ለወጪ ንግድ የሚውሉ የግብርና ምርቶችን በሕገ-ወጥ መንገድ የላኩ እና በክምችት የያዙ 69 ላኪዎች ላይ ርምጃ መውሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይት የሚፈጸምባቸው የሰሊጥ፣ የነጭ ቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር እና የማሾ ምርቶችን ከዓለም አቀፍ ዋጋ በላይ ከምርት ገበያ በመግዛት የግብይት መዛባትን ያስከተሉ ላኪዎች ላይ ነው ሚኒስቴሩ ርምጃው የወሰደው።
የተወሰደው ርምጃ ከምርት ገበያ ግብይት ከመታገድ እስከ ንግድ ፈቃድ እገዳ የሚደርስ መሆኑን የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባደር ምሥጋኑ አረጋ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከክልል መንግሥታት የግብይት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት እና የመስክ ቅኝት (ኢንተለጀንስ) ሥራዎችን በማከናወን ምርቶችን በሕገ-ወጥ መንገድ በክምችት የያዙ የግብይት ተዋንያን ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ ወስዷል።
በክምችት የተያዙ ምርቶች ወደ ምርት ገበያ ኢንዲገቡ መደረጉንና ይህንን ተግባራዊ ያላደረጉ እና 5 ሺህ 542 ቶን ቀይ ቦሎቄ የሰወሩ 10 ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው መሰረዙንም አመልክተዋል።
የወጪ ንግድ ምርቶችን የግብይት ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገራት የላኩ 59 ላኪዎች ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸው ለሦስት ወራት ታግዷል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት ከክልል መንግሥታት የግብይትና በወጪ ንግድ ላይ ከሚሠሩ ቢሮዎች፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከግብይት ተዋንያን ማኅበራት ጋር በሠራቸው ቋሚ ቅንጅታዊ ሥራዎች 374 ሺህ 514 ቶን የሰሊጥ፣ የነጭ ቦሎቄ፣ የቀይ ቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር እና የማሾ ማርቶች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገቡ ማድረጉን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማስታወቁን የዘገበው አብመድ ነው።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *