ከሳምንት በፊት ከፍተኛ  የኤርትራ ጀነራል ስለ ኤርትራ ጦር ጥንካሬና አቅም ሲናገሩ ዛቻ ቢጤም ሰንዝረው ነበር። ከወራት በፊት ደግሞ በሱዳን እንደተደረገው ዓይነት መፈንቅለ መንግስት ህወሃት እያቀነባበረ መሆኑም በአንዳንድ ሚዲያዎች ይፋ መደረጉ ይታወቃል። የህወሃት አፍቃሪዎች ኤርትራ ዘልቀው መንግስት የመጣል አቅም እንዳላቸው በይፋ ሲናገሩ መስማት ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ የይፋ መፈክር ነው።

በመከላከያና በድህንነት ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ያደረግችው ኤርትራ ዛሬ ያሳየችው ወታደራዊ አቅሟ ከላይ ከተባለው ጋር ስለመገናኘቱ ባለስልጣኖች በይፋ ባይናገሩም ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ለማስወገድ በህወሃት በኩል ለሚሸረበው ሴራ ፍቱን መደሃኒት እንዳላቸው ለማሳየት እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ቢቢሲ የሚከተለውን ዘግቧል

ባለፈው ሳምንት የኤርትራ መንግሥት ብሔራዊ አገልግሎት የተጀመረበትን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሮታል።

ዕለቱን አስመልክቶ የሃገሪቱን ርዕሰ ብሔር ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመገናኛ ብዙኃን ብቅ ብለው ንግግር አድርገዋል። ክብረ በዓሉ ከሙዚቃ፣ ድራማና ሌሎች የአደባባይ ትርዒቶች ባሻገር ወታደራዊ ትዕይንቶችም የቀረቡበት ነበር።

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ኤርትራ የብሔራዊ አገልግሎት ከጀመረችበት አንስቶ ባለፉት 25 ዓመታት የተገኘውን ተሞክሮ በመገምገም ብሄራዊ አገልግሎቱ ለአገር እድገትና ብልጽግና ያደረገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኤርትራ ብሔራዊ አዋጅ አገልግሎት ከጤና እክል፤ የቀድሞ ታጋዮች፣ ያገቡና ከወለዱ ሴቶች ውጭ ሁሉም ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ የሆነ ኤርትራዊ ለ18 ወራት ብሔራዊ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል።

ነገር ግን አዋጁ እንደሚያዘው ሳይሆን ብዙ ኤርትራውያን ለአስርት ዓመታትም በውትድርና አገልግሎት ተሰማርተው ቆይተዋል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተሰጠው ኤርትራ ከኢትዮጰያ ጋር ጦርነት ላይ በመሆኗ ነው የሚል ነው።

በሁለቱ ሃገራትም መካከል ሰላም ቢሰፍንም የብሔራዊ አገልግሎቱ እጣ ፈንታ ግን እስካሁን አልለየም። የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ኢትዮጵያ ከኤርትራ መሬት ስላልወጣች ወታደሮቹ አሁንም ባሉበት እንደሚቀጥሉ ተናግሯል።

ሁለቱ ሃገራት የሰላም ስምምነቶችን ሲፈርሙ ኤርትራ የኔ ናቸው የምትላቸው መሬቶች ጉዳይ ለምን ውል አልያዘም ብለው የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም።

በዚሀም ክብረ በዓል ላይ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንትም ሆነ ሌሎቹ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ብሔራዊ አገልግሎቱ አዋጁ ባስቀመጠው መሰረት (ለአስራ ስምንት ወራት) ለማከናወን እቅድ ስለመያዙ የተናገሩት የለም፤ በሁለቱ ሃገራትም መካከል ስለተደረሱ ስምምነቶችም ምንም ጉዳይ አልተነሳም።

ከፍተኛ ወታደራዊ ትእይንት ለምን?

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲከበር የሰነበተው ይሄው ክብረ በዓል ባለፈው ሐሙስ በባህላዊ ስፖርትና በከፍተኛ የጦር መሳርያ በታጀበ ወታደራዊ ሰልፍ በሳዋ ተጠናቋል።

በዚህም ወታደራዊ ትእይንት ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታንኮች፣ የጦር ሄሊኮፕተሮችና ተዋጊ አውሮፕላኖች እንዲሁም መሳሪያ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ መኪኖች ተሳትፈዋል።

ከፍተኛ ወታደራዊ ትዕይንት በነበረበት በዚህ ስፍራ ላይም ወታደሮች ከጦር ሄሊኮፕተሮች ላይ በፓራሹት ሲወርዱ እንዲሁም ተዋጊ አውሮፕላኖቹ በሰማይ ላይ ሲያንዣብቡ ታይተዋል።

ይህ ወታደራዊ ትእይንት ለዓመታት ኤርትራ የገነባችው የብሔራዊ አገልግሎት ውጤት ማሳያ መሆኑንም መድረኩን ይመሩ የነበሩት ግለሰቦች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ነበር።

ይህ ትእይንት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ባልነበረችበት ወቅት ብዙ አስገራሚ ባይሆንም በሁለቱ ሃገራት መካከል ሰላም መስፈን ተከትሎ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር ትዕይንት ማሳየቷ የአፍሪካ ቀንድን የፖለቲካ ሂደት ለሚከታተሉ ጥያቄን አጭሯል።

ወታደራዊ ትይንቱ እንግዳ ከሆነባቸው መካከል የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኙና የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ዶክተር አሌክስ ድቫል ዋነኛው ናቸው።

በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ግጭቶች፣ የሰላምና ግንባታ እንዲሁም የከሸፉ አገራትን በተመለከተ በርካታ ጥናታዊ ስራዎችና ፅሁፎች ያቀረቡት አሌክስ ድቫል “የታየው ሰልፍና ወታደራዊ ትርዒት በተለይ ሰላም በሰፈነበትና ሀገራቱ ተረጋግተው ባለበት ሁኔታ የተካሄደ በመሆኑ እንግዳ ነገር (odd) ሊባል የሚችል ነው።” ይላሉ።

ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቅሱት ከኢትዮጵያ ጋር የተጀመረው የሰላም ሂደት በአሁኑም ወቅት ቀጣይ በመሆኑ እንዲሁም ለዓመታት ከሱዳን ጋር ተፋጣ የነበረችው ኤርትራ ሰላም መፍጠሯ እንዲሁም ለሶስት አስርት አመታት በስልጣን ላይ የነበሩት ኦማር አልበሽር መውደቅን ተከትሎ በሱዳን የሲቪል አስተዳደር እየተመሰረተ መሆኑ ኤርትራ ከአካባቢው አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በአዲስ መልኩ እንደሚታይ ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ከጎረቤቶቿ ጋር ብቻ ሳይሆን ኤርትራ ከመካከለኛ ምስራቅ አገሮች በተለይ ደግሞ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከኢሚሬትስ ጋር ያላት ግንኙነት በተሻሻለበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ወታደራዊ ትርኢት ማሳየት አስፈላጊ አልነበረም የሚል አቋም አላቸው።

ዶክተር አሌክስ አሁን ኤርትራ እያደረገችው ያለውን “አትኩሮት ፍለጋ” ባለፉት ከነበረው አስርት አመታት የሃገሪቴ ስትራቴጂ (አካሄድ) አንፃር መታየት እንዳለበት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

“ባለፉት 20 ዓመታት የፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ስትራተጂ (አካሄድ) በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲያገኙ መስራት ነበር። ይህ አኳኋን ደግሞ የሚረብሽና ሰላምን የሚያደፈርስ አካሄድ ነበር። “ይላሉ

በዚህ ጥቂት አመታት ግን በአካባቢው የነበረው ግጭት መቀነስ፤ እንዲሁም የአረብ ኤምሬትስ በአከባቢው ያላቸው ተጽዕኖ እየቀነሰ መምጣትን የአሰብን አስፈላጊነት እየቀነሰ ስለሚመጣ ይህ ደግሞ የኤርትራን ወይም የመሪዋን “እዩኝ” ማለት ተፅእኖ ሊፈጥርበት ይችላል ይላሉ።

አሰብ በየመን ሲካሄድ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት መናሃርያ ነበረች። ምሁሩ አክለውም “ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከወዳጆቹ ጋር ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋወሪ ኤርትራን ከሚፈልጓት ሃገራት ከሳውዲዓረብያ ኣጋሮች (ማለትም ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ቻይና) ተፈላጊነትም ዝቅ ሊል ይችላል” ይላሉ።

በአጠቃላይ ወታደራዊ ትዕይንቴ ፕሬዚዳንቱ እንዳይዘነጉ ወይም ኤርትራ ያላትን ስፍራ ቀልብ የመሳብ ጉዳይ ነው በማለት ያስቀምጡታል።

ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተለያዩ የሰላም ስምምነቶችን ቢፈራረሙም አሁንም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ ከህወሐት ጋር ያላቸው መካረር መፍትሄ እንዳላገኘ ዶክተር አሌክስ ይናገራሉ።

“ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ሰላም ሲፈጥሩ ኤርትራን በፅኑ ወጥረዋት የነበሩትን የህወሐት መሪዎች ቅርቃር ውስጥ የሚያስገቡ (የሚጨፈልቁ) መስሏቸው ነበር። በእርግጥ ለውጡን ተከትሎ ህወሐት በማዕከላዊ መንግሥት የነበረው ሚና ተዳክሟል። ሆኖም እንደታሰበው አይደለም። የትግራይ ህዝብ ደግሞ ከወንድሙ የኤርትራ ህዝብ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት በጸጋ ነው የተቀበለው።” በማለት የተጠበቀውና የሆነውን ሁኔታ ይገልፁታል።

ምሁሩ ጨምረውም ከህወሐት ጋር ያለው ሁኔታ ሰላምም ጦርነትም ባለመሆኑ ፕሬዚዳንቱ ኃያልነታቸውን ማሳየት መፈለጋቸው የትዕይንቱ ዋነኛ ትኩረት ይላሉ።

“ሰላም ለፕሬዚደንት ኢሳይያስ ስልጣን ከጦርነት በላይ ከባድ ፈተና ነው። ህዝቡ በጦርነት ተሸብሮ ከሚኖር ሰላም ሲያገኝ ነው ዓይኑን የሚገልጠው። በዚህ ምክንያት ነው ፕሬዚደንት ኢሳይያስ ‘አሁንም ኃይሌ እንዳለ ነው’ የሚል መልእክት ለማስተላለፍ የሞከሩት የሚመስለኝ” ብለዋል።

መቀመጫውን ኬንያ ያደረገውና ዘ አፍሪካኒስት ኢንፎ የተሰኘ ድረ ገፅ ያለው ሆላንዳዊው ጋዜጠኛ ከርት ሊንዲየር በበኩሉ ባለፈው ዓመት የተገኘው ሰላም ከብዙ ውጣውረድ በኋላ የመጣ መሆኑን በማስታወስ “በእንደዚህ ሁኔታ ሰላምን የሚያደናቅፍ ትርኢት ማካሄድ አስፈላጊ አልነበረም። እኔ እንደሚመስለኝ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የስልጣን ሽምያ ወዴት እንደሚያዘነብል የሚጠባበቁ ይመስለኛል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሳዋ የታለመለትን ግብ ከመምታቴ አንፃር ከዚህ በኋላ ሊቆም ይገባል የምትለው ደግሞ በኤርትራ ላይ በሚያጠነጥነው መፅሀፏ”I Didn’t Do It For You: How the World Used and Abused a small African Nation” በሚል የምትታወቀው ሚከላ ሮንግ ናት።

“በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የሰላም አየር እየነፈሰ ስለሆነ ኤርትራ በተጠንቀቅ መኖር የለባትም። የኤርትራ ወጣቶች ማብቅያ በሌለው የወታደራዊ አገልግሎት ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው በመሰደድ ላይ እንደሆኑ ዓለም እየታዘበ ነው” ትላለች።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላምን መፍጠሯ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን የሚናገሩት ተንታኟ ለኤርትራ ህዝብም አዲስ አይነት አስተዳደር ማምጣት ነበረባቸው ይላሉ።

“የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ከተጨባበጡ ጀምሮ ኤርትራውያን ልጆቻቸው ከወታደራዊ አገልግሎት ነጻ የሚወጡበት ፖሊሲ እንዲተገበር በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ” የምትለው ሚከላ ሮንግ

“ባለፈው ሳምንት በሳዋ የተመለከትነው በከባድ የጦር መሳርያዎች የታጀበ ትዕይንት ግን ‘የተለወጠ ነገር የለም ሁሉም እንደነበረበት ይቀጥላል’ የሚል አንድምታ አለው” ትላለች። አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንተኝ ዳን ኮኔልም የሚከላን ሀሳብ ይጋራል።

“ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮ ኤርትራ ዕርቀ ሰላም ከተፈረመበት ከአንድ አመት በኋላ ህዝቡን አሰባስቦ ወደ ሌላ የፖለቲካ ምዕራፍ ሊያሻግራቸው በተገባ ነበር” ይላል።

ነገር ግን የፕሬዚዳንቱ ፖለቲካ ወደየትም ፈቅ እንዳላለ ማሳያው ደግሞ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ወታደራዊ ትእይንት በቅርቡ ማሳየቷ ነው።

“በድሮ ፖለቲካው ተቸክለው የቀሩ ይመስለኛል” በማለት “በከባድ መሳርያ የታገዘ የጦር ትዕይንት የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ሊያስጨንቅ ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባ ነበር” ሲል አስተያየቱን ያጠናክራል።

“የጦር ትዕይንቱ የኤርትራ ወጣቶች ምን ያክል አቅም እንዳለቸው ያሳየ ቢሆንም የከባድ መሳርያ ትዕይንቱ ግን ይረብሻል” በማለትም ሀሳቡን ያጠናቅቃል።

ሌላኛው የሰላም እና ግጭት ጥናት ምሁር ፕሮፌሰር ጀትል ትሮንቮል በበኩላቸው ወታደራዊ አገልግሎት የሀገር አንድነት በመገንባት ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው ቢሆንም ዓለማውን እንዳይስት በተጣያቂነት አሰራር ሊተገበር እንደሚገባ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

“የተካሄዱት ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ኤርትራውያን ከሀገራቸው የሚሰደዱበት ዋነኛው ምክንያት መጨረሻ የሌለው ብሔራዊ አገልግሎት ነው። ብሔራዊ አገልግሎቱ ወጣቶቹ መጪ ህይወታቸውን ስለሚያጨልምባቸው ሀገራቸው ከመገንባት ይልቅ ወደ ውጪ ሀገራት በመሰደድ ላይ ናቸው” ይላሉ።

በአጠቃላይ ይላሉ ምሁሩ የሰሞኑ የጦር መሳርያዎች ትዕይንት ኃይልን ለማሳየትና ፕሬዚደንት ኢሳይያስ “ከእነ አቅሜ ነኝ ለማለት የፈለጉ ይመስለኛል” ይላሉ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *