የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ለ1ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በመደበኛና በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታወቀ።

የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ 1ሚሊዮን 813ሺ93 ለሚሆኑ ዜጎች በመደበኛና በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች 87በመቶ ሥራ ማስያዝ ተችሏል ።

የሥራ ፈጠራው ሁለት ዓይነት መሆኑን የሚጠቁሙት ወይዘሮ አቦዘነች፣ በመደበኛ አምስት የሥራ ዘርፎች ጥቃቅንና ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ከተማ ግብርና አገልግሎትና ንግድ ላይ 882ሺ98 ፤ በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ 712ሺ389 የሥራ ዕድል መፈጠሩን አብራርተዋል። ከተቀጣሪዎቹ ውስጥ 47ሺ387 የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወደ 3ሺ407 አካል ጉዳተኞችና 82 ከስደት ተመላሾች መሆናቸውን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪዋ አስረድተዋል ።

መንግሥት በበጀት ዓመቱ ለ3ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ላቀደው ሥራ የኤጀንሲው ድርሻ ከፍተኛ እንደሚሆን የተናገሩት ወይዘሮ አቦዘነች፣ የከተሞች ድርሻ 1ነጥብ 5 ሚሊየን እንደሆነ አስታውቀዋል ።

‹‹በመምራት፣ በማስተባበር በመደገፍ ሥልጠና በመስጠት ዐቅም በማጎልበትና በማብቃት ኃላፊነት አለብን›› ያሉት ወይዘሮ አቦዘነች ፣በዚህ ላይም ኤጀንሲውም ሆነ በክልል የሚገኙ የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት በጣም ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

እንደ ወይዘሮ አቦዘነች ማብራሪያ፤ኤጀንሲው ዜጎች በየምዝገባ ጣቢያዎች ወይም ቤት ለቤት እንዲመዘገቡ በማድረግ ሥልጠና እንዲያገኙ በማስተባበር ብድር እንዲያገኙና የመሥሪያ የመሸጫ ቦታዎች እንዲሚመቻች የማስተባበር ሥራውን የመምራት የመከታተል አፈፃፀሙን የመገምገም ነገሮች በዋነኛነት ከሌሎች ተቋማት ከወጣቶች ከሴቶች ጋር በመተባበር ይሰራል፡፡

‹‹በኤጀንሲው ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ይመጣሉ ፤ይመዘገባሉ፤ የማስተባበር ሥራ እንሠራለን ፤የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በየክልሉ ያሉ ኤጀንሲዎች የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲዎች የቴክኒክም የኢንተርፕረነርሺፕም ስልጠና ይሰጣሉ›› ሲሉ አብራርተዋል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 14/2011

ኃይለማርያም ወንድሙ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *