አቤሴሎም ነጋ የተባለውና ነዋሪነቱ በአውስትራሊያ የሆነው ስብሃት ነጋ ወንድም 4 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር (2.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር) በማጭበርበርና በመስረቅ መከሰሱን Herald Sun ዘገበ።

እኤአ ከ2008 – 2019 ባሉት ዓመታት የ54 ዓመቱ አቤሴሎም ነጋ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎችን በመፈጸም ነው 4.2 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ወደ ግል የባንክ ሒሳቡና iEmpower በሚል ለሚመራው የግል ድርጅቱ ሒሳብ እንዲገባ ያደረገው። ወንጀሉ ስርቆት ብቻ ሳይሆን በኑሯቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የሚሰጠውን (የዌልፌር) ገንዘብን አጭበርብሮ መውሰድም የሚጨምር ነው።

አቤሴሎም ከዘረፈው ገንዘብ ውስጥ $25,300 የሚሆነውን ያጭበረበረው ከሕግ ጋር ችግር ያለባቸውን የአፍሪካ ወጣቶችን ለመርዳት ከተቋቋመ ድርጅት በመስረቅ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አቤሴሎም የቪክቶሪያ ጠቅላይ ግዛት የእኩል ተጠቃሚነትና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የቦርድ አባል ለመሆን ብሎ ባቀረበው ሰነድ ማጭበርበሩና መዋሸቱ ተደርሶበታል። በዚሁ ጠቅላይ ግዛት ታዋቂ የአፍሪካውያን ማኅበረሰብ ተወካይ ሆኖ ይጠቀስ የነበረውን አቤሴሎም፤ ፖሊስ ለሁለት ዓመታት ሲከታተለው እንደነበር የዜና ዘገባው ያስረዳል። ክሱ እስካሁን ሊዘገይ የቻለው በየጊዜው ሲለዋወጣቸው የነበሩትን የስልክ ንግግሮች ለማስተርጎም ጊዜ በመውሰዱ ነው።

የመርማሪዎቹ መረጃ እንደሚጠቁመው አቤሴሎም የሃሰት ሰነዶችን በማቅረብ iEmpower ለተባለው ድርጅቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ “ባፋጣኝ ገንዘብ ያስፈልጋል” በሚል እያምታታ ሲወስድ መኖሩን ያመለክታል። ይህንን ወንጀሉን ለመደበቅ በየዓመቱ በሚያወጣው የፋይናንስ ዘገባ መረጃ በመደበቅ ሪፖርት ያደርግ እንደነበር ተደርሶበታል።

በሌብነት የተከሰሰው አቤሴሎም ወሳኝ ከሆኑ የጠቅላይ ግዛቱና የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ትሥሥር በመፍጠር ለመታወቅ የበቃ ሲሆን ኅብረባህላዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በሚዲያ አስተያየት በመስጠት የሚታወቅም ነበር። ከዚህ በፊትም የቪክቶሪያ ግዛት ኅብረባሕላዊ ኮሚሽነር እንደነበር ለመታወቅ ተችሏል።

አቤሴሎም የሃሰት ማስረጃ በማቅረብ ከጥቅምት 2012 እስከ ነሐሴ 2018 የቪክቶሪያ ጠቅላይ ግዛት የእኩል ተጠቃሚነትና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የቦርድ አባል በመሆን 21,578 ዶላር በማምታታት ለራሱ ያደረገ ሲሆን ለቃልና ጽሁፍ ተርጓሚዎች ዕውቅና የሚሰጠው ባለሥልጣን የቦርድ አባል እንደነበር የወጣው ዘገባ ይጠቁማል።

አቤሴሎም፣ ዳንኤል ነጋ ከተባለ ጋር በማሤር የ iEmpower የኦፐሬሽን መምሪያ ኃላፊ በሆነው ሪቻርድ ራያን ላይ የከፋ ጉዳት ለማድረስ በሚል ተጨማሪ ክስ ቀርቦበታል።

ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዝርፊ፣ ማጭበርበርና ሌብነት በጠቅላይ ግዛቱ ከፍተኛ የድንጋጤ ንዝረት ፈጥሯል። አቤሴሎም በዋስ የተፈታ ሲሆን ፍርድ ቤት ሴፕቴምበር 23 በድጋሚ ይቀርባል።

ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም ሲገዛ የነበረው ህወሃት የተባለው የበረሃ ወንበዴዎች ቡድን በሥልጣን ለረጅም ዓመታት የቆየው እንደ አቤሴሎም ዓይነቶች በሚደጉሙት እንደሆነ ይህ አንድ ማሳያ ነው። ስብሃት ነጋ የተባለው ቀንደኛ የወንበዴ በረኸኞቹ አባት ከሌሎቹ ወንበዴዎች ጋር በመሆን መቀሌ መሽጎ የወንድሙን ዓይነት “ዕድል” እየተጠባበቀ የሚገኝ ይመስላል።

ይህ ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ሒደት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና በተለይ በፖለቲካው ዓለም በየዕለቱ የዓመጽ ተግባራትን ከሚሰብኩት አንደ ጸጋዬ አራርሳ ዓይነቱ የአቤሴሎም ዕጣ እንዲደርሳቸው ለማድረግ በርትተን መታገል አለብን በማለት ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ተናግረዋል።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *