በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ተበጀ በርሄ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ከኳታር ልማት ፈንድ የፕሮጀክት ኃላፊዎች ጋር በሀገራችን የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ለማቋቋም ዝርዝር ውይይት አድርጓል።

በልዑክ ቡድኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ልዩ የፕሮጀክት አማካሪ ዶክተር ሰናይት በየነ እና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የኩላሊት ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር አዲሱ መልኬ ተካተዋል።

እንዲሁም በኳታር የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ እና የኤምባሲው ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል።

በኳታር በኩል የኳታር ልማት ፈንድ የልማት ፕሮጀክቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሚስፈር ሃማድ አል ሻህዋኒ እና ሌሎች የተቋሙ ፕሮጀክት ባለሙያዎች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በውይይታቸውም ከአሁን ቀደም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች ስምምነት መሰረት የኳታር መንግስት በአዲስ አበባ የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ለመገንባት የገባውን ቃል በአፋጣኝ ወደ ተግባር ለማሸጋገር በሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በዚህ መሰረትም ፕሮጀክቱን በፍጥነት ሥራ ለማስጀመር ስምምነት ላይ መደረሱ ነው የተገለጸው።

የሆስፒታል ግንባታ ሂደቱ ሁለት ምዕራፎች የሚኖሩት ሲሆን፥ የመጀመሪያው ምዕራፍ የህንፃ ግንባታውንና የባለሙያዎች ስልጠናን የሚያካትት ይሆናል።

እነዚህን ሥራዎች ተፈጻሚ ለማድረግም የኳታር ልማት ፈንድ 18 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የመደበ መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የልዑክ ቡድኑ ከኳታር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በዘርፉ ትብብር ለማድረግ እንዲቻል የጎንዮሽ ውይይቶችን ማካሄዱን በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም በእድሳት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የጎበኘ ሲሆን፥ በኤምባሲ በሚገኘው የኮሚዩኒቲ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችንም አነጋግሯል።

ኤፍቢሲ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *