያቄዎች ይዞ ተነስቷል። የክልሉ አመሰራረት ታሪካዊ ዳራ ምን ነበር? ክልሉ ከተመሰረተ በኋላ የተገኙ ቱሩፋቶችና ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? አሁን ያለንበትን የለውጥ ሂደት ተከትሎም ሆነ ቀደም ብሎ ለተነሳው የአደረጃጀት ጥያቄ መንስኤው ምንድ ነው? ለተነሳው ጥያቄ እራሱ በክልሉ ውስጥ የሚገኘው ህዝብ ምን ሀሰብ ያቀርባል? የሚሉት ይገኙበታል።

የጥናቱ አጠቃላይ ሁኔታ

የአንድ ሳይንሳዊ ምርምር ተአማኒነቱ የሚረጋገጠው በዓለም የጥናት ምርምር ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን የምርምር ዘዴ ጥቅም ላይ በማዋል ውጤት ማግኘት ሲቻል ነው። አሁን በዓለም ካሉ ዋናዋና የጥናት ዓይነቶች ውስጥ ተጠቃሽ የሚሆኑት ዓይነታዊና መጠናዊ የጥናት መንገዶች ሲሆኑ እነዚህን የጥናት መንዶችን በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ በማዋል መረጃን መሰብሰብ እና መተንተን እንደተቻለ የጥናት ቡዱኑ አስታውቋል።

በተለይ አሁን በሀገር ደረጃ ያለው ድባብ እንደ አንድ ውሱንነት ታይቷል። በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖች መረጃ ለመሰብሰብ ተሞክሮ ከሀዋሳ ከተማና ከሲዳማ ዞን ከመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ ለመሰብሰብ እንዳልተቻለ የአጥኚ ቡዱኑ አሳውቋል። ሆኖም ግን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ የጥናት ዘዴዎችን ጥቅም ላይ በማዋል መረጃውን ምሉዕ ማድረግ ተችሏል። ሌላው ከዚህ ቀደም መሰል ጥናቶች በሀገሪቱ ባለመደረጋቸውና ይህም የመጀመሪያው በመሆኑ ሀገር በቀል የጥናት ተሞክሮዎችን የማየት ዕድል አለመኖሩ እንደ ውሱንነት ተጠቅሷል።

ይህ ጥናት አሁን ባለው ሳይንሳዊ ተሞክሮዎችና አስተምህሮቶች መሰረት ሊታይ የሚገባ መሆኑን በማየት በተለይ ዓለም ዓቀፍ ተዛማጅ ጽሑፎችንና መዛግብትን ለማየት እንደተሞከረ ተወስቷል። በዚህም መሠረት አሁን ባለው በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚጠኑ ጥናቶች ከዚህ በፊት ካሉ ማህበራዊ ሳይንስ ባይበልጥም ከፌደራሊዝም አስተምህሮቶች የጥኞቹ ሞዴሎች ናቸው ትክክለኛ መረጃ የሚሰጡት የሚለውን በሚገባ ለማየት ተሞክሯል። በመሆኑም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች፣ ልምዶችና ጽሑፎችን ለመቃኘት ሰፊ ቦታ ተሰጥቶታል።

ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው የዚህ ጥናት ዓላማ በደቡብ ክልል የተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች መነሻቸው ምን እንደሆነ በመለየት መልስ ለመስጠት ያለመ እንደመሆኑ በተገኘው መረጃ መሰረት የተለያዩ አራቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች የተሰጠውን ምላሽ ተተንትኖ ውጤቱ እንደሚከተለው አስቀምጧል።

የደቡብ ክልል አመሰራረት

አጥኚው ቡድን እንደገለፀው ክልሉ ላለፉት 27 ዓመታት ወደ ሕብረ ብሔራዊነት በመምጣት አንድ ክልል እንዲመሰረትና ወደ አንድነት ለመምጣቱም በርካታ ምክንያቶች እንደነበሩ አስረድቷል። በወቅቱ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት እንዲደራጁ የተደረገው ‹‹ዛሬ እየተባለ እንዳለው አንድ ላይ ጨፍልቆ ማንነትን ለማሳጣት ሳይሆን የክልሉ ምሁራን የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ አንድ ላይ መሆን ይበጀናል የሚል አቋም በመያዛቸው ነበር›› ሲል የአጥኚው ቡድን አስረድቷል።

ምሁራኑ አንድ ላይ ለመደራጀት ከመከሩባቸው ምክንያቶች ውስጥ የተወሰኑት ተጠቅሰዋል። በወቅቱ በክልሉ ውስጥ ውስን የሰው ሀብት መኖሩና ይህም በተወሰኑ ዞኖች ውስጥ ያለ መሆኑን በመረዳት በጋራ የሰው ሃይልን የመጠቀም ዓላማ የነበረው አደረጃጀት እንደነበር ተነግሯል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጥሮ ሀብትንም በጋራ የመጠቀም ዓላማ እንደነበር ተወስቷል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ አብዛኛዎቹ የክልሉ ህዝቦች በባህል፣ በቋንቋና በማህበራዊ አኗኗራቸው ጥብቅ ትስስር ያላቸው በመሆኑ ይህንን ቀረቤታና አንድነት አስጠብቀው ለመቀጠል በማሰብ እንዲሁም የፖለቲካ ተሰሚነታቸውንና በሀገር ጉዳይ ያላቸውን የመወሰን አቅም ለማጎልበት እንዲረዳቸው ምሁራን በአንድ ላይ መደራጀት መልካም እንደሆነ መክረው እንደነበር በጥናት መገኘቱን ቡድኑ ተናግሯል።

‹‹ክልሉን ለመጨፍለቅና ማንነትን ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው›› የተባለውም የተሳሳተ የግለሰቦች ሀሳብ መሆኑ ተነግሯል። ቡድኑ ስለክልሉ አመሰራረት ወደ ኋላ ሄዶ ያጠናበት ዋናው ምክንያትም ወደፊትም ክልሎች ሲመሰረቱ ውስንነቶችን ለማስቀረትና ልምድ ለማግኘት እንደሆነ የጥናት ቡድኑ አስረድቷል።

የተገኙ ትሩፋቶችና ተግዳሮቶች

የደቡብ ክልል መልካም እሴቶችን አጎልብቶ በመሄድ የህዝቦችን አንድነት አጠናክሮ ለመቀጠል በሚያስችል ሁኔታ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። በእነዚህ ጊዜያት ክልሉ አብሮ በመኖሩ ያገኛቸው ጥቅሞች ምንድናቸው የሚለውን ለማየት ተሞክሯል። በዚህም መሰረት በማህበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካው ዘርፎች የተገኙ ጥቅሞች እንዳሉ ለማረጋገጥ ተችሏል።

አሁን ያለው አስተሳሰብ እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙ ሰዎች ሲጠየቁ ‹‹ከደቡብ መጥቻለሁ›› ማለት ጀምረዋል ። ይህም አዲስ የደቡብ ማንነትና ሕብረ ብሔራዊነት እንደተፈጠረ አመላካች ነው። ይህንንም ዛሬ ከተፈጠረው ስሜት ውጭ ሆኖ በጣም ዝግ ባለና ሰከን ባለ መንፈስ ማየት እንደሚያስፈልግ ተነግሯል ። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የነበረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ተጠቃሚነትም ከፍ ወዳለ ደረጃ መሸጋገሩ በጥናት ቡድኑ ተነስቷል። በአመዛኙ በክልሉ የሚገኙ ብዙ አካባቢዎችም ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውና ተጠቃሚነታቸው አድጓል። ህዝቦች በሚፈልጉበት የክልሉ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የመሥራት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንደ ህዝብ ብዛቱም እንደቆዳ ስፋቱም በሀገሪቱ ካሉ ክልሎች ተወዳዳሪ የሆነ ትልቅ ክልል የተፈጠረ መሆኑ አንድ እምርታ እንደሆነ ከምላሹ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በዚህም የደቡብ ክልል ከሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ጋር በመሆን በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን የመወሰን ፖለቲካዊ አቅም እንዲኖረው አድርጓል። እነዚህ ቱሩፋቶች በክልሉ የተፈጠረው ሕብረ ብሔራዊነት ያስገኛቸው ውጤቶች መሆናቸውን መረዳት እንደተቻለም የጥናት ቡድኑ አስረድቷል።

በአጠቃላይ በአመሰራረቱ ጊዜ የነበሩ ዓላማዎች በየትኛውም ጊዜ ተቀባይነት ያላቸውና በጋራ የመጠቀምና የመበልፀግ መርህ ክልላዊ ወይም ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዓቀፋዊም አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግም ገለፃ ተደርጓል።

በሌላ በኩል ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ላይ ተሳስበው በመኖራቸው ምክንያት የተገኙ ትሩፋቶች መገኘታቸው እንዳለ ሆኖ በተለይ ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንፃር የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩም ማየቱን የጥናት ቡድኑ አመልክቷል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከልማት ተጠቃሚነት፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከፍትሐዊነት አንፃር የሚታዩ ክፍተቶች እንደነበሩም ከምላሻቸው መረዳት መቻሉን አጥኚ ቡድኑ አስረድቷል።

የክልልነት ጥያቄ መነሻ

ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት በከተማም ሆነ በገጠር የኢ-ፍትሐዊነት ጥያቄዎች ለሀገራችን የሰላም መደፍረስ ምክንያት እንደነበሩ ይታወቃል። እንደሌሎች ሀገሪቱ ክፍሎችም በደቡብ ክልል እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ሲነሱ መክረማቸው አይረሳም። ይህንን ተከትሎም በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ዞኖች እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።

የክልልነት ጥያቄዎች መንስኤያቸው ምን እንደሆነም ለማጥናት ተሞክሯል። በዚሁ መሰረት ጥያቄው ከአደረጃጀት ወይስ ፍትሐዊነትን ተከትሎ የመጣ ስለመሆኑ ጥናት ተደርጓል። የጥናቱ ውጤቱ እንደሚያስረዳውና ከአብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊዎች መረዳት እንደተቻለው ክልል የመሆን ጥያቄው ከአደረጃጀት ሳይሆን ከአሠራር ብልሽት የመነጨ ፍላጎት እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።

ይህ ማለት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ክልል መደራጀታቸው ምንም ዓይነት ችግር እንዳልፈጠረባቸው ነገር ግን ከዞን ዞን፣ ከአካባቢ አካባቢ እኩል የልማት ተጠቃሚነት ያለመኖሩ፣ የማዕከላዊ ከተማው መራቅ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖር የራስን ክልል የመፍጠር ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ከሰጡት መልስ መረዳት መቻሉን የጥናት ቡድኑ አስቀምጧል። በመሆኑም ጥያቄውን ያስነሳው በጋራ መደራጀቱ ሳይሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ የሚችል አሠራር አለመኖሩና ቢኖርም መተግበር ያልቻለ መሆኑ ነው።

ሕዝቡ ያስቀመጠው መፍትሔ

የክልሉ ህዝብ ክልሉ በጋራ መደራጀቱ ላይ ቅሬታ እንደሌለበት ከተሰጡት ምላሾች ማወቅ እንደተቻለ የጥናት ቡድኑ ገልጧል። አብዛኛዎቹ ምላሾች በኢ-ፍታዊነት የሚገለፁ ነገሮች መሻሻል አለባቸው የሚሉ አንድምታዎች እንዳሏቸውም አስረድተዋል። በተለይ አንድነቱን ለማስቀጠል ከተፈለገ የሥልጣን ክፍፍልን፣ የሀብት ክፍፍልን፣ መሰረተ ልማትን ፍትሐዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ሀሳቦች መሰንዘራቸውን ገልፀዋል። እነዚህን ችግሮች መፍታት ከተቻለ በጋራ መደራጀትን የሚጠላ እንደሌለና የመከፋፈል ምክንያት እንደሌላቸውም ከሰጡት መልሶች መገኘታቸውን የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል።

የጥናት ቡድኑ ምክረ ሐሳቦች

በመጨረሻም የጥናት ቡድኑ ከ17 ሺህ መላሾች በተሰበሰበው መልስ መሰረት አድርጎ የራሱን ምክረ ሐሳብ እንደሚያመለክተው ማንኛውም የህብረተሰብ አካል በወቅቱ ከሚንፀባረቀው ስሜታዊነት ወጥቶ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባውና ከአማራጭች የተሻለውን መምረጥ እንዲችል እራሱን ማዘጋጀት እንደሚገባው መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። በግልም በቡድንም በአመራር ደረጃም የሚወሰኑ ውሳኔዎች ታሪካዊ ስህተትን እንዳያስከትሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ቡድኑ መክሯል።

በሰነዱ ላይ ህጋዊ ውሳኔዎች ሆነው ታሪካዊ ስህተትን ያስከተሉና ዋጋ ያስከፈሉ ተሞክሮዎች መፈተሻቸውንና ከዚህ ተሞክሮ ተነስቶ አግባብ ያለው ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።

የፌደራል ሥርዓትን የሚከተሉ በርካታ አገሮች የጋራ አገር ሲገነቡ ያገጠሟቸውን ችግሮችና እነዚያን ችግሮች እንዴት እንደተሻገሩ ልምዳቸው ተቀምጧል። በተለይ በመጪው ትውልድና በህዝብ ላይ የሚወሰን ውሳኔ ግብታዊ መሆን እንደሌለበት ተመልክቷል።

ከማህበራዊ ሳይንስ፣ ከፌደራል አስተምሮና ዓለም ከሚያውቃቸው ሞዴሎች አፈፃፀም አንፃር ሲታይ በትክክል አይቶ መወሰንን የሚጠይቅ እንደሆነ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሌላው በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚታዩ ትርክቶች አሉ ምክንያቱን ለመወሰን የሚያነሳሳቸው ምክንያት እነዚያ ምክንያቶች እያንዳንዳቸው እንደአቀራረባቸው ታይተው የሚሄዱ እንዲሆን፤ በስተመጨረሻም በጥድፊያ የሚደረግ ውሳኔ እንዳይኖርና ሰፊ የሆነ የህዝብ፣ የሊሂቃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር እንደሚያስፈልግ መክረዋል። ሰዎች ቢወዱትም ባይወዱትም የፈለገ ነገር ቢሆን ከራስ ፍላጎት ባሻገር ማየት እንደሚገባቸው ቡድኑ አስገንዝቧል።

አመራሮች ሁልጊዜ ሰውን የሚያስደስት ውሳኔ ላይወስኑ ይችላሉ ያሉት የጥናት ቡድኑ ውሳኔው ግን ሀገራቸውን ከጥፋት ሊታደግላቸው ይችላል ብለዋል። ሰዎች በስሜት ውስጥ ሲሆኑ አንድ ሲደመር አንድ ሁለት መሆኑ ላያግባባቸው እንደሚችል በመናገርም በዚህ ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምንወስነው ውሳኔ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ መክረዋል። በመጨረሻም የአጥኚ ቡድኑ ከእነዚህ ግኝቶች በመነሳት ውሳኔ ለሚሰጡ አካላት ይረዳ ዘንድ ሦስት አማራጮችን የያዘ ምክረ ሐሳብ አስቀምጧል።

አብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊዎች አሁን ክልሉን ባለበት ማስቀጠል አንደኛ አማራጭ አድርገው አስቀምጠዋል። ይህን አማራጭ የመጀመሪያ ሲያደርጉ ግን እነዚህ የገጠሙን ችግሮች ቁጭ ብሎ መፍታት ከተቻለ በሀገር ደረጃ ያለን ተደማጭነት ለማሳደግና ለማስቀጠል ወደ ፊት ቀጣይነት ያለውና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ ለመሥራት በማሰብ ነው።

በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ በማህበራዊና በባህል መስተጋብር ላይ እያደገ የመጣውን የጋራ ስነልቦና በማስቀጠል ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለሚደረገው ሂደት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለው ያምናሉ። ምናልባትም አሁን በሀገራችን እያጋጠመ ያለ የከረረ ብሔርተኝነትን ችግር የቀረፈና ለኢትዮጵያዊ አንድነት ተምሳሌት እንደሆነ በመግለጽ ማስቀጠል እንዳለባቸው የጥናቱ ውጤት አመላክቷል።

ባለበት ማስቀጠል የሚለው የመጀመሪያ አማራጭ ሲመረጥ ግን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በክልሉ የሚነሳው የፍትሐዊነት ጥያቄ በደንብ ተጠንቶ መልስ ማግኘት ካልቻለ ችግር ሊያመጣ እንደሚችልም ተመላክቷል። የፍትሐዊነት ችግሮችን ፈጥቶ ክልሉን ማስቀጠል እንደመጀመሪያ አማራጭ ተይዟል።

ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ክልሉን አሁን ባለው ሁኔታ ማስቀጠል የማይቻል ከሆነ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆነ መልክ ማደራጀት ነው። ቀደም ሲል እንደተገለፀው ከሚጠቀሰው የፍትሀዊነት ችግር አንዱ ክልሉ ሰፊ የቆዳ ስፋት እያለው ሰፊ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እምቅ አቅም በአንድ ማዕከል ላይ ታጥሮ ከተሞችን ማስፋት ያለመቻሉ ነው። በዚህም ክልል እፈልጋለሁ የራሴን ማዕከል አለማለሁ የሚል ጥያቄ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ክልሉ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆነ መንገድ ቢደራጅ አሁን ባለው ሁኔታ ማዕከላትን የማስፋት ዕድል ሊፈጥር ይችላል። በዚህም ከርቀት አንፃር የሚነሱ ችግሮችን መፍታት ይቻላል። በሌላ አገራት እንዳለው ተሞክሮ እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የንግድ ማዕከል፣ የቱሪስት ማዕከል፣ የኢኮኖሚ ማዕከል፣ የፖለቲካ አስተዳደር ማዕከል፣ በማለት መለየት ይቻላል። የደቡብ ክልልም በእንዲህ መልክ ቢደራጅና ሁለተኛው አማራጭ ተግባራዊ ቢሆን አሁን የእየተነሱ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ያስችላል የሚል ሁለተኛ አማራጭ በጥናቱ ቀርቧል።

አማራጭ አንድና አማራጭ ሁለት በህዝብ ውይይት ሳይመረጡ ቢቀሩ በሦስተኛ ደረጃ የተያዘው አማራጭና ጥናቱም የሚያመላክተው የክልል ጥያቄዎችን በጊዜያዊነት ቢሆን ማቆየት የሚል ነው። ይህ የክልልነት ጥያቄ ለጊዜው የሚቆመው ችግሮች ተባብሰው ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው ከክልል አልፈው ሀገራዊ አደጋ የሚያስከትል ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት እልባት መስጠት በማስፈለጉ ነው።

በተለይ አሁን ካለው የለውጥ ሂደት ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ እያጋጠማት ካለው ፈተና በተጨማሪ ሁለቱ አማራጮች ሳይሰሩ ቢቀሩ ሀገራዊ የደህንነት ሥጋት ሊያስከትል ስለሚችል የክልልነት ጥያቄን ሀገር ከተረጋጋች በኋላ እንይ የሚለውን ሦስተኛ አማራጭ አድርጓል።

በጥናቱ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች

በሕገ መንግሥት የተሰጠን መብት ማጥናት አስፈላጊነቱ ምን ያህል ነው? ይህ ሕገ መንግሥት ተመሥርቶ የመጣን ጥያቄ ማጥናት ለምን አስፈለገ? ጥያቄውን ተንተርሶ መመለስ በቂ አይሆንም ነበር? የደቡባዊ ማንነት ተፈጥሯል የሚል የጥናት ግኝት እንዳለ ተመልክቷል። የደቡባዊ ማንነት መገለጫዎች ምንድን ናቸው።

ደቡብ አቅጣጫ አመላካች ሆኖ ሳለ እንዴት ማንነትን ገላጭ ሆኖ በሰዎች ውስጥ ገባ? የናሙና አወሳሰዱ ወካይነት ምን ያህል ታማኝ ነው? ከ17 ሺህ ሰው የተወሰደው መረጃ ከዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የአዋሳ ከተማና የሲዳማ ዞን በጥናቱ ለምን ማካተት አልተቻለም? ይህ ጥናት ለምን መጀመሪያ አልተጠናም? ምሁራን የጥናቱን ውጤት አቅርበዋል። በቀጣይ ጥናቱን ያስጠናው ደኢህዴን ምንድነ የሚያደርገው? ሦስት አማራጮችን አቅርባችኋል፤ ይህ ‹‹የሲዳማ ክልልንም ይመለከታል ወይስ የሲዳሞ ዞን ከእጃችሁ አልወጣም›› ሲሉ ጋዜጠኞች ጠይቀዋል።

የተሰጡ ምላሾች

ከሳይንሳዊ ምርምር ፅንሰ ሐሳብ አኳያ ጥናት የሚጠናው ለችግሮች መፍትሄ መስጠት ሲያስቸግርና በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ ጥናት በማድረግ መልስ ለመስጠት ያሰበ ነው። በመሆኑም የዚህ ጥናት ዓላማ በሀገሪቱ የቀረበውን ጥያቄ ሰፋ አድርጎ ለመመልከት የሚያስችል ጥናት በማድረግ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። የጥናቱ ዋነኛ ዓላማም ስለደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄ በመሆኑ ለዚህ ችግር መልስ የሚሆኑ ሂደቶችን ብቻ የሚፈትሽ ነው።

ደቡባዊነት እንደማንነት የተገለፀበት አግባብ ትክክል ነው ወይ? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ጥናቱ ቡድኑ ሲመልስ 56ቱ ብሔረሰቦች አንድ በመሆናቸው እጅግ በጣም በርካታ ቱሩፋቶች ተገኝተዋል ሲባል አንዱ በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የሚካተተው የደቡባዊነት ሥነ ልቦና ነው። ደቡባዊ ማንነት ከባህል ከማህበራዊ መስተጋብር ከኢኮኖሚ ከፖለቲካዊ ጠቀሜታ ጋር ሊያያዝ ይችላል።

ደቡብ ክልል በሀገር ደረጃ እንደሌሎች ክልሎች ተሰሚነት ማግኘቱና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ አንድ ትልቅ ስኬት ነው። ከአሁን በፊት በሀገር ደረጃ ተሰሚነት ያላቸው የትኞቹ ክልሎች እንደነበሩ የሚታወቅ ነው። ሥነ ልቦና እዚህ ውስጥ እንዳለም ማወቅ ይኖርብናል። የደቡብ ክልል ተወላጅ ከሌሎች ክልል ተወላጆች ጋር ሲገናኝ ደቡብ ነኝ ብሎ የመናገር ሥነ ልቦና ተፈጥሮለታል። ይህ ሲባል 56ቱን ማንነት ጠቅልሎ አንድ ማንነት ውጦታል ማለት አይደለም። አንድ ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸዋል ለማለት ነው።

ወካይነት በቁጥር ብቻ አይገለፅም ጥናቱ የተከተለው ዘዴ ምንድነው? የጥናቱ ዓላማ ምንድ ነው? የሚለው ሊታይ ይገባል። የተሰጠው መረጃ በቂ ነው ወይ እነማን ተሳተፉ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ እንዴት ማዳረስ ተቻለ ምን ያህል ሽፋን ሰጠ? ምን አይነት የጥናት ዘዴዎች ጥቅም ላይ ዋሉ? የሚሉት ሁሉ ሊታዩ ይገባል።

ስለሆነም 17 ሺ መረጃ ሰጪዎች በዚህ ጥናት እንዲሳተፉ ሲደረግ የክልሉን 94 በመቶም መሸፈን ተችሏል። ስለዚህ ውክልና ተገቢ እንደነበር ተገልጧል። ጥናቱ ከሀዋሳና ከሲዳማ ዞን አካባቢዎች ተጠኝዎችን ያላከተተው በተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ቢሆንም ጥናቱ የሚደረገው አጠቃላይ ክልሉን መሰረት አድርጎ በመሆኑና ከመጀመሪያ መረጃ ማግኘት ያልተቻለውን ሁለተኛ የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ጽሑፎችንና ሰነዶችን በመጠቀም የሚፈለገውን መረጃ ማግኘት ተችሏል።

ጥናቱ ቀደም ብሎ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የተነሱት ጥያቄዎች ባልተነሱ ነበር። የአደረጃጀት ጥያቄዎች ከዚህም በፊትም ነበሩ። ነገር ግን አሁን ጉዳዩ ጫፍ ስለነካና በተለያዩ ጊዜያት ይሰጥ የነበረው የፖለቲካ ውሳኔ መፍትሄ ባለማምጣቱ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ ጥያቄዎችን ለመመለስ በመታሰቡ ነው።

የምርምሩ ውጤት ለአስጠኚው አንድ ግብዓት ሆኖ ለውሳኔ ይጠቅመዋል። ደኢህዴን ይህን የምርምር ውጤት ለህዝብ አቅርቦ እንደሚያወያይ ይጠበቃል። ጥቅምና ጉዳቱን በመመልከትም አንድ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ይጠቀምበታል። ምንም እንኳን የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ቀደም ያለ ቢሆንም አሁንም ለብቻው ያለና ከእጅ የወጣ ጉዳይ አይደለም። ይህ ጥናት ሲዳማን ጨምሮ በደቡብ ክልል ያሉትን በሙሉ የሚመለከት ይሆናል። ሁሉንም በክልሉ የሚገኙ ዞኖች በአንድ ማዕቀፍ አድርጎ የተጠና ጥናት ነው።

በአጠቃላይ ደኢህዴን ያስጠናው ጥናት ሦስት አማራጮችን ያመጣ ቢሆንም በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብክፍሎች ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም ሲሉ ተቃውሟቸውን እየገለፁ ነው። ይህ ቢሆንም የጥናቱን ትክክለኛነት በሚመለከት ነፃ የሆኑሌሎች ምሁራን እንዲተቹት ማድረግና ሐሳባቸውን ለህዝብ ማቅረብ ይገባል።

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 25/2011 –  ኢያሱ መሰለ

ፎቶ ሪፖርተር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *