እያንዳንዷ የምግብ ገበታ የእርስዎን በሕይወት መኖርና አለመኖር የምትወስን ብትሆንስ? የሚቀርብልዎ ቁርስ፣ ምሳ ወይም እራት፤ የሞትዎ ዕጣ የሚመዘዝበት እድልን የሚፈጥር ነገር ግን እምቢ ማለት ደግሞ የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ የሚኖርን ሰው አስቡት። ይህ ልብ ወለድ አይደለም። የሂትለር ወጥ ቀማሾች የየቀን እውነታ እንጂ።

የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የመጨረሻዎቹ 30 ወራት አካባቢ ሂትለር እያንዳንዷ ወደ አፉ የምትገባ ነገር በሌላ ሰው መቀመስ ነበረባት።

• ለልጃቸው “ሂትለር” የሚል ስም የሰጡ እናትና አባት ተፈረደባቸው

የጀርመን ጠላቶች ወይም የእርሱ ምቀኞች እንደው በምግብ መርዘው ፍፃሜውን እንዳይቀርቡበት የሰጋው ሂትለር፤ ጀርመናዊ ጉብሎች አስመልምሎ ሲያበቃ ‘ወጥ ቀማሽ’ አደረጋቸው።

የእኒህ ሴቶች አስገራሚ ታሪክ ለጆሮ የበቃው የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ነው፤ ታሪኩን ለሰሚ ያደረሰችው ደግሞ የ95 ዓመቷ የያኔዋ የሂትለር ወጥ ቀማሽ የነበረችው ማርጎ ዎክ ናት።

የማርጎ ዎክ ታሪክ ‘የሂትለር ወጥ ቀማሾች’ በሚል ርዕስ ተከሽኖ ትያትር ሊሆን በቅቷል።

ሁሉም ተዋንያን ሴቶች ናቸው። ጭብጡ የሚያጠነጥነው ደግሞ አራት የሂትለር ወጥ ቀማሽ የነበሩ ወጣት ሴቶች ላይ ነው።

ማርጎ መጀመሪያ ታሪኳን ያጫወተችው ሚሼል ብሩክስ ለተሰኘች ጋዜጠኛ ነበር። «መቼም ይህን ታሪክ ትፅፊዋለሽ?» የብሩክስ ጥያቄ። «እኔ አልፅፈውም የምትይ ከሆነ፤ እመኚኝ እኔ መፃፌ አይቀርም።»

• የሂትለር ሥዕሎች ለምን አልተሸጡም?

ብሩክስ ታሪኩ እጅግ አሳዛኝና ጨለም ያለ መሆኑን ብታውቅም ‘ትራጃይኮሜዲ’ አድርጋ ለመሥራት ነበር የወሰነችው። እኒህ ወጥ ቀማሽ ሴቶች በዚያ ጨለማ ወቅት እንዴት ጓደኛሞች ሆነው መዝለቅ እንደቻሉ እንዲያትት አድርጋ ነው ትያትሩን የፃፈችው።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመናዊያን በከባድ ችጋር ተመተው በርካቶች በረሃብ አለንጋ የተገረፉበት ዘመን ነበር። ነገር ግን እኒህ ሴቶች በቀን ሦስት ጊዜ ለሂትለር ተብሎ የበሰለ በቅመም ያበደ ምግብ ያገኙ ነበር።

ወቅቱን የምትዘክረው ማርጎ፤ ሂትለር ሥጋ መመገብ ብዙም የማይወድ ሰው ነበረ ትላለች። አትክልት፣ ሩዝ፣ ፓስታ እና ፍራፍሬ የሰውዬው ምርጫዎች ነበሩ። እኒህን ምግቦች በዚያን ጊዜ ማግኘት ቀርቶ ማሰቢያ የሚሆን አቅም የሚሰጥ ምግብ ማግኘት የከበደበት ዘመን ነበር።

አዶልፍ ሂትለርና ሙሶሊኒ 'የዎልፍ ሌር' በተሰኘው የሂትለር መሸሸጊያ ስለጦርነቱ ሲመክሩImage copyrightGETTY IMAGESአጭር የምስል መግለጫአዶልፍ ሂትለርና ሙሶሊኒ ‘የዎልፍ ሌር’ በተሰኘው የሂትለር መሸሸጊያ ስለጦርነቱ ሲመክሩ

«ምንም እንኳ የሚቀርቡት የምግብ ዓይነቶች በዓይን የሚበሉ ቢሆኑም እኛ ግን በሰቀቀን ነበር የምንመገባቸው።»

«በርካታ ሴቶች ምግቦቹን የሚመገቡት እያለቀሱ ነው። በጣም ይፈሩ ነበር። የቀረበለንን ጥርግ አድርገን መብላት አለበን። ከዚያ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያክል መጠበቅ አለብን። ብዙዎቻችን ከአሁን አሁን ታመምን እያልን እናለቅስ እንደነበር አስታውሳለሁ» ስትል ወቅቱን ታስታውሳለች።

የሂትለር የወጥ ቤት ሰዎች ሴቶቹ ከተመገቡ አንድ ሰዓት በኋላ ነው ምግቡን በዓይነት በዓይነቱ ለአዛዣቸው ያቀርቡ የነበረው። በሴቶቹ ቅምሻና በሂትለር የምግብ ሰዓት መካከል ያለችው 60 ደቂቃ ምጥ ነበረች። ቁጭ ብሎ ሞትን የሚጠባበቁባት

ከምግብ ቀማሾቹ መካከል ተመርዛ የሞተች ሴት ያለች እንደሁ የሚታወቅ ነገር የለም፤ ማርጎ ዎክ «እኔ በነበርኩበት ወቅት ማንም ተመርዞ የሞተ የለም» ትላለች። የዛሬ ስድስት ዓመት ማርጎ ዎክ ታሪኳን እስከተናገረችበት ወቅት ድረስ ግን ስለ ወጥ ቀማሾቹ ሴቶች የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

የሩሲያ ወታደሮች ወደ አዶልፍ ሂትለር ቤተ መንግሥት መቅረብ ሲጀምሩ አንድ ባለማዕረግ ወታደር ማርጎን አሾልኮ ያስወጣትና ወደ በርሊን የሚሄድ ባቡር ላይ ያሳፍራታል። ሌሎች ሴቶች ግን እምጥ ይግቡ ስምጥ ማርጎ የምታውቀው ነገር የለም። ምናልባትም የሩሲያ ወታደሮች በፈጸሙት ጥቃት ተገድለው ይሆናል ስትል ትገምታለች።

• አዶልፍ ሂትለርን በሳምሶናይት ቦምብ ያቆሰለው መኮንን

ሰው ለመኖር ይመገባል። ማርጎ እና ወጥ ቀማሽ ጓደኞቿ ግን ይመገቡ የነበረው ለመሞት ነበር፤ ሞትን ከሂትለር ቀድሞ ለመቅመስ። እንዴት ይህን የመሰለ ታሪክ ‘አስቂኝ ትያትር’ ይሆናል? «እኔም ገርሞኛል» ትላለች ማርጎ።

«ሰዎች ወደ እኔ መጥተው እንዴት አድርገን ነው ይህን ትያትር የምናየው? እንዴትስ ጥርሳችን ይስቅልናል? ሲሉ ይጠይቁኛል። ነገር ግን ትያትሩን ብታዩት ይገባችኋል። እኛ እኮ ከሂትለር ጋር ምንም ግንኙነት የለንም። እንደውም እንደተቀረው ሰው በጣም እንጠላው ነበር [ሳቅ]።»

Credit – BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *