በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን የከተማ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ እንዳለ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ።
የዘርፉ ምሁራን በበኩላቸው የሚገነቡ ቤቶች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለነዋሪዎች መቅረብ እንዲችሉ የከተማ ፕላንና የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የከተማ ልማት ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድን ለዘርፉ ተዋንያን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት በመሪ የልማት ዕቅዱ ለከተማ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመኖሪያ ቤትና መሰረተ ልማት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከ24 ሚሊየን በላይ መሆኑን ጠቅሰው “እስከ 2022 ዓ.ም ቁጥሩን ወደ 40 ሚሊየን በማሳደግ 35 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የከተማ ነዋሪ ይሆናል” ብለዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ከተሞች የሚነሳውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ኢ-ፍትሃዊነትና የጥራት ችግር ለማሻሻል በመንግስት፣ በባለሃብቶች፣ በማህበራትና በሌሎችም መንገዶች 4 ነጥብ 4 ሚሊየን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ዛሬም ቅሬታ እየተነሳ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ “በመሪ የልማት ዕቅዱ የተገልጋዮችን እርካታ 80 በመቶ ለማድረስ እንሰራለን” ብለዋል።
እንደ ኢንጂነር አይሻ ገለጻ በከተሞች የድህነት ምጣኔን ከ15 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ በማድረግ የከተሞች ምርት የሀገራዊውን ጥቅል ኢኮኖሚ 73 በመቶ ለመሸፈን ዕቅድ ተይዟል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የከተሞች ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ፍቅረስላሴ ኢትዮጵያ በከተሞች ላይ ለመስራት ያቀደችው ዕቅድ ጤናማና ሊሳካ የሚችል ብለውታል።
የሚገነቡ ቤቶች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለነዋሪዎች መቅረብ እንዲችሉ የከተማ ፕላንና የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
“ዕቅዱ እውን እንዲሆንም ከተሞች የሚመሩባቸው ህጎችና ደንቦች ማስፈጸሚያ ፕላን ሊኖራቸው ይገባል” ብለዋል።
የዓለም ከተሞች የተመሰረቱት በሦስት በመቶ የመሬት ክፍል ላይ ቢሆንም 70 በመቶ የሚሆነውን ጥቅል ምርት እንደሚያመርቱ አመልክተዋል።
“ከተሞች ዘመናዊ ሆነው ለሰው ልጅ አስፈላጊውን ጥቅም መስጠት እንዲችሉ ‘የት ምን፣ ለምንና እንዴት መሰራት አለበት’ የሚለውን ግልጽ ፕላን መንደፍ ይገባል” ብለዋል።
“በፕላን የማይመሩ ከተሞች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል” ያሉት ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት የከተማ ልማት ክፍል ኃላፊ ዶክተር እድላም አበራ ናቸው።
የሥራ ዕድል የማይፈጥር የከተሞች መስፋፋት ረብ የለሽ መሆኑን ጠቁመው ከተሞችን በትክክል ማሳየት የሚችል የመረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ከአሁን በፊት የነበረው የመሬት ዝግጅት ፍላጎትና አቅርቦትን መሰረት ያደረገ እንዳልነበር ጠቁመዋል።
በዚህም መሬቱ ከተዘጋጀ በኋላ ለዓመታት ጥቅም ላይ ሳይውል ስለሚቀመጥ ህገ ወጥ የመሬት ቅርምት እንደነበር ገልጸዋል።
በቀጣይ የመሬት ዝግጅትና አቅርቦት ለምንና ለማን እንደሚዘጋጅ ከመለየት ባለፈ ፍላጎትን መሰረት አድርጉ የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ በፕላን ላይ ያለው የከተሞች መሬት 30 በመቶ በአረንጓዴ ልማት የሚሸፈን ይሆናልም ተብሏል።
በገጠር ማዕከላት ተጨማሪ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ሲሆን ከደረጃ በታች ያሉ ቤቶች አሁን ካሉበት 74 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ይደረጋሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *