የዳያስፖራ ባንኩን የመመሥረት ሐሳብ ያመነጩትና እያደረጁ የሚገኙት በአሁኑ ወቅትም በምሥረታ ላይ የሚገኘው የ‹‹ኢትዮጵያ ዳያስፖራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር›› ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው የትአለ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ባንኩ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል አቅም እንዲኖር ታልሞ፣ በ150 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል እንዲመሠረት ለማስቻል እንቅስቃሴ እየተደረገበት ይገኛል፡፡

ባንኩን መመሥረት ስላስፈለገበት ምክንያት ሲያብራሩም፣ በኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ የሚያስችሏትን የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች በመደገፍ ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን ሀብት ለማመንጨት እንዲቻል በማሰብ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ አንዱ መንገድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚመሠርቱትና ኢንቨስት የሚያደርጉበት ባንክ መመሥረት ጊዜው የሚጠይቀው ሆኖ እንዳገኙት የሚገልጹት አቶ ጋሻው፣ ከሦስት ሚሊዮን ያላነሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ እንደሚኖሩ በማጣቃስ ይህ ኃይል ለኢትዮጵያ ማበርከት የሚችለውን ወሳኝ አስተዋጽኦ በመገንዘብ የዳያስፖራ ባንክ ለማደራጀት መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ እንዲመሠረት የታሰበው ከፍተኛ የገቢ ምንጭና መተዳደሪያ ባላቸው በውጭ ባለአክሲዮኖች እንደሆነ ገልጸው፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከሚያስፈልገው ካፒታል በላይ በማሰባሰብ ቢያንስ በ150 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል ሊመሠረት እንደሚችል አቶ ጋሻው ይናገራሉ፡፡

ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ ባንኩን ለማደራጀት እንቅስቃሴ ሲካሄድ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ነባሩን የባንክ ሥራ አዋጅን የሚያሻሽል ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱና፣ በዚሁ ሕግም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አሊያም በአገር ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች ጋር ባንክ ማቋቋም እንደሚችሉ የሚፈቅዱ የማሻሻያ አንቀጾችን ያካተተበትን ሕግ ለማውጣት ጫፍ መድረሱ የባንኩን የምሥረታ ሒደት እንደሚያፋጥነው አቶ ጋሻው ይጠቅሳሉ፡፡

ባንኩ የአንድ ቢሊዮን ዶላር አቅም የመፍጠር ራዕይ ከመሰነቁም ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ባንክ ነክ ባልሆኑ ሥራዎች ውስጥም ለመሳተፍ የሚችልባቸው ዕቅዶች እንደተዘጋጁለት አቶ ጋሻው ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም የባንክ ባለሙያዎችን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ የሚያሠለጥን የባንክ ልቀት ማዕከል የሚሆን ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ፣ አዋጭ በሆኑ የመካከኛና ረዥም ጊዜ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ በተለይም በሪል ስቴትና መሰል ዘርፎች ተሳትፎ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

መንግሥት የባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የውጭ ባንኮች እንዳይገቡ ዝግ ማድረጉ ዘርፉ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳያድግ ከማድረጉም ባሻገር፣ አገሪቱ ለምትተገብራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተገቢውን የገንዘብ አቅርቦት በአገር ውስጥ የማመንጨት ዕድሏንም እንደጎዳው በመግለጽ፣ ወደ ፊት የዓለም ባንክ አባል ለመሆን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲህ ያሉ ክልከላዎች መነሳታቸው አይቀሬ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚመጣ በማመን ከወዲሁ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚመሠረት ባንክ ማቋቋሙ ትኩረት ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለትልውደ ኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ለውጭ ባንኮችም ክፍት ማድረግ እንዳለበት የሚያሳስቡት አቶ ጋሻው፣ የውጭ ምንዛሪ ተመኑንም ለገበያው መተው እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

ምንም እንኳ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ቢመጡም፣ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ለገበያው ክፍት ማድረጉ ጥቁር ገበያውን ሊያከስመው እንደሚችልና በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የውጭ ምንዛሪም በመደበኛው መንገድ እንዲዘዋወር ለማድረግ እንደሚያግዝ የመታመኑን ያህል፣ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር በማይጣጣምበት ወቅት በተለይም ለዘመናት የቆየው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ባልተቀረፈበት ወቅት የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረጉ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በማድረግና የምንዛሪ ተመኑን ዋጋም ወደ ላይ በመስቀል ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ሥጋታቸውን የሚገልጹ ባለሙያዎች አሉ፡፡ አቶ ጋሻው ግን የምንዛሪ እጥረቱን ሊፈቱ የሚችሉ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩና ወደ ውጭ ምርቶችን የሚልኩ ፕሮጀክቶች ከተስፋፉ የምንዛሪ ተመን ችግር እንደሚቀረፍ ይገልጻሉ፡፡

ይህም ሆኖ መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሚጠቅሱት የዳያስፖራ ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት የሕግ ሰውነት እንዲያገኝ ስያሜውን በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማስመዝገብና ዕውቅና ከማግኘት ጀምሮ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንኩን ለማደራጀት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ጋሻው አስታውቀዋል፡፡ 

ብርሃኑ ፈቃደ ሪፖርተር  

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *