ከ15 ዓመት በታች ታዳጊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በኤርትራ የሚደረገው የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ቀጣና ሻምፕዮና (ሴካፋ) ውድድር ሊሳተፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ ከ20 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኤርትራ የሚጫወት የኢትዮጵያ ቡድን እንደሚሆን ኢብኮ ዘግቧል፡፡ በምድብ ሁለት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በቅድሚያ ከኡጋንዳ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ነገ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፕሬስ ኃላፊ ባሕሩ ጥላሁን “ይህ ለእኛ የተጠፋፋ ቤተሰብ እንደመገናኘት የሚቆጠር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ኤርትራ ውስጥ በተዘጋጀው ውድድር ተደስተናል፤ ከ20 ዓመታት በላይ ተለያይተናል። ይህም ኤርትራ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ዘላቂ ወዳጅነት የምንመሠርትበት መልካም አጋጣሚ ይሆናልም” ብለዋል።

በውድድሩ ላይ አስተናጋጇ ኤርትራ በምድብ አንድ ከሚገኙት ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ጋር ትጫወታለች። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከየምድባቸው ማለፍ ከቻሉ አብረው የመጫወት ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችልም ቢቢሲን ጠቅሶ ኢብኮ ዘግቧል፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2011 ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *