በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር በመሆኑ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮም ዝግጅት ይደረግበታል፡፡ ዘንድሮም ልጃገረዶች እንደ አደይ አበባ ደምቀውና አምረው በአንድ ላይ በመሰብሰብ ቆርጠው ያመጡትን የአሸንዳ ተክል ከሚታጠቁት ገመድ ላይ በስርዓት አቀጣጥለው በጉንጉን መልክ አስረው በወገባቸው ታጥቀዋል፡፡ በባህላዊ ልብሶች አጊጠው፤ ፀጉራቸውን በተለያዩ የአሰራር አይነቶች ተውበው ላያቸው የክረምቱን ማብቃትና የመስከረምን ጸደይ እንድናይ የሚያብሱሩንን አበቦች ይመስላሉ፡፡

በዓሉ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ ክልል በሰቆጣ፣ በዋግህምራ፣ በላስታ ላሊበላ በመሳሰሉት አካባቢዎች፤ በትግራይ ክልል ዓብይ ዓዲ (ተንቤን)፣ በመቐለና በሌሎች አካባቢዎችም አሸብርቆ ውሏል፡ ፡ ልጃገረዶችም በአካባቢያቸው ያሉትን መንደሮች እየዞሩ የታጠቁትን የአሸንዳ ተክል ወደ ግራ ወደ ቀኝ እያወዛወዙ የተለያዩ ዜማዎችን እያዜሙ ባህሉን አድምቀውታል፡፡

በዓሉ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአህጉሩ ትልቅ ሀብት መሆኑን የተናገሩት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡ ይህንን ያሉት ደግሞ ትናንት በዓሉን ለማክበር በመቐለ ከተማ  በተገኙበት ወቅት ነው፡፡ በልጃገረዶች ደማቅ ትርዒት ታጅቦ በርካታ ዘመናትን ያሳለፈው የአሸንዳ በዓል በቀጣይ እንደ መስቀል፣ ፊቼ ጨምበላላና የገዳ ሥርዓት ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ ቅርስ እንደሚሆን ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡ ባህሉ ተጠብቆ እንዲቆይ የትግራይ ህዝብ ለተጫወተው ግንባር ቀደም ሚናም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

“የቅርሶች ዓለም አቀፋዊ መሆን ማለት ብሔራዊ መሆን ማለት ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ አንዳንድ ቅርሶች ከአንድ አገር በላይ ባለቤት እንደሚኖራቸውና ባህል በፖለቲካ ድንበር ሊታገድ እንደማይችል አስታውቀዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚባለውና በአደባባይና በጎዳና ትርዒት የሚከበሩት የማይዳሰሱ ቅርሶች ከመሠረታዊ ትውፊታቸው ጀምረው አሁን እስካሉበት ሁኔታ ድረስ በአንክሮ ተስተውለዋል፡፡ ዓላማቸውም ሠላምን፣ አንድነትን፣ መደጋገፍንና መከባበርን በመስበክ በዓለም ላይ መሠረት ያላቸው ህዝቦች ሆነን እንድንታይ የሚረዱን የኩራታችን ምንጮች ናቸው፡፡

ለአሸንዳ ሴት የሚሰጠው ክብር ለሁሉም የኢትዮጵያ ሴቶች በ365ቱ ቀናት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ውብ የሆኑ እሴቶቻችን የመነሻ ቀለምና ለዛቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር ውስጣዊ አንድነታችንን ከማጠናከር ባለፈ ለአገራችን  ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸውን እምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ከባለቤቶቹ ባለፈ ሌላውም ዓለም እንዲያውቃቸው ለማድረግ ሠፊ ሥራ ያስፈልጋል” ብለዋል ፕሬዚዳንቷ የባህሉን ተጨማሪ ትሩፋት ሲያብራሩ፤ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፤ “የአሸንዳ ልጆች በዓላችሁን እና ክብራችሁን ለመግለጽ፤ እንዲሁም ለዓለም ለማስተዋወቅ በባህላዊ ልብሶች ተውባችሁ በመምጣታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ!” በማለት ለዘመናት ሲከበር የመጣውን የሴቶች በዓል አሸንዳ ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ መከበሩ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ትግራይ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባህሎች እና ቅርሶች መገኛ ናት ያሉት ዶክተር ደብረ ጽዮን፣ የትግራይ ህዝብም ቢሆን ባህሉን እና ማንነቱን ለረጅም ዓመታት ተንከባክቦ ያቆየ ህዝብ መሆኑን፤ የአሸንዳ በዓል በቱሪዝም መስህብነት የሚጫወተው ሚና  ከፍተኛ መሆኑን፤ የሃይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫውን ጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ሰው ግዴታውን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፤ በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረው፤ የአሸንዳ ልጆች የሰላም እና የፍቅር መገለጫ በመሆን አጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ እንዲሁም ስለ ፍቅር፣ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ አንድነታቸውን ጠብቀው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በትግራይ እየታዩ ያሉትን የሴቶች ጥቃቶች በንግግራቸው የኮነኑት ዶክተር ደብረ ጽዮን፣ ይህንን በመከላከል ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል በአማራ ክልል ልጃገረዶች የሻደይን በዓል በጭፈራ፣ በባህል ትርኢት፣ በፎቶ ኤግዚቢሽንና በተለያዩ ዝግጅቶች በሰቆጣ ከተማም አክብረዋል፡ ፡ በበዓሉ ሥነ ሥርዓት ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሻደይ በዓል በትውልድ መካከል የታሪክ ቅብብሎሽ ለማጠናከርና ጥላቻን ለማስወገድ ትልቅ ጠቃሜታ እንዳለው በመድረኩ ተናግረዋል፡፡ የዋግ ኸምራ ህዝብ የቀድሞ ስልጣኔ ባለቤት መሆኑን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህዝቡ አሁንም ድረስ ባህሉን ጠብቆ መቆየቱንና በዚህም አካባቢው ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ የመሆን አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሻደይ በዓል በተለይ ከባህላዊ ጠቃሜታው ባሻገር ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቃሜታ ያለውና ለአካባቢው ትውፊታዊ የሃብት ክብካቤ ሊደረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሴቶችን በራስ መተማመን ከፍ ማድረጉም የበዓሉ ትልቁ ትሩፋት ነው ብለዋል፡፡ በህዝቦች መካከል መከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ከማጎልበት አንጻር ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህ አስደናቂ ባህል ከአካባቢው ሌላ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲከበር ማድረግና ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

የአዊ፣የቅማንትና የሰቆጣ የባህል ዘፋኞችና የዋግህምራ የአሸንዳ ልጃገረዶች ከትግራይ ክልል የበዓሉ አክባሪዎች ጋር በመሆን በዓብይ ዓዲ (ተምቤን) ላይ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ባህሎች ውስጥ አንዱ የሆነው የአሸንዳ በዓል ባህሉን ጠብቀው ላቆዩት አባቶችና እናቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በዓሉ የሴት ልጆች የእኩልነትና የነጻነት ቀን መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ብዙነሽ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያውያን ታላቅ የአብሮነት በዓል ሲሆን፤ በተለይ ከአማራ ክልል ከአጎራባች ዞኖች ከመጡት ጋር አንድ ላይ ማክበሩ አስተሳሳሪና አብሮነትን የሚገልጽ ነው፡፡ በባህል ዘርፍ ለውጥ የሚመጣው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን ህዝቦች በእንዲህ ዓይነቶቹ ባህላዊ እሴቶች ላይ አብሮነታቸውን ሲያጎሉ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011 

አዲሱ ገረመው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *