አይ ትንተና !! አይ መረጃ –
ይህንን ትንተና ሳነበው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “አሃዳዊ ” በመሆናቸው ጃዋር ስላልተመቻቸው አሳሰሩት ነው ድምዳሜው። አሃዳዊ የምን ቋንቋ ነው? የማን ክስ ነው? የብልጽግና መመስረት ህመም የሆነው ለማን ነው? የብልጽግና መመስረት ሌሎችን ለምን አሳሰበ? ለምን አጋሮች ሲባሉ የነበሩት እያሉ ሌሎች ተቃውሞ ውስጥ ገቡ? ምን አገባቸው? ጃዋር የመሰለውን ፍልስፍና መከተል መብቱ ነው። ግን ቄሮን ያደራጀው እሱ ነው? ቢቢሲ ምን ማስረጃ አለው?
ይህንን ለማወቅ የዛሬው የኦነግ ዩኒቲ ወይም የአባ ነጋ ምክትል ሆኖ የተመረጠውን የጥቁር ኢንጪኒ ልጅ ፈልጎ ማነጋገር ይበጃል። እነ አባ ነጋ የኦሮሞ ድርጅቶች ወደ ህብረት እንዲመጡ ሲጋበዙ አልተጋበዙም። በደጋፊ፣ በተቀባይነት፣ ግዙፍ መሆናቸው እየታወቀ ለምን ተዘለሉ? ለምን በይተኛውም መድረክ አይጋበዙም? ለምን ኦ ኤም ኤን ላይ አናያቸውም?
የ OLF unity ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ በቅርቡ የተሾመውን የጥቁር ኢንጪኒ ወጣት ቢቢሲ ቢያነጋግረው የቄሮን ባለቤትና አደራጅ በግልጽ ይረዳ ነበር። ፓሪያቸውም ከተለያዩ ህብረቶችና ከተለያዩ ጉዳዮች የሚገለለው ለምን እንደሆነ ያስረዳ ነበር።
ሌላው ጃዋር ከቄሮ ጋር ስሙ የተጎዳኘው በወቅቱ ኦህዴድ ህወሃትን የመፈንቀል ትግሉን ሲያጧጡፍ ራሱ የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት ስለማይችል ጃዋር ይህንን ስራ እንዲሰራ መደረጉን ለማ መገርሳ የተናገሩትን መስማት በቂ ነው። ጃዋር ቀስ እያለ ሚዲያውን ሲቆጣጠር አብረውት የነበሩና ያባረራቸው ወገኖችም ማስረጃ ናቸው። በዚያ ሃላፊነት ውስጥ ሆኖ ኦህዴድ መዋቅር ውስጥ ገባ። ኦህዴድ ከለውጡ በሁዋላ ቀስ እያለ ከፍቶት የነበረውን በር ሲዘጋጋ ቅሬታ ተፈጠረ። ” ተካድን” የሚለው ዘመቻ ተነሳ።
ዛሬ ቄሮን የሚመሩት የእን ጃዋር ሃይል ቢሆን ኖሮ ድፍን ኦሮሚያ ልክ ከለውጡ በፊት በኦህዴድ ፈቃድ በአመጽ እንደሚቆጣጠሩት ማድረግ በቻሉ ነበር። እርግጥ እነ ጃዋር ደጋፊ ቢኖራቸውም ድፍን ኦሮሚያ አይደለም። መንደርና ሰፈር የለየ ነው። ቢቢሲ በዚህ ትንተናው ይህቺን መረጃ ወስዶ አድማሱን ሰፋ ቢያደርግ እንደ አንድ ትልቅ ሚዲያ ከተውሶ ማደናበሪያ ቃላት ራሱን ነጻ ማውጣት ይችላል የሚል እመነት አለኝ!! ወደፊት የማውቀውን እጽፋለሁ።
ገመቹ ከዋሽንገቶን ዲሲ
ሃሳቤን የገለጽኩበት የቢቢሲ ትንተና ከታ ች ያለው  ነው። ለፍርድ እንዲመች እንዳለ ቀርቧል።

ጃዋር መሐመድ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ

አሁን ላይ በእስር ከሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አንዱ የሆነው አቶ ጃዋር መሐመድ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ “ወደ ሕገ ወጥ መሪነት” እያመሩ ነው ማለቱ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ሽልማት ካገኙ ወዲህ ከታሰሩ እውቅ የተቃውሞ ፖለቲከኞች አንዱ ጃዋር፤ ፌስቡክ ላይ ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ተከታዮች አሉት።

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተነሳው ግርግር በቁጥጥር ሥር ከዋሉ አንዱ ሲሆን፤ በግርግሩ ሳቢያ ከተገደለ ፖሊስ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶበታል።

ደጋፊዎቹ ክሱን በማጣጣል፤ የታሰረው በጠቅላይ ሚንስትሩ ትዕዛዝ፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ለማክሸፍ ነው ይላሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይና ፖለቲከኛው ጃዋር የወደፊቷን ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላቸው ራዕይ የተለያየ ይመስላል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ሲይዙ በብሔር መስመሮች የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያ ለማዋሃድና ዴሞክራሲ ለማስፈን ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

የመንግሥትን ሐሳብ የሚደግፉ አካላት፤ ጀዋር መታሰሩ ብሔርን ያማከለ ንቅናቄን ለማክሰም ያግዛል ይላሉ። ከጠቅላይ ሚንስትሩ የ “አንድነት” ራዕይ በተቃራኒው ብሔር ተኮር ግጭቶት ለመነሳታቸው ጀዋርን ተጠያቂ ስለሚያደርጉም መታሰሩን በበጎ ያዩታል።

በተቃራኒው የጃዋር ደጋፊዎች እንደሚሉት መታሰሩ፤ ለ34 ዓመታት ሲቀነቀን የነበረው የኦሮሞ እንዲሁም የሌሎች ብሔሮች ራስን የአስተዳደር ሀሳብን ጠቅላይ ሚንስትሩ ማስተናገድ እንዳልቻሉ ያሳያል ይላሉ።

“መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ”

ጃዋር የተወለደው እንደ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1986 ነው። አባቱ ሙስሊም እናቱ ደግሞ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ናቸው።

ያኔ በስደት አሜሪካ የነበረው ጃዋር 2013 ላይ ከአልጀዚራ ጋር ባደረገው ቆይታ “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ” ብሎ፤ ኢትዮጵያዊ የሚለው ማንነት “እንደተጫነበት” ገልጾ ነበር።

በኬል ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት አወል አሎ የዚያን ጊዜውን የጃዋር አስተያየት “ፖለቲካዊ ሱናሚ” አስነስቷል ብለው ነበር።

ንግግሩ በኢትዮጵያና በውጪ አገራትም ጃዋርን በእጅጉ በሚደግፉና አጥብቀው በሚተቹ ሰዎች መካከል የጋለና የተካረረ ክርክርንም አጭሮ ነበር።

“መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ” የኋላ ኋላ ወደ ፖለቲካዊ ንቅናቄ አድጓል። ጃዋር በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በመዘዋወር ዳያስፖራው የኢትዮጵያን አገዛዝ እንዲያወግዝ፣ ለነፃነቱ እንዲታገልም ቀስቅሷል።

ንቅናቄው ይበልጥ የተቀጣጠለው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) 2013 ላይ የቴሌቭዥንን ጣቢያ በከፈተበት ወቅት ነው። ጣቢያው ሲመረቅ ጃዋር “አሁን የኦሮሚያን አየር ሞገድ ነፃ አውጥተናል” ማለቱ ይታወሳል።

የኦኤምኤን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳለ፤ ጣቢያው የወጣቱን (ቄሮ) ድምጽ እንዲያስተጋባ አድርጓል። ቄሮ የሚለው መጠሪያ በስፋት የተዋወቀው በ1990ዎቹ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አማካይነት ነበር።

ኦነግ ከሚንቀሳቀስባቸው ከተሞች በአንዱ ያደገው ጃዋር “የተወለድኩት በኦሮሞ ትግል ውስጥ ነው፤ በአምባገነኖች እና በአጼዎቹ ዘመን የኦሮሞ ሕዝብ መጨቆኑን አስተውያለሁ” ይላል።

ጃዋር መሐመድ ከኢትዮጵያ የወጣው በወጣትነቱ ነው። 2003 ላይ ሲንጋፖር የነፃ ትምህርት እድል አግኝቶ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ አሜሪካ ሄዶ ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ 2013 ላይ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በሰብዓዊ መብት ይዟል።

በርካታ ወጣቶች በተቃውሞ ላይ

ዋርና ጠቅላይ ሚንስትሩ

ጃዋር የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለ ራሱን ከኦነግ አርቆ ነበር። በአመራሩ መካከል ያለው መከፋፈል ግንባሩን “እንዳይጠገን አርጎ ሰብሮታል” ሲል በጦማሩ ላይ ጽፎ ነበር።

ሆኖም ዳያስፖራ የኦሮሞ ተወላጆች የአገር ቤቱን ትግል እንዲደግፉ ከማነሳሳት ወደ ኋላ አላለም። በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመነሳቱ ምክንያት ከሆኑ እንቅስቃሴዎች አንዱም ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዶ/ር ዐብይ ሲተኩ፤ ጀዋር “ስትራቴጂያዊ ስህተት” ብሎ ሥልጣኑን መያዝ ያለባቸው የአሁኑ የመከላከያ ሚንስትር አቶ ለማ መገርሳ እንደሆኑ ተናግሮ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመሪነት መንበሩን እንደያዙ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ ሲያደርጉና ጃዋርን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ውጪ የነበሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ከ ‘ሽብርተኛ’ መዝገብ ከሰረዙ በኋላ፤ ጃዋር ጠቅላይ ሚንስትሩን መደገፍ ጀምሮ ነበር።

ወደ አገር ቤት ተመልሶም የኦኤምን ቅርንጫፍን በአዲስ አበባ ከፍቷል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትሩን በመደገፉ አልገፋበትም። የራስ አስተዳደር ለሁሉንም ብሔሮች የምጣኔ ሃብት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥና መረጋጋትን የሚፈጥር ነው ብሎ ስለሚያምን ከጠቅላይ ሚንስትሩ በተቃራኒው ቆሟል።

የጃዋር መታሰር ደጋፊዎቹ በጠቅላይ ሚንስትሩ የነበራቸውን የተስፋ ጭላንጭል ያከሰመ ይመስላል። በተለይም በኮቪድ-19 ሳቢያ የተራዘመው ምርጫ ጉዳይ የሚነሱትን ጥያቄዎች አጉልቷቸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እና ኦፌኮ

ጠቅላይ ሚንስትሩ በብሔር ውክልና ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባርን (ኢሕአዴግ) አክስመው ብልጽግና ፓርቲን ፈጥረዋል።

ጃዋር ደግሞ ከኦኤምኤን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለቆ፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ተቀላቅሏል።

ኦፌኮ እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ሊኖር በሚችልባቸው አካባቢዎች በተቀናቃኝነት ሳይሆን በመደጋገፍ ለመሥራት ተስማምተዋል። ይህም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በኦሮሚያ የምርጫ ቀጠናዎች ሊያገኙ የሚችሉትን ድምጽ ሊያሳጣ ይችላል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በወረርሽኙ ስጋት ሳቢያ ምርጫው እንደተራዘመ ማስታወቁን ተከትሎ፤ ጃዋር ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከመስከረም 2013 ዓ. ም በኋላ “ሕገ ወጥ መሪ” ናቸው ብሏል።

የኦፌኮ አመራሮች እንደሚሉት የጀዋር ጠበቃና ቤተሰቦቹን እስካሁን ሊያገኙት አልቻሉም። የረሃብ አድማ ላይ እንደሆነም የፓርቲው አመራሮች ገልጸዋል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *