ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ አካባቢ አመቻች ወይም (ዩኤን ሃቢታት) በጋራ በሚያቋቁሙት ግብረ ሃይል ክፍት የገበያ ቦታዎችን ለኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ በሚያስችል ሁኔታ ሊያመቻቹ መሆኑ ተገልጿል።

መንግስትና ዩኤን ሃቢታት የኮቪድ- 19 ወረርሸኝን ለመከላከል በአራት ከተሞች የሚገኙ የተጨናነቁ የገበያ ቦታዎችን ዲዛይን መልሰው ለመገንባትና ጊዜያዊ የገበያ ቦታዎችን በጋራ ለማዘጋጀት መስማማታቸው ተገልጿል።

ከዩኤን ሃቢታት የተወከሉ የከተማ ቅየሳ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ፣ ባሀር ዳር፣ ሃዋሳ እና አዳማ የሚገኙ በርካታ ባህላዊ የግብይት ቦታዎችን መጎብኘታቸው በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ የወጣው ዘገባ ያሳያል።

የግብይት ቦታዎቹ በአብዛኛው የምግብ ሸቀጦች፣ አትክልትና ፍራፍሬ አለፍ ሲልም የቆም እንስሳት የሚሸጥባቸው ሲሆኑ ልቅና በጣም የተጨናነቁ ናቸው።

የቅየሳ ባለሙያዎቹ አዲስ ዲዛይን በመስራት ያቀረቡ ሲሆን ዲዛይኑ አካላዊ ርቀትን ያማከለ፣ የእጅ መታበቢያ ቦታ ያለው፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያና የገበያ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጣቢያ የተዘጋጀለት መሆኑ ተገልጿል።

Related stories   "... ያለን ብቸኛ መፍትሔ የኢትዮጵያን ሕዝብ አብሮነት መመለስ ነው" ዶ/ር ኢንጅነር ጥላሁን

ከዚህ ባለፈ በበርካታ ቦታዎች ጊዜያዊ የገበያ ስፍራዎች እንደሚቋቋሙ በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ ተመላክቷል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን ክፍት ገበያ መልሶ ማዋቀሪያ መመሪያና ዲዛይን መቀበሉ ተገልጿል።

የተሻሻለው ዲዛይን በዩኤን ሃቢታት ተጠሪዎችና በከተሞቹ ከንቲባዎች አማካኝነት በመጪው ሳምንት ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

“ክፍት የገበያ ቦታዎች በተገቢው መንገድ ካልተገነቡ መጨናነቃቸው የማይቀር ነው። የዚህ አይነት የገበያ ስፍራዎች መልሰው ካልተዋቀሩ ቫይረሱን የማስፋፋት አቅማቸው ከፍተኛ ነው” በማለት የዩኤን ሃቢታት የአፍሪካ ተጠሪ ቶማስ ሲራምባ ተናግረዋል።

“ዩኤን ሃቢታት የገበያ ቦታዎችን በአዲስ መልክ ዲዛይን ለማድረግና ለማዋቀር የጀመረው ስራ የቫይረሱን ስርጭት ከመቀነስ ባለፈ የዜጎችን ኑሮ ምቹ ለማድረግ ያግዛል።”

የገበያ ስፍራዎቹን ምቹ ለማድረግ የተዘጋጀው መመሪያና በአዲስ መልክ የተሰራው ዲዛይን ዩኤን ሃቢታት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያከናውነው ቀዳሚ ምላሽ ነው ተብሏል።

Related stories   የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለሽሬ እና አካባቢው አልሚ ምግብና መድሃኒት መላኩን ገለጸ

ከዚህ በተጨማሪ በቆሼ አካባቢ የእጅ መታጠቢያ ቁሶችን በማቅረብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የራሱን እገዛ ማድረጉ ዩኤን ሃቢታት በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል።

ዩኤን ሃቢታት በአውሮፓዊያኑ ቀመር ከ1998 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀምቶችን በማከናወን ይጠቀሳል።

በተለይ ደግሞ ለዘላቂ የከተማ ልማት ግንባታ መርሃ ግብር የአቅም ግንባታ ስራዎችንና የከተማ ልማት ፖሊሲዎችን በማገዝ ይታወቃል።( ኢዜአ)

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *