በሱማሌ እና በ ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረ ግጭት ፣ ከሞቀ ቤታቸው እና ንብረታቸው የተፈናቀሉ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ኑሯችን ምስቅልቅል እንዳለ ሶስት አመት ሊሞላን ነው ፣ መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ቅሬታቸውን ለጣቢያችን አቅርበዋል፡፡

በ11 የተለያዩ አከባቢዎች ሰፍረው የሚገኙት ተፈናቃዮቹ ፣ ኑሯችን ምስቅልቅል እንዳለ ሶስተኛ አመታችን እየደረሰ ነው ፣ እስከመቼ ነው የሰው እጅ እያየን የምንኖረው ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሩዝና ስንዴ እንዲሁም አንድ ሊትር የማይሞላ ዘይትም ይሰጠናል ፣ አሁን ፈታኝ ችግሩ ውስጥ ነው ያለነው የተሰጠንን ስንዴና ሩዝ በመሸጥ ለማብሰያ የሚሆን ሽንኩርትና መሰል ግብዓቶችን እንገዛለን ፣ ለንጽህና መጠበቂም ሳሙና የምንገዛው ከዚሁ ላይ ነው በዚህም ምክንያት የከፋ ችግር ገጥሞናል ብለዋል እነዚህ ተፈናቃዮች፡፡

በመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፉም በ3 ወር በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ችግራችንን አሳሳቢ ያደርገዋል ፣ ሽንኩርትም ፣ ቲማቲምም ፣ ድንችም የምንገዛው የሚሰጠንን እህል በመሸጥ ነው እኛም ልጆቻችንም ችግር ውስጥ ነን ያለነው ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡

ልጆቻችንም ችግር ውስጥ ነው ያሉት አሁን ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ ለተለያዩ የጤና እክል እየተጋለጡብን ነው ፣ ገቢ የሚያስገኝ አንድም ስራ የለንም ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለነው ፣ ይህ የሰው እጅ በመጠበቅ ብቻ ሶስት አመት ሊሞላን ነው፣ የሰው እጅ መጠበቅ ደግሞ ከረሀብ አላዳነንም ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮምንኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው ፣ ከሞቀ ቤቱ እና ንብረቱ የተፈናቀለ ሰው መልሶ ለማደራጀት ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ይተወቃል ፣ መንግስትም የተፈናቃዮችን ችግር ለመቅረፍ በእቅድ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ቀድመው ወደ ነበሩበት አከባቢ መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ የነበረው ጥረት በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት ተቀዛቅዟል ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አስኪገኝ መንግስትም የተቻለውን ያደረግጋል ህብረተሰቡ በየአካባቢው ላሉት እና ችግር ላይ ለሆኑን ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከሶስት አመት በፊት በሱማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መፈናቀላቸው ተከትሎ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም መዘጋጀቱ ይታወሳል።

ከተገኘው ገቢ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በቅርቡ ስራ ይጀመራል መባሉንም ከሀላፊው ሰምተናል፡፡
ethio FM

በዳንኤል መላኩ

ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *