“Our true nationality is mankind.”H.G.

አገራዊ ለውጡን ምን ገጠመው ? – በፖለቲከኞች ዐይን

ምክር ከትናንት ጀምሮ ‘የኢትዮጵያ ለውጥ ሂደት ሁኔታ፣ መጻኢ እድል፣ ተግዳሮትና ስጋቶች’ በሚል አገራዊ ለውጡን በኢሲኤ እየገመገመ በሚገኘው መድረክ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ጌታቸው ረዳ የየራሳቸውን ምልከታ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ያስገደዱ ምክንያቶች ምንድናቸው? ብለው በጥያቄ የጀመሩት ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፤ መሰረታዊ ችግሩ የህገ መንግስት ቅራኔ፣ ብሔራዊ አለመግባባትና የመልካም አስተዳደር እጦት መሆናቸውን ያነሳሉ።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ሲጸድቅ “የኢትዮጵያን ታሪካዊ አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲሁም የዜጎችን የአገር ባለቤትነት መብት የነፈገ ነው” በሚል በወቅቱ በህብረ ብሄራዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ በጉልህ የሚነሳ አጀንዳ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ለውጥ እንዲመጣ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶችና ዳያስፖራዎች በቅርብ ከመቀላቀላቸው በፊት፤ “ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች፣ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሙያ ማኅበራትና ነጻ ፕሬስ፣ ብዙ ታግለዋል፤ ዋጋም ተከፍሏል” ብለው ያምናሉ።

“ያም ሆኖ ለውጥ ከመጣ በኋላ አንዳንድ የኢህአዴግ አመራሮች ‘ለውጡን ያመጣነው እኛ ነን’ በሚል በመመጻደቅ ለ27 ዓመት ትግል ሲያደርጉ የነበሩትን መርሳት ለውጡን ውለታ ቢስ ያደርገዋልም” ብለዋል።

የእስረኞች መፈታት፣ የስደተኞች መመለስ፣ የሚዲያ ነጻነት፣ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ስራዎችን ከለውጡ ፍሬዎች መካከል በአብነት እንደሚነሳም ተናግረዋል።

አገራዊ ለውጡ ተስፋ እንዲጣልበት ያስቻሉትን አራት ምክንያቶችን ያነሱት አቶ ልደቱ፣ የመጀመሪው በአውዳሚ ትጥቅ ትግል ሳይሆን በአንጻራዊነት በሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ መምጣቱ፣ ሁለተኛው ለውጡ በታርክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘቱ ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ሶስተኛው ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገው ደግሞ ገዥው ፓርቲ ሽንፈቱን ተቀብሎ ይቅርታ መጠየቁ፣ እንዲሁም በአራተኛ ደረጃ የውጡን መሪ ሆነው የመጡት ሰዎች ወጣቶች በመሆናቸው አዲስ የፖለቲካ ባህል ያመጣል በሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር ነው የተናገሩት።

በመጨረሻው ለውጡ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በሚል ግምገማቸውን የጠቀሱት አቶ ልደቱ፣ “አስሮ መፍታት ሳይሆን ለችግሩ መሰረታዊ ምክንያት የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች ተፈተዋል ወይ የሚለው ከዜሮ በታች ነው” ብለዋል።

ሽንፈቱን አምኖ ይቅርታ የጠየቀው ገዥ ፓርቲ ሁሉንም በማግለል “እኔ ብቻ አሻግራችኋለሁ ማለቱ ትልቁ ችግር” መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ውለታ መዋል ካለበት እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ ራሱን መጠበቅ ነበረበት የሚሉት አቶ ልደቱ፣ “ከለውጥ በኋላ በወራት እድሜ ውስጥ ፓርቲው እርስ በራሱ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ውስጥ መግባቱ የፓርቲው ብቻ ሳይሆን የመንግስት መዋቅር እንዲዳከም አድርጓል” ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የሰላምና የህግ የበላይነት ጉዳይ በለውጥ ሃይሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ተደርገው አልታዩም፤ “የፍትህ ሂደቱም ሁሉም ተሸናፊዎች ሆነው ታሳሪና አሳሪ ሆነው መቀጠላቸው ከደቡብ አፍሪካ አለመማር ነው” ብለዋል።

የለውጥ ሃይሉ ለውጡን ወደፊት ውጤታማ ከማድረግ ይልቅ “ዳግም የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብቷል፤ አዲስ የሃይል አሰላለፍ እየተፈጠረ ነውም” ብለዋል።

ብሄራዊ መግባባትና የዕርቅ ጉዳይ “ማን ከማን ተጣላ? እየተባለ ትልቅ ጉዳይ ተደርጎ አልታየም፤ የኢኮኖሚና፣ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አልታዩም” ሲሉም ለውጡን ወርፈዋል።

በጥቅሉ የለውጥ ሂደቱ በምን ላይ ይገኛል? የሚለው በእኔ አመለካከት በጀመረው ፍጥነት አልቀጠለም፤ በማዝገም ላይ ነውም ብለዋል።

ሌላው ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል አሁን ያለው መንግስታዊ ስርዓት ሲመጣ የህገ መንግስቱ መሰረት እንዲጣል፣ የመሰብሰብና ሃሳብን በነፃነት የመግልጽ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻ  ፕሬስ የመሳሰሉ መልካም ጅምሮች ተፈጥረው እንደነበር” አስታውሰዋል።

ነገር ግን ተስፋ የተጣለበትና ከ28 ዓመታት በፊት የመጣው ለውጥ ብዙ ሳይቆይ “የአገሪቷ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በአንድ ቡድን የበላይነት ስር መውደቁን፣ የቀደመ ሰብዓዊ መብት ረገጣ መጀመሩን፣ በርካቶች ሲታሰሩ፣ ሲደኸዩና ሲሰወሩ ጥቂቶቹ ወደ ሀብት ማማ መውጣታቸውን” ይገልጻሉ።

በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎችና ህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ብዙ ግፎች መፈጸማቸውን፣ በኦሮሚያ የመሬት መቀራመት መከሰቱን በሂደትም የተደራጀ ሃይል ባይኖርም በኦሮሚያ የተጀመረው ትግል በአማራ ክልልም ቀጥሎ የለውጥ አማራጭ እንዲመጣ ማስገደዱንም አብራርተዋል።

በለውጥ አመራሩ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲቆም፣ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ሃሳብን በነጻነት መግልጽ፣ መሰብሰብ የመደራጀት መብቶች መከበራቸውን፣ ስደተኞች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መፈቀዱን፣ የተወሰኑ የሙስና ወንጀል ተጠርጣዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከለውጡ በጎ ጎኖች ለአብነት አንስተዋል።

ከውጭ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አገር ቤት ሲገቡ የለውጥ እንቅስቃሴው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን፤ ጊዜያችን አሁን ነው በሚል ለውጡን ወደ ራሳቸው አቅጣጫ ለመውሰድ የሞከሩ ድርጅቶች መፈጠራቸውን፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥ መከፋፈል መፈጠሩን በማንሳትም ለውጡ እንዳይሰምር እክል እንደተፈጠረበት ገልጸዋል።

“አንዱ ወደ አዲስ ስርዓት ለመለወጥ ሲፈልግ አንዳንዶች ወደ ቀደመው ስርዓት ለመመለስና ለመደራደር ያለመፈለግ ፍትጊያም አገሪቷ ግራ መጋባት ውስጥ እንድትገ አድርጓልም” ይላሉ።

በመሆኑም አቶ በቀለ በጀመረው ፍጥነት እየሄደ አይደለም በማዝገም ላይ ነው ብለዋል።

ከለውጥ በፊት ሲነሱ የነበሩ ሙስናና የመሬት ዘረፋ፣ የህዝብ መፈናቀል፤ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን ማሰር መቀጠሉን፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት የመሳሰሉ የዴሞክራሲያ መብቶችም መገደብ መጀመሩንም ገልጸዋል አቶ በቀለ።

“ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች በወቅቱ ባለመመለሳቸው ግጭቶች መበራከታቸውን፣ መንግስትም በጦር መሳሪያና በእስር ቤቶች መመካት መጀመሩን” አንስተው፤ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች በለውጥ ሂደቱ ስር መቀጠላቸውን አንስተዋል።

ወደፊት ምን አይነት አገር ነው መመስረት የምንፈልገው? በሚለው ጉዳይ ላይ አቶ በቀለ ሲያብራሩ፣  “ዜጎች ባህላቸው፣ ማንነታቸው፣ ቋንቋቸው ተከብሮ በእኩልነት የሚኖሩባትን አገር እንድትኖረን እንፈልጋለን” ብለዋል።

በባንዲራ እንኳን ያልተግባባን ፖለተከኞች አሁንም መነጋገር፣ አዳዲስ ተቋማትን ከመገንባት ያሉትን ማጠናከርና ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መራመድ፣ የቡድንና የግል ስሜቶቻችንን ገተን ሰላማዊ ሽግግሩን ማሳካት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሶሰተኛው ፖለቲከኛ የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ ጌታቸው ረዳ እስረኞችን መፍታትና ስደተኞችን የመመለስ ስራዎች የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ከለውጡ በኋላ የተደረጉትን ስራዎችን ተገቢነት አንስተዋል።

‘አየር መንገድ፣ ቴሌኮምና መሰል ድርጅቶች ለሽያጭ ቀርበዋል’ የሚለው ትልቁ የሪፎርም አጀንዳ ተድርጎ ይወሰዳል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ነገር ግን ይህ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ምን ያህል ተስፋ አጭሯል? የሚለው መፈተሽ እንዳለበት ተናግረዋል።

የውጭ አገራት በለውጥ ሂደቱ ላይ ያላቸው አቋም ድጋፍና ተቃውሟችው  በዋናነት በራሳቸው ጥቅም ዙሪ ላይ ያጠነጠነ በመሆኑ ከውጭ አገራት ፍላጎት ይልቅ በህዝብ ፍላጎት ላይ ማድረግ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በለውጡ ባለቤትነት መሻማት ሂደት እንደሚታይ የገለጹት አቶ ጌታቸው “ኢህአዴግን እንደ ፓርቲ ያገለለ ለውጥ ነው የተደረገው ማለትና ዶክተር አብይን የለውጥ መሪ ሌላውን ጸረ ለውጥ አድረጎ ማቅረብ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ያባብሳልም” ነው ያሉት።

በሌላ በኩል “የለውጥ አመራር እኔን ጨምሮ ከዕውነት የሚሸሽ አመራር ነው” የሚሉት ፖለቲከኛው፣ የሚፈጠሩ የሞት፣ የመፈናቀልና ሌሎች ችግሮች ነገ የሚፈቱ እንደ ተራ ነገር የሚያጋጥሙ ተደርገው እየተወሰዱ ነው በሚል ተችተዋል።

በየሰፈሩ ያልተማከለ ታጣቂ መኖሩን፣ የደቦ ፍርድ እንደሚሰጥ፣ በአጠቃላይ መንግስትን የሚፈታተን ሃይል እንዳለ በመጥቀስም የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ላይ ሂስ አቅርበዋል።

በአገሪቱ ያለውን ብሄርተኝነት እንደሌለ ቆጥሮ መንቀሳቀስም የአገሪቷንና የወጣቱን ችግር ለመፍታት አያገለግልም፣ በመሆኑም እውነቱን አውቆ ጥያቄዎችን መፍታት ተገቢ እንደሆነ ነው ያነሱት።

ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት ቀድሞውንም ባይኖሩም አሁን ባለው ለውጥ ሂደት ግን የለውጥ አካል ተደርገው እንዲንቀሳቀሱ ከማድረግ ይልቅ “እንዲገለሉ እየተደረገና መፈራረስ እየታየባቸው በመሆኑ ትልቅ ስጋት ነው” ብለዋል።

“ኢህአዴግ ካሁን በፊት የፈጸማቸው ስህተቶች መቀጠል አለባቸው የሚል ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የለም” የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ መልካም ስራዎቹን ለአገር ህልውናና ለውጥ አድርጎ መስራት አለበት ብለዋል።

“በዶክተር አብይ ስምና ዝና ላይ የተመሰረተ ለውጥ አድርጎ መንቀሳቀስ አማራጭ የፖለቲካ አስተሳስብ ባልተቀመጠበት ሁኔታ አገር ማስቀጠል ሳይሆን ትርምስ ውስጥ የሚከት ለውጥ ይሆናልም” ነው ያሉት።

ለ27 ዓመታት አገርን የመራ ድርጅት ወደ ጎን ተትቶ ለውጥ ማስቀጠል እንደማይቻል የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ “በቅርቡ ግን መቀራረብ፣ ቢያንስ ዕውነት ማውራት ጀምረናል” ብለዋል።

አሁንም ለውጡን ለማስቀጠል እድሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በጥቅሉ ለውጡን ሲገመግሙ “አሁን ባለንበት ሁኔታ ለውጡ ፈተና ውስጥ ገብቷል የሚል አምነት አለኝ” ብለዋል።

ፖለቲከኞች ባቀረቡት ግምገማ ላይ ከተሳታፊዎቹ ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪን ጨምሮ ከ200 በላይ አንጋፋና ወጣት ፖለቲኮኞችና ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች በታደሙበት የኢትዮጵያን ወቅታዊ የለውጥ ሂደት ገምጋሚ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

ኢዜአ

0Shares
0